በሃሚድ አወል
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ለገባችበት “የድንበር ይገባኛል” ውዝግብ፤ የድንበር ኮሚሽን ለማቋቋም የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሀገሪቱ ከጎረቤቶቿ ጋር ያለባትን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት፤ የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በመቋቋም ላይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ያስታወቀው፤ የመስሪያ ቤቱ የስድስት ወር የስራ አፈጻጸም በተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተገመገመበት ወቅት ነው። የመስሪያ ቤቱን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ ረቡዕ ጥር 24፤ 2015 ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ያቀረቡት፤ በሚኒስቴሩ የዕቅድ ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተሩ አቶ አለማየሁ ሰዋገኝ ናቸው።
አቶ አለማየሁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያለፉትን ስድስት ወራት ዕቅድ በሚያዘጋጅበት ወቅት ትኩረት ያደረገው፤ በጎረቤት ሀገራት ላይ መሆኑን በዚሁ ሪፖርታቸው ጠቅሰዋል። ከድንበር ይገባኛል ጋር በተያያዘ ከሱዳን ጋር “ግጭት፣ የጦርነት ጉሰማ እና ትንኮሳዎች” እንደነበሩ ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ ባለፉት ስድስት ወራት “የድንበሩን ውዝግብ በውይይት ለመፍታት ስምምነት ላይ መደረሱን” አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም ከውዝግቡ ጋር በተያያዘ በሱዳን በኩል “ድንበሩ የእኛ ነው፤ መሬቱ የእኛ ነው፤ ያለቀ ጉዳይ ነው” የሚሉ ድምጾች ጎላ ብለው ይደመጡ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አለማየሁ፤ አሁን ግን ከዚያ በተቃራኒ በ“ሰከነ መንገድ መግባባት ላይ የሚደረስበት ሁኔታ” እንዳለ ጠቁመዋል። ለዚህም የሚረዳ “የድንበር ኮሚሽን ለማቋቋም የሚያስችል አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተከናውነዋል” ሲሉ አብራርተዋል።
የድንበር ኮሚሽን የማቋቋም ሂደቱ በሱዳን ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፤ ከጅቡቲ ጋር ላለው ድንበርም ተመሳሳዩን አካሄድ ለመከተል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አክለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዕቅድ ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተሩ የመስሪያ ቤቱን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ፤ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል።
አቶ ተስፋሁን ስመኝ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል “ከሱዳን ጋር ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል። ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን “ከሱዳን ጋር ወደ ከፋ ነገር ውስጥ ሳንገባ፣ የወጣንበት መንገድ፣ የደረስንበት ደረጃ፤ ቀሪውንም ችግር ለመፍታት የሚያስችል መሰረት [የጣለ] ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለበርካታ ዓመታት የይገባኛል ጥያቄ ሲነሳበት በቆየው የአል-ፋሽጋ አካባቢ ሳቢያ፤ እንደ አዲስ ውዝግብ ውስጥ ከገቡ ሁለት ዓመታትን አስቆጥረዋል። የውዝግቡ መንስኤ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ወታደሮች በቁጥጥራቸው ስር ይገኝ የነበረውን ስፍራ ለቅቀው ከወጡ በኋላ የሱዳን ወታደሮች በአካባቢው መስፈራቸው ነው።
ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት በአል-ፋሽጋ አካባቢ በተለያዩ ወቅቶች ውጊያዎች ሲካሄዱ እንደነበር ከስፍራው የሚወጡ ዘገባዎች ሲያመልክቱ ቆይተዋል። የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌፍተናንት ጄነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ከአንድም ሁለት ጊዜ አካባቢውን በመጎብኘት በስፍራው የሚገኘውን ጦራቸውን ማበረታታቸውም ይታወሳል። ኢትዮጵያ በበኩሏ “በአካባቢው ያለው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ሊፈታ የሚገባው በንግግር ነው” የሚለውን አቋሟን በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በኬንያ በተካሄደው የኢጋድ ስብሰባ ላይ በተገናኙበት ወቅት፤ በአገሮቻቸው መካከል የተቀሰቀሰውን ውጥረት ለመፍታት ንግግር መጀመራቸውን አስታውቀው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን ከናይሮቢው ንግግራቸው በኋላ፤ ባለፈው ጥቅምት ወር በባህርዳር ከተማ በተካሄደው 10ኛው የጣና ፎረም ጉባኤ ወቅት ተገናኝተው በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ይህ ውይይት ከተካሄደ ከሶስት ወራት በኋላ ደግሞ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጥር 18፤ 2015 ወደ ሱዳን አቅንተው ከአል-ቡርሃን ጋር ተገናኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ሳምንት በሱዳን ያደረጉት ጉብኝት፤ በሱዳን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከተካሄደ በኋላ ሲደረግ የመጀመሪያው ነው። አብይ ለመጨረሻ ጊዜ ሱዳን የጎበኙት በሀገሪቱ የተቋቋመው የሽግግር መንግስት ይመሩ የነበሩት አብደላ ሀምዶክ ስልጣን ላይ በነበሩበት በነሐሴ 2012 ነበር።
አብይ ባለፈው ሳምንት በካርቱም ከአል-ቡርሃን ካደረጉት ውይይት በኋላ ይፋ በተደረገው የሁለቱ ሀገራት የአቋም መግለጫ፤ የድንበር ጉዳይ ተነስቶ ነበር። ሁለቱ መሪዎች በአካል በተገኙበት በተነበበው የአቋም መግለጫ፤ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የታላቁ የህዳሴ ግድብ እና የድንበር ጉዳዮችን በ“ውይይት እና በጋራ መግባባት” የመፍታት አስፈላጊነትን በአጽንኦት ማንሳታቸው ተጠቅሷል።
በዛሬው የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ላለባት የድንበር ጉዳይ እልባት የሚሰጥ ጽህፈት ቤት በማቋቋም ላይ መሆኗን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ገልጸዋል። “የድንበር ጉዳይ ከአዋሳኞቻችን ከብዙዎቹ ጋር ስላለ፤ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት እያዘጋጀን ነው። የእያንዳንዱን ‘ፕሮፋይል’ በዝርዝር በማወቅ፣ በዚያ ላይ ተመስርተን፤ ቀጣዩ የድንበር ጉዳይ በዘላቂነት እንዲፈታ ለማድረግ የሚያስችል ስራ እየሰራን ነው” ሲሉ የሚመሩትን ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለሚከታተለው የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)