ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ የአራት ሀገራት መሪዎች፤ በአልሻባብ ጉዳይ ነገ ሊወያዩ ነው 

የሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ መሪዎች በአልሻባብ ጉዳይ ላይ በነገው ዕለት ሊወያዩ ነው። የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ መሐሙድ በሚመሩት ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደሚገኙ የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስትር ዳውድ አዌይስ ጃማ ተናግረዋል። 

የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ከሶማሊያ ድንበር የሚጋሩ አራት ሀገራት መሪዎች ነገ ረቡዕ ጥር 24፤ 2015 እንደሚገናኙ ይፋ ያደረጉት ዛሬ በሞቃዲሾ በሰጡት መግለጫ ነው። ሆኖም ሚኒስትሩ ስብሰባው የሚካሄድበትን ቦታ ከመግለጽ ተቆጥበዋል። “አሁን ያለው የሶማሊያ የጸጥታ ሁኔታ ሶማሊያን ብቻ ሳይሆን ጎረቤት ሀገራትንም ስለሚጎዳ ይህ ስብሰባ ወሳኝ ነው” ሲሉ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በዛሬው መግለጫቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ የሚሳተፉበት የነገው ስብሰባ “ታሪካዊ” እንደሚሆንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የነገው ስብሰባ “ለቀጠናው መረጋጋት ብቻ ሳይሆን፤ በሽብር እና ሽብርተኞች ላይ ለሚደረግ ዓለም አቀፍ ዘመቻ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ብለዋል ዳውድ አዌይስ ጃማ። የአራቱ ሀገራት መሪዎች ከነገው ውይይታቸው በኋላ “የቀጠናውን ፍላጎት የሚያስጠብቅ የጋራ መግለጫ ያወጣሉ” ተብሎ እንደሚጠብቅም የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስትር ጠቁመዋል። 

የነገው የመሪዎቹ ስብሰባ፤ የአራቱ ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ ልዑካን በዛሬው ዕለት ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ የሚካሄድ ነው። የኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና የጅቡቲ ወታደራዊ ልዑካን የተሳተፉበት የዛሬው ስብሰባ ዋነኛ አጀንዳ፤ ሶማሊያ በአልሻባብ ላይ ስለምታካሄደው ዘመቻ “መወያየት እና የጋራ አቋም መያዝ” እንደነበር ዳውድ አዌይስ ጃማ ገልጸዋል። 

የነገውን ስብሰባ የሚመሩት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የጎሳ ሚሊሺያዎችን በማስተባበር በአልሻባብ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ የከፈቱት፤ ባለፈው ግንቦት ወር በሀገሪቱ የተካሄደውን ምርጫ አሸንፈው ስልጣኑን በተቆጣጠሩ በጥቂት ጊዜያት ልዩነት ነው። በአልሻባብ ላይ በተጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ “በርካታ መሻሻሎች” መኖሩን የጠቀሱት የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስትር፤ ሶማሊያ ለመረጋጋት በምታደርገው ጥረት ሶስቱን ጎረቤት ሀገራት ማሳተፍ “አስፈላጊ እንደሆነ” የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ መሐሙድ መንግስት መረዳቱን አስታውቀዋል።

ላለፉት 16 ገደማ ዓመታት የሶማሊያን ማዕከላዊ መንግስት የሚወጋው አልሸባብ፤ ሞቃዲሾን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ተከታታይ ጥቃቶች ሲፈጽም ቆይቷል። የአልሸባብ ታጣቂዎች በሶማሊያ ሳይወሰኑ የኢትዮጵያን ድንበር በመሻገር ባለፈው ዓመት ሐምሌ እና ነሐሴ ወራት በሶማሌ ክልል የጥቃት ሙከራዎችን ማድረጋቸውን የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የመከላከያ ሰራዊት የጦር አዛዦች ማስታወቃቸው ይታወሳል። 

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመተባበር ለእነዚህ የጥቃት ሙከራዎች በሰጡት አጸፋ፤ በርካታ የአልሻባብ ታጣቂዎች መደምሰሳቸው እና በቁጥጥር ስር መዋላቸው በወቅቱ ተገልጾ ነበር። ከእነዚህ የጥቃት ሙከራዎች አንድ ወር ገደማ በኋላ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ መሐሙድ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ተነጋግረዋል። ሐሰን ሼይክ መሐሙድ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበረው፤ ኤርትራ እና ግብጽን ጨምሮ በስድስት ሀገራት ተመሳሳይ ይፋዊ ጉብኘት ካካሄዱ በኋላ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)