በሶማሌ ክልል “ያለ ፈቃድ በጋዜጠኝነት ስራ ተሰማርተዋል” የተባሉ 15 መገናኛ ብዙሃን ታገዱ 

በአማኑኤል ይልቃል

ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን “ፈቃድ የላቸውም” የተባሉ 15 መገናኛ ብዙሃን እና ወኪሎቻቸው፤ በሶማሌ ክልል የሚያከናውኑትን የዘገባ ስራ እንዲያቆሙ ታዘዙ። የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር፤ ከውሳኔው አስቀድሞ “ንግግር መደረግ ነበረበት” ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል።

ውሳኔውን ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ጥር 20፤ 2015 በጻፈው ደብዳቤ ለመገናኛ ብዙሃኑ እና ወኪሎቻቸው ያስተላለፈው፤ የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ነው። ስራ እንዲያቆሙ በደብዳቤው ትዕዛዝ ከተሰጣቸው መገናኛ ብዙሃን መካከል፤ የቢቢሲ የሶማሊኛ ቋንቋ አገልግሎት፣ ዩኒቨርሳል ቲቪ፣ ስታር ቲቪ፣ ኤም ኤም ቲቪ እና ሆርን ኬብል ቲቪ ይገኙበታል። 

በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሱት እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ማስጠንቀቂያው የደረሳቸው፤ ውሳኔው ከመተላለፉ አንድ ቀን አስቀድሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ደብዳቤ መጻፉን ተከትሎ ነው። በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ የተፈረመው ይህ ደብዳቤ፤ በሶማሌ ክልል “ከባለስልጣኑ እውቅና ሳይኖራቸው የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የውጭ ሀገር ሚዲያ ወኪሎች፣ ተቀጣሪዎች እና ጋዜጠኞች” እንዳሉ መስሪያ ቤታቸው ባደረገው “የማጣራት እና የክትትል ስራ” እንዳረጋገጠ ይገልጻል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱት እነዚህ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ወኪሎች፤ “በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ገብተው በጋዜጠኝነት ስራ የተሰማሩ” እንደሆኑም በደብዳቤው ላይ ሰፍሯል። የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ “ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር አስፈላጊውን የህግ ማስከበር እርምጃ” እንዲወስድ ባለስልጣኑ በዚህ ደብዳቤው አሳስቧል። 

ይህንን የባለስልጣኑን ማሳሰቢያ ተከትሎም የሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እገዳውን ያስተላለፈ ሲሆን፤ የጸጥታ አካላት “በህጉ መሰረት” በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱም ትዕዛዝ አስተላልፏል። በታገዱት መገናኛ ብዙሃን ውስጥ የሚሰሩ ሁለት ጋዜጠኞች፤ ይህ ትዕዛዝ ከተላለፈ በኋላ ስራቸውን ሙሉ ለሙሉ ማቆማቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት አብዱራዛቅ ሀሰን፤ የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እገዳውን ከማስተላለፉ በፊት “ውይይት መደረግ ነበረበት” ሲሉ ተቃውሟቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። እገዳው ከተላለፈባቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መካከል መቀመጫቸውን በለንደን፣ ሞቃዲሾ እና ሀርጌሳ ከተሞች ያደረጉ እንደሚገኙበት የሚናገሩት አብዱራዛቅ፤ መገናኛ ብዙሃኑ በሶማሌ ክልል ውስጥ መንቀሳቀስ የጀመሩት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ የክልሉ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ “በተደረገላቸው ጥሪ ነው” ብለዋል። 

ፎቶ፦ የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር

የክልሉ መንግስት እና መገናኛ ብዙሃኑ ባደረጉት ስምምነት መሰረትም፤ ለመገናኛ ብዙሃኑ “በየስድስት ወሩ የሚታደስ ፈቃድ” ሲሰጣቸው እንደቆየ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ጠቅሰዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረችው የ“ሆርን ኬብል ቲቪ” ጋዜጠኛ ኡመር መሐመድም ተመሳሳይ ሀሳብ አንስቷል። መቀመጫውን በሶማሌ ላንድ ሀርጌሳ ከተማ ያደረገው “ሆርን ኬብል ቲቪ”፤ ላለፉት አራት ዓመታት በጅግጅጋ ከተማ ቅርንጫፍ ከፍቶ ሲንቀሳቀስ የቆየው ከክልሉ መንግስት ባገኘው “ጊዜያዊ ፈቃድ” መሆኑን ኡመር ይናገራል። በዚሁ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ከመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ፈቃድ አለማግኘቱንም አክሏል።   

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ባለፈው አርብ በጻፈው ደብዳቤ፤ የሶማሌ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ከውጭ ሀገር የሚመጡ ጋዜጠኞችን ማስተናገድ ያለበት ባለስልጣኑ “በሚሰጣቸው ፈቃድ ብቻ” መሆን እንዳለበት አሳስቦ ነበር። በ2013 ዓ.ም የወጣው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ፤ ከውጭ ሀገር ለሚመጡም እና ተቀማጭነታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ለሆኑ የውጭ ሀገር መገናኛ ብዙሃን እና የዜና ወኪሎችን የመመዝገብ ስልጣን ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን እንደሆነ ይደነግጋል። 

በሶማሌ ክልል የዘገባ ስራ እንዳያከናውኑ እገዳ የተላለፈባቸው መገናኛ ብዙሃን፤ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ፈቃድ የሌላቸው መሆኑን የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንትም ይቀበላሉ። ሆኖም በክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ባለፈው ቅዳሜ የተላለፈው ውሳኔ፤ ከፈቃድ ጋር የተገናኘ ሳይሆን “መገናኛ ብዙሃኑ ከሚሰሩት ዘገባ ጋር የተያያዘ ነው” የሚል እምነት እንዳላቸው አብዱራዛቅ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ስለእገዳው ጥያቄ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ፤ እርምጃው የተወሰደው የመገናኛ ብዙሃኑን “ወደ ህጋዊ መስመር ለማስገባት” መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል፡፡ ባለስልጣኑ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ከክልሉ መንግስት ጋር ንግግር ካደረገ በኋላ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ መገናኛ ብዙሃኑ ፈቃድ የሌላቸው በመሆናቸው ተጠያቂነትን ማስፈን አለመቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃኑ “ከክልሉ ፈቃድ አግኝተው” ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር የቀረበውን ገለጻም አቶ መሐመድ አይሰማሙበትም፡፡ ክልሎች ለየትኛውም የመገናኛ ብዙሃን ፈቃድ የመስጠት ስልጣን እንደሌላቸው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ መገናኛ ብዙሃኑ በክልሉ ለመንቀሳቀስ ከባለስልጣኑ “የስራ ፈቃድ” እንደሚያስፈልጋቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ “[መገናኛ ብዙሃኑ] በጥሩ ሁኔታ ሲሰሩ ከነበረ የክልሉ መንግስት የድጋፍ ደብዳቤ ይጻፍላቸው፡፡ የስራ ፈቃድ (operation license) ከእኛ ይወስዳሉ። ለጋዜጠኞቻቸው ደግሞ የውጭ ሚዲያ ፈቃድ ባጅ ይሰጣቸዋል፡፡ በዚያ መሰረት ጥፋት ሲያጠፉ ይጠየቃሉ” ሲሉ የቀጣዩን ሂደት አካሄድ አቶ መሐመድ አስረድተዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እና መረጃ ለማግኘት ለሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብታደርግም፤ ዘገባው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አላገኘችም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሏል]