በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽንን “የ39.8 ትሪሊዮን ብር ባለ እዳ የሚያደርግ ውል ፈርመዋል” የተባሉ የስራ ኃላፊዎች ላይ “እርምጃ” እንዲወሰድ፤ በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። ኮርፖሬሽኑን በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ፤ ዛሬ በተካሄደ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ቢደረግላቸውም አለመገኘታቸው ቁጣን ቀስቅሷል።
የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ የዛሬውን ስብሰባ የጠራው፤ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የሶስት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ውይይት ለማድረግ ነበር። ለውይይቱ መነሻ የተደረገው የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት፤ በመጀመሪያ ለቋሚ ኮሚቴው ቀርቦ የነበረው ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ነበር።
ይህ የኦዲት ሪፖርት፤ ኮርፖሬሽኑ ከሰባት ዓመታት በፊት በገባው ውል መሰረት ግዴታውን መወጣት ባለመቻሉ ለከፍተኛ ቅጣት መዳረጉን ያትታል። ኮርፖሬሽኑ በግንቦት 2008 ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር የተፈራረመው ይህ ውል፤ የአዳማ አዋሽ መንገድን ላይ ከፍተኛ ጥገና ለማድረግ እና ለ10 ዓመት ለማስተዳደር የተስማማበት ነበር። ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ በገባው የውል ስምምነት መሰረት ግዴታውን ባለመወጣቱ፤ በመንገዱ ጉዳት ልክ በየወሩ በትሪሊዮን የሚቆጠር ክፍያ መጠየቁን የኦዲት ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት፤ ኮርፖሬሽኑ የተጠየቀው 39.8 ትሪሊዮን ብር ክፍያ ከተቋቋመበት ካፒታል በላይ መሆኑንም በሪፖርቱ ጠቅሷል። ከሰባት ዓመታት በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣ ደንብ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን፤ 20 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል አለው። ከዘጠኝ ወር በፊት ለፓርላማ የቀረበው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት፤ ኮርፖሬሽኑ ከዚህ እዳ ለመውጣት ማድረግ የሚገባው ምክረ ሃሳብን ጭምር ያካተተ ነበር።
ኮርፖሬሽኑ “የመጀመሪያው ውል ላይ ተገቢ የሆነ ማሻሻያ ውል ሊዋዋል፤ ወይንም ውሉን ማፍረስ ይጠበቅበታል” ሲል የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በወቅቱ ያቀረበው ምክረ ሃሳብ፤ በተቋሙ እስካሁን ተፈጻሚ አለመሆኑ ከፓርላማ ቋሚ ኮሚቴው አባላት ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች አስነስቷል። በፓርላማ የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ ውሉ “ከውጭ ኩባንያ ጋር የተደረገ ቢሆን ኖሮ ሀገርን በእዳ አሽጦ ነበር” ሲሉ የጉዳዩን ክብደት አስረድተዋል።
የኮርፖሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች፤ ውሉን እስከ ግንቦት 30፤ 2014 ዓ.ም “ለማስተካከል” ቃል ገብተው እንደነበር ያስታወሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ “ውሉ እንዳይሻሻል ያደረገው ነገር ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ለሰንዝረዋል። “39 ትሪሊዮን ብር ቅጣት የሚያስከፍል የኮንትራት ውል ስምምነት በምን መንገድ ልትፈርሙ ቻላችሁ?” ሲሉም ተጨማሪ ጥያቄ ለኃላፊዎች አቅርበዋል።
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት፤ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አመንቴ ዳዲ ናቸው። አቶ አመንቴ “ውሉ ላይ ችግር ያለበት መሆኑ በመጀመሪያም ይታወቃል። ግን በሂደት እያየን እናስተካክላለን በሚል ዝም ብሎ የተዘነጋ እና የቆየ ሆኖ ነው” ሲሉ መልሰዋል። “ውሉ መሻሻል እንዳለበት ጥያቄው ቀርቦ፤ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር እየታየ ነው” ሲሉም አክለዋል።
ውሉ ኮርፖሬሽኑ ከመቋቋሙ በፊት የተፈረመ መሆኑን የጠቀሱት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ አያሌው፤ ከስራ ባልደረባቸው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ምላሽ ሰጥተዋል። አቶ ዮናስ “ለኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ውሉ እንዲሻሻልን ደብዳቤ ጽፈናል። ከውል እንደሚያወጡልን በቃል ተነጋግረናል” ሲሉ ውሉን በተመለከተ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል። ጉዳዩ አሁን የተያዘው በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ስለሆነ፤ ተቋሙ ለችግሩ “ቶሎ እልባት” እንዲሰጥ ቋሚ ኮሚቴው አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ውሉን ለማሻሻል ቃል መግባቱን አቶ ዮናስ ቢገልጹም፤ የሚመሩት ተቋም ግን ከትችት አልዳነም። በዛሬው ውይይት ላይ የተገኙት የቋሚ ኮሚቴው አባላት ኮርፖሬሽኑ “አጥጋቢ ምላሽ አልሰጠንም” ሲሉ ተደምጠዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያንም፤ “ያልተገባ የውል ስምምነት በመውሰድ ኮርፖሬሽኑን ለዕዳ በዳረጉ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ ተወስዶ ሪፖርቱ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲቀርብልን፤ የትም ይሂዱ ተገቢውን የሆነ ቅጣት ተቀጥተው ሪፖርት እንዲቀርብልን እንፈልጋለን” ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው፤ የኮርፖሬሽኑ “የኮንትራት አስተዳደር፤ የገቡት ውል እና የፈረሙት ውል የራሱ የሆነ ሰፊ ክፍተት አለበት” ብለዋል። ዋና ኦዲተሯ አክለውም “የጠፋ ገንዘብ የለም። የተከፈለ ገንዘብ የለም። ማሳየት የፈለግነው ግን ያለውን ግዴለሽነት ነው። እንዲማሩበት እንፈልጋለን” ሲሉ 39.8 ትሪሊዮን ብር ዕዳ ያመጣው የውል ስምምነት በኦዲት ሪፖርት የተካተተበትን ምክንያት አብራርተዋል።
በዛሬው ስብሰባ ሌላው መነጋገገሪያ ሆኖ የነበረው ጉዳይ፤ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የበላይ ጠባቂ የሆነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ በውይይቱ ላይ አለመገኘት ነው። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አብዱራህማን ዒድ በዛሬው ስብሰባ እንዲገኙ በስልክ እና ደብዳቤ ጥሪ ተደርጎላቸው እንደነበር በውይይቱ መግቢያ ላይ የተናገሩት አቶ ክርስቲያን፤ ሆኖም ስራ አስፈጻሚው “የምክር ቤቱን ጥሪ በመናቅ” አለመገኘታቸውን ገልጸዋል።
የዋና ስራ አስፈጻሚው አለመገኘት “የምክር ቤቱን ግርማ እና ሞገስ ጭምር ያዋረደ ነው” ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ድርጊቱን ጠንከር ባሉ ቃላት ተችተዋል። ምክር ቤቱ የአስፈጻሚ አካላትን ማብራሪያ እንዲሰጡ የመጥራት ስልጣን እንዳለው ያስታወሱት አቶ ክርስቲያን፤ “ተጠያቂነት ሊሰፍን እንደሚገባ” አሳስበዋል።
አቶ አብዱራህማን ዒድ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተሾሙት፤ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ጥር 17፤ 2015 ነበር። አቶ አብዱራህማን ሹመቱን ያገኙት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆነው የተሾሙትን ማሞ ምህረቱን በመተካት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)