የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማትን “በተለየ ሁኔታ” ኢላማ ያደረጉ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን ኢንሳ አስታወቀ 

በአማኑኤል ይልቃል

በኢትዮጵያ ባሉ ተቋማት ላይ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች፤ የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማትን “በተለየ ሁኔታ” ኢላማ ማድረጋቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) አስታወቀ። በግማሽ  ዓመቱ ውስጥ በተቋማት ላይ ከተቃጡት የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ፤ 41 በመቶው “እጅግ በጣም ከፍተኛ” የሆነ ጉዳት የማድረስ አቅም የነበራቸው መሆኑን ተቋሙ ገልጿል።

ይህ የተገለጸው፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸምን አስመልክቶ ዛሬ ሐሙስ ጥር 25፣ 2015 በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ፤ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 2,145 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን አስታውቀዋል። በመንግስት እና የግል ተቋማት ላይ ከተሞከሩ ከእነዚህ የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ 91.5 በመቶውን ማክሸፍ መቻሉን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።

ከሳይበር ጥቃቶቹ መካከል 96 ያህሉ “ስኬታማ” መሆናቸውን በመግለጫቸው የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ እርሳቸው የሚመሩት ተቋም ለእነዚህ ጥቃቶች “ምላሽ የመስጠት ስራ” እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። በእነዚህ ጥቃቶች “የደረሰው ጥፋት መጠን” ምን ያህል እንደሆነ የሚታወቀው፤ ተቋማቸው  የሚሰጠው ምላሽ ሲጠናቀቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የተደረጉ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር “ዝቅተኛ” መሆኑ በዛሬው መግለጫ ተመላክቷል። በ2014 ዓ.ም. የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ብዛት 3,036 ነበር። ዘንድሮ በተመሳሳይ ወቅት የተፈጸሙ ጥቃቶች ከአምናው ጋር ሲነጻጸሩ በ29.3 በመቶ ያነሱ መሆናቸው ተገልጿል። 

የጥቃት ሙከራዎች ቁጥር መቀነሱ “በመልካም ሊታይ የሚችል” ቢሆንም፤ የተሰነዘሩት ጥቃቶች “ግዙፍ የሆነ ጉዳት” የማምጣት አዝማሚያ ያላቸው መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ በአጽንኦት አንስተዋል። ጥቃቶቹ ኢላማ ያደረጓቸው፤ “እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የሀገር ሀብት እና ህልውና ወይም ሉዐላዊነት የሚያስጠብቁ ተቋማት” መሆናቸው የጉዳቱን መጠን ከፍ የሚያደርገው መሆኑንም አብራርተዋል።

በዚህ ዓመት በታዩት ጥቃቶች፤ የሀገሪቱ የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት “በተለየ ሁኔታ” ትኩረት እንደተደረገባቸው ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ሀገሪቱ “ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ሌሎች ውጥንቅጦች ውስጥ ገብታ በነበረችባቸው ጊዜያት” እንኳ እነዚህ ተቋማት በዚህ መጠን ኢላማ እንዳልተደረጉ አስረድተዋል። 

በሀገሪቱ የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት ላይ የተቃጡት ሙከራዎችን “ውስብስብ” ሲሉ የገለጿቸው አቶ ሰለሞን፤ ጥቃቶቹ “ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ” ፍላጎቶችን ያነገቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የሳይበር ጥቃት አድራሾች የጸጥታ እና የደህንነት ተቋማትን ኢላማ ያደረጉት፤ “ከፍተኛ ትርፍ” ስለሚያስገኝላቸው እንደሆነ የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።  

ባለፈው መንፈቅ ዓመት፤ ከጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት ባሻገር ቁልፍ የመንግስት ተቋማት፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የግል ተቋማት እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይበር ጥቃት ሙከራ እንደተደረገባቸው በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። በስድስቱ ወራት ውስጥ ከተሰነዘሩት የጥቃት ሙከራዎች ውስጥ 41 በመቶው፤ የክብደት ደረጃቸው “እጅግ በጣም ከፍተኛ” እንደሆነ ተነግሯል። በግማሽ ዓመቱ የተደረጉት የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች 15 ቢሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ እንደነበሩም ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)