በሃሚድ አወል
ኢትዮጵያ “የቀይ ባህር ፎረም” ከተሰኘው የስምንት ሀገራት ስብስብ ውጭ መደረጓ፤ በተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄ አስነሳ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፤ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር አካባቢ የሚፈጠሩ አደረጃጀቶች እና ፎረሞች “ኢትዮጵያን ታሳቢ ያደረጉ” እንዲሆኑ እርሳቸው በሚመሩት መስሪያ ቤት የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል።
በሳዑዲ አረቢያ አነሳሽነት ከሶስት ዓመት በፊት የተመሰረተው “የቀይ ባህር ፎረም” የተሰኘው ስብስብ ያነጋገረው፤ ዛሬ ረቡዕ ጥር 24፤ 2015 በተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ነው። የፓርላማው የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዛሬውን ስብሰባ የጠራው፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ለመገምገም ነበር።
በዚሁ ስብስባ ላይ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር ዲማ ነገዎ፤ ኢትዮጵያ በ“ቀይ ባህር ፎረም” ለመካተት ያደረገችውን ጥረት በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። “ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ፖለቲካ ውስጥ ፍላጎት አላት። ቀረብ ብለን ስለምንገኝ ፍላጎት አለን። በፎረሙ ውስጥ አራት የኢጋድ አባል ሀገራት አሉ። ለኢትዮጵያ የታዛቢነት ቦታ እንዲኖራት በእነዚህ ሀገራት ድጋፍ ለማግኘት አልቻልንም ወይ?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።
“የቀይ ባህር ፎረም” በአባልነት ያቀፋቸው አራት የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አባል ሀገራት፤ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ናቸው። በአባይ ውሃ አጠቃቀም እና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ በምታንጸባርቀው የከረረ አቋም ከኢትዮጵያ ጋር ስትወዛገብ የቆየችው ግብጽም የእዚህ ፎረም አባል ነች። ቀሪዎቹ የፎረሙ አባል ሀገራት የመን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ዮርዳኖስ ናቸው።
“በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ የሚዋሰኑ የአረብ እና የአፍሪካ መንግስታት ምክር ቤት” በሚል ስያሜ የተመሰረተው ይህ ስብስብ፤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የአባል ሀገራቱን ትብብር እና ቅንጅት የማሻሻል ዓላማ እንዳለው ይገለጻል። “የቀይ ባህር ፎረም” ትኩረት የሚያደርግባቸው ጉዳዮች፤ ከፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ባህል፣ አካባቢ እና ደህንነት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን በምስረታው ወቅት የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።
ስብስቡ ከተመሰረተባቸው 12 ዓላማዎች አንዱ፤ በቀጠናው የሚከሰቱ ሽብርተኝነት፣ የባህር ላይ ውንብድና እና ኮንትሮባንድን መከላከል ነው። በአባል ሀገራት የሚዘዋወሩ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀለኞችን እና ህገ-ወጥ ስደትን መከላከልም ከ“ቀይ ባህር ፎረም” ዓላማዎች ይጠቀሳል። በስብስቡ በተካተቱ ሀገራት ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ማስተዋወቅ ሌላኛው ዓላማው የሆነው “የቀይ ባህር ፎረም”፤ በቀጠናው የሸቀጦች፣ አገልግሎቶች እና የገንዘብ እንቅስቃሴን እንዲሁም የባህር ላይ ንግድን የማሻሻል ትልም አለው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶ/ር ዮናስ አሽኔ፤ “የቀይ ባህር ፎረም” በግልጽ ከሚጠቀሱት ዓላማዎች ባለፈ የዓለም “ጂኦ ፖለቲካ” ፉክክር ነጻብራቅ ነው ይላሉ። “ ‘ጂኦ ፖለቲካው’ የቀዝቃዛው ጦርነት ተመልሶ የመምጣት አይነት አዝማሚያዎች እና ሁኔታዎች ይታዩበታል። በዚህ ውስጥ ነው የቀይ ባህር ተጽዕኖ ውስጥ የወደቀው። ለዚህ ነው ከሌሎች ሀገራት መጥተው እዚህ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚሞክሩት” ሲሉ የስብስቡን ምንነት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።
“ነገሩ ዝም ብሎ ውሃውን በዘላቂነት ለዓለም ሀብት በጋራ ለመጠቀም ሳይሆን የአፍሪካም፣ የመካከለኛው ምስራቅም፣ የዓለምም ጂኦ ፖለቲካዊ ፉክክር ውጤት ነው” ሲሉ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ያክላሉ። “ኃይላቸውን ወደ ሆነ ቦታ የማስፈንጠር አቅም ያላቸው በሙሉ ወደዚህ ያስፈነጥራሉ” ሲሉ የቀይ ባህርን ቁልፍ ቦታነት የሚናገሩት ዶ/ር ዮናስ፤ “ፎረሙ ሆን ብሎ ከአካባቢው በትንሽ ኪሎ ሜትሮች ርቀት የምትገኘውን ኢትዮጵያ ያገለለ ነው” ሲሉ ይተቻሉ።
ዶ/ር ዮናስ የኢትዮጵያን ከስብስቡ መገለል የሚኖረውን ተጽዕኖ ሲያስረዱ፤ “ጅቡቲ ማለት የኢትዮጵያ ጉሮሮ ናት። ጅቡቲ ላይ የሆነ ነገር የሚዘጋ ሰው ቢመጣ፤ ኢትዮጵያ ድምጽ የማይኖራት ከሆነ የራሷ ብሔራዊ ጥቅም፣ ደህንነት እና ህልውና በሙሉ አደጋ ላይ ይወድቃል” ይላሉ። ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸው አብዛኛዎቹ ሸቀጦች፤ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት በጅቡቲ በኩል ነው።
ኢትዮጵያ ከዚህ ስብስብ ውጭ እንድትሆን ከመደረጓ ጀርባ የግብጽ እጅ እንዳለበት ዶ/ር ዮናስ ይናገራሉ። “ግብጽ ኢትዮጵያ እንድትገባ አትፈልግም። ባለማስገባት ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ትፈልጋለች” የሚሉት የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ፤ “ነገሩን ከኢትዮጵያ በተቃራኒ የመስራት ነገር አለ” ሲሉ በሂደቱ የነበረውን አካሄድ ያስረዳሉ።
በዛሬው የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ “የቀይ ባህር ፎረም”ን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ፤ ስብስቡ “ኢትዮጵያን ያገለለ ነው” ሲሉ ወቅሰዋል። “ኢትዮጵያ በፎረሙ ውስጥ ሊኖራት የሚገባውን ሚና በግልጽ ጥያቄ አቅርበናል። ኢትዮጵያን እውቅና ያልሰጠ እና ያላሳተፈ እንዲህ አይነት ፎረም፤ ዘላቂነትም፣ ጥቅምም እንደማይኖረው ሊታይ እንደሚገባው ስራ እየሰራን ነው” ሲሉም ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል።
“በኢጋድ በኩል በሚሰሩ ስራዎች የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አሉ” ያሉት አቶ ደመቀ፤ “ወደፊት ማንኛውም ፎረም እና አደረጃጀት፤ በዚህ ቀጠና ውስጥ [ሲመሰረት] ኢትዮጵያን ታሳቢ ያደረገ፤ ኢትዮጵያ ግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን ለማድረግ ስራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።
አቶ ደመቀ የኢትዮጵያን በስብስቡ አለመካተት አንስተው ወቀሳ ሲሰነዝሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት በጀርመን በተካሄደው 58ኛው የሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ ላይም ይኼንኑ ጉዳይ አንስተውት ነበር። ትኩረቱን በዓለም የጸጥታ ጉዳዮች ላይ አድርጎ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ አቶ ደመቀ ባደረጉት ንግግር፤ “ኢትዮጵያ ለዚህ ቀጠና ሰላም እና ጸጥታ መጠናከር የምታበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ከቀይ ባህር መድረክ መገለሏ ስህተት ነው” ማለታቸውን የሚመሩት መስሪያ ቤት በወቅቱ አስታውቆ ነበር።
“የቀይ ባህር ፎረም” አባል ሀገር የሆነችው እና ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ያደሰችው የኤርትራ ጉዳይም በዛሬው የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተነስቶ ነበር። የፓርላማ አባላቱ ከኤርትራ ጋር ስላለው ግንኙነት ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበውላቸዋል። የቋሚ ኮሚቴው ስብሳቢ ዶ/ር ዲማ “ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት ምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው? የአሰብ ወደብን ለመጠቀም እየተደረገ ያለው ጥረት ምንድን ነው” የሚሉ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል።
ሁለቱ ሀገራት ግንኙታቸውን በይፋ እንደገና ከጀመሩ በኋላ “ብዙ እድገት እና ለውጥ ሳያመጣ ቆይቷል” የሚሉ አስተያየቶች ሲሰጡ እንደነበር አቶ ደመቀ አስታውሰዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ “ከዚህ የባሰ ችግር አጋጥሞን ስለነበር ያንን ስጋት የመከላከል እና መልክ የማስያዝ ስራ ዋናው ስለነበር ነው” ብለዋል።
“ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ ሌሎቹ የትብብር ግንኙነት ማዕቀፎች ብዙ ርቀት ሳንወስደው፤ የደረሰው የቀጠናው ግጭት ይታወቃል። ተጠምደን የቆየነው በዚያ ነው” ሲሉ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ፈር ያልያዘበትን ምክንያት አብራርተዋል። አቶ ደመቀ ስለኤርትራ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት የሰጡትን ምላሽ ያሳረጉት፤ “አሁን በሚፈጠረው አዎንታዊ ሁኔታ ግንኙነታችን በኢኮኖሚ [እና] በልዩ ልዩ መልክ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሆን እናደርጋለን ብለን እናምናለን” በሚል ገለጻ ነው።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የአሰብ ወደብን ለመጠቀም እየተደረገ ስላለው ጥረት ለተነሳው ጥያቄም አጭር ምላሽ ሰጥተዋል። “አብዛኛው የወደብ እንቅስቃሴ ጅቡቲ ጋር ነው ያለው” ያሉት አቶ ደመቀ፤ የወደብ አጠቃቀምን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ከኤርትራ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ወደብን ጨምሮ የጋራ የኢኮኖሚ እና የደህንነት ትስስር ሊኖረው እንደሚገባም ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)