በሃሚድ አወል
የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ወጥ የሆነ የካሳ ግመታ ስርዓት አለመኖር የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለመከወን ችግር እንደሆነበት አስታወቀ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የካሳ ግመታ ክፍያዎች “በጣም የተጋነኑ” መሆናቸውንም ገልጿል። በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ፤ ሚኒስቴሩ በህግ የተሰጠውን ስልጣን “በአግባቡ እየተወጣ አይደለም” ሲል ወቅሷል።
ይህ የተገለጸው፤ መብት እና ግዴታዎቹ በአዋጅ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተላለፈውን “የፌደራል የተቀናጀ መሰረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ” በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ጥር 22፤ 2015 በተወካዮች ምክር ቤት ውይይት በተካሄደበት ወቅት ነው። ውይይቱ የተካሄደው፤ የቀድሞው ኤጀንሲ የስራ አፈጻጸምን በተመለከተ የፌደራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ባለፈው ዓመት ለፓርላማው የላከው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን መሰረት በማድረግ ነው።
ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የነበረው ይህ ኤጀንሲ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ገደማ ሲቋቋም፤ “በመንገዶች ማስተር ፕላን ላይ የተመሰረቱ የተቀናጁ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲካሄዱ የማስተባበር” ዓላማን ይዞ ነበር። “በተቀናጀ የመሰረተ ልማት ስራ ምክንያት ለሚነሱ ንብረቶች እና ለሚለቀቁ የመሬት ይዞታዎች የካሳ ግምት ቀመር ማዘጋጀት” ኤጀንሲው ከተጣሉበት ኃላፊነቶች ውስጥ የሚጠቀስ ነው። ምንም እንኳ ኤጀንሲው ባለፈው ዓመት መስከረም ወር አዲስ መንግስት ሲመሰረት በአዋጅ እንዲፈርስ ቢደረግም፤ የመስሪያ ቤቱ የ2013/ 2014 የክዋኔ ኦዲት ግን በዛሬው ዕለት ውይይት ተደርጎበታል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተዘጋጀው በዚህ ውይይት፤ ከመሰረተ ልማት ቅንጅት እና ከካሳ አከፋፈል ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ተነስተዋል። የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ የኤጀንሲውን ስልጣን እና ኃላፊነት ለተረከበው ለከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች፤ እነዚህን ጉዳዮች የተመለከቱ ጥያቄዎች አቅርበዋል።
በቋሚ ኮሚቴው ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል “በመሰረተ ልማት ግንባታ ወቅት አንዱ ተቋም በሌላው ላይ ጉዳት ሲያደርስ ግልጽ የካሳ አከፋፈል ለምን አልተዘረጋም?” የሚለው ይገኝበታል። “የካሳ ክፍያዎች በጊዜው ያልተከፈሉበት ምክንያት” ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥም ተጠይቋል። የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ወንድሙ ሴታ ለእነዚህ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ “የመሰረተ ልማት አቅራቢዎች የሚጠይቋቸው የካሳ ክፍያዎች በጣም የተጋነኑ ናቸው” ብለዋል።
ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆነውን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርን በምሳሌነት ያነሱት ሚኒስትር ዲኤታው፤ “ወጥ የሆነ የካሳ ግመታ ስርዓት አለመኖሩ” ለተቋሙ ችግር እንደሆነበት ገልጸዋል። የካሳ ግመታን በተመለከተ ክልሎች የራሳቸውን መመሪያዎች አውጥተው እንደሚተገብሩ የገለጹት አቶ ወንድሙ፤ “በሁሉም አካባቢዎች ያለው ጉራማይሌ ነው። ጉራማይሌ ብቻም ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ ካሳ ነው የሚጠየቀው” ሲሉ ችግሩን ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል።
የካሳ ግመታ ጉዳይ እስካሁንም “ያልተሻገርነው ችግር ነው” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ “ከፍተኛ የካሳ ክፍያ” ጥያቄዎች የሚቀርቡት በፌደራል መንግስት በሚሰሩ ፕሮጀክቶች ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። “የፌደራል ተቋማት መሰረተ ልማት መጣ ሲባል የሚከፈለው የካሳ ክፍያ፤ [ከሚሰራው] መንገድ በላይ ነው” ሲሉም አቶ ወንድሙ የችግሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል።
በዛሬው ውይይት የተገኙት የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት፤ ከሚኒስቴር ዴኤታው ምላሽ በኋላ ተጨማሪ ምላሽ እና ማብራሪያ ይሻሉ ያሏቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል። ከካሳ ክፍያዎች ጋር በተያያዘ “አሉ” የተባሉ ችግሮችን “በተጨባጭ የማናውቃቸው ናቸው” ያሉት እየሩሳሌም ሌዊ የተባሉ አባል፤ “ተቋሙ መፍትሔው ምንድን ነው ብሎ ነው የሚያምነው?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል። ነኢማ ኡስማን የተባሉ ሌላ አባል ደግሞ፤ የካሳ ክፍያ “ከህብረተሰቡ ወቀሳ” እንደሚነሳበት ጠቅሰው የካሳ ግመታው “ከምን አንጻር ነው የተለያየው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ዴኤታው በምላሻቸው፤ መስሪያ ቤታቸው “ዋና ችግር” ብሎ የለየው የካሳ ግመታ ቀመር አለመሆኑን ገልጸዋል። “የካሳ አዋጁ ወጥቷል ግን ካሳው የሚመራበት ቀመር የለም። እሱን ቀመር እያዘጋጀን ነው” ያሉት አቶ ወንድሙ፤ የካሳ ተመን ስነ ስርዓትም እየተዘጋጀ መሆኑን ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። በዚህ በጀት ዓመት መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የካሳ ቀመር እና ተመን ስነ ስርዓቱ፤ ለክልሎች እንደሚላክም ሚኒስቴር ዲኤታው አስረድተዋል።
አቶ ወንድሙ በምላሻቸው ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ የካሳ ግመታን የማውጣት ስልጣን ነው። “አዋጁ ግምት እና ሌሎች ጉዳዮችን ስልጣን የሚሰጠው ለታችኛው መዋቅር ነው” ያሉት አቶ ወንድሙ፤ “ይህ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ የመንገዶች አስተዳደር ካሳ የመክፈል እንጂ በቀረበው የካሳ ግምት ላይ አስተያየት የማቅረብ ስልጣን እንኳን የለውም” ሲሉ ችግሩን አብራርተዋል።
በውይይቱ ማገባደጃ ላይ በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ የማጠቃለያ ሀሳቦችን አንስተዋል። አቶ ክርስቲያን “የካሳ ግመታዎች ወጥነት እንዲኖራቸው፤ የገንዘብ ሚኒስቴር አስቻይ አሰራር እንዲዘረጋ እና ተግባራዊነቱን እንዲከታተል እንፈልጋለን” ሲሉ በውይይቱ ለተነሱ ችግሮች ገንዘብ ሚኒስቴር መፍትሔ እንዲያበጅ አሳስበዋል።
በዛሬው ውይይት የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በሰጣቸው ምላሾች ላይ “የዝግጅት ማነሶች ይስተዋላሉ” ሲሉ የተቹት ዋና ሰብሳቢው፤ “የተሰጣችሁን ስልጣን በአግባቡ እየተጠቀማችሁ አይደለም” ሲሉ የስራ ኃላፊዎቹን ወቅሰዋል። “ይህ ተቋም በህግ የተሰጠውን ስልጣን፤ እንዲሰራ የተቋቋመበትን ዓላማዎች መወጣት ካልቻለ፤ የመስሪያ ቤቱ መቋቋም ለህዝቡ የሚሰጠው ጠቀሜታ ምንድን ነው?” ሲሉም ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)