በወልቂጤ ከተማ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ፤ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ ሰባት ሰዎች መቁሰላቸው ተገለጸ   

በሃሚድ አወል

በደቡብ ክልል፤ ጉራጌ ዞን፤ ወልቂጤ ከተማ ያለን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር አስመልክቶ ቅሬታቸውን ለማቅረብ በወጡ ሰልፈኞች ላይ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ፤ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ ቢያንስ ሰባት ሰዎች መቁሰላቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች እና የጤና ባለሙያ ተናገሩ። የወልቂጤ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሟቾቹን እና የቁስለኞቹን ብዛት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው ክስተት መነሻ፤ በወልቂጤ ከተማ በሚገኘው አዲስ ክፍለ ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላለፉት ሶስት ወራት መቋረጡ እንደሆነ የከተማይቱ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ለዕለታዊ ፍጆታ የሚያስፈልጋቸውን የመጠጥ ውሃ ከመኖሪያቸው 14 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ከሚገኙ አካባቢዎች ሲያጓጉዙ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል። 

ነዋሪዎቹ በተመሳሳይ መልኩ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 8 ጠዋት ውሃ ለመቅዳት በተለምዶ “ዱባይ ካፌ አደባባይ” ተብሎ ወደሚጠራው አካባቢ ቢጓዙም፤ በስፍራው የውሃ አገልግሎት በመቋረጡ ተቃውሟቸውን ለማሰማት አደባባይ መውጣታቸውን ሶስት የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ነዋሪዎቹ የጉራጌ ዞን አስተዳደር፣ የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት እና የወልቂጤ ከተማ ውሃ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ወደሚገኙበት ስፍራ በማምራት፤ ተቃውሟቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ሲገልጹ መቆየታቸውን አክለዋል።

በአካባቢው ጸጥታ ለማስከበር የተሰማሩት የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት የተቃውሞ ሰልፉን ለመበተን የአስለቃሽ ጭስ በመተኮሳቸው፤ ሰልፈኞቹ ድንጋይ ወደ መወርወር መግባታቸውን የዓይን እማኞቹ ገልጸዋል። ይህን ተከትሎም የጸጥታ ኃይሎች  በከፈቱት ተኩስ የቆሰሉ ዘጠኝ ሰልፈኞችን ወደ ወልቂጤ ጤና ጣቢያ መውሰዳቸውን አብራርተዋል።  

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በወልቂጤ ጤና ጣቢያ የሚሰሩ አንድ የጤና ባለሙያ፤ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ጤና ጣቢያው ከመጡ ዘጠኝ ሰዎች መካከል ሁለቱ በህክምና ላይ እንዳሉ ህይወታቸው ማለፉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ህክምና እየተደረገላቸው ከሚገኙ ቁስለኞች ውስጥ የተወሰኑት ጀርባቸው እና እግራቸው ላይ በጥይት የተመቱ መሆኑንም አስረድተዋል። 

የወልቂጤ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ዋና አዛዥ ሳጅን ስንታየሁ አበበ፤ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን እና ሰባት ሰዎች መቁሰላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ሆኖም ሳጅን ስንታየሁ የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ የወሰዱት ከሰልፈኞች ድንጋይ መወርወር ከተጀመረ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል። በጸጥታ ኃይሎች እና በሰልፈኞች መካከል ግጭት ከመቀስቀሱ አስቀድሞ ግን ውይይት ተጀምሮ እንደነበር የሚናገሩት የፖሊስ አዛዡ፤ ከዚያ በኋላ የነበረውን ክስተት እንደሚከተለው አብራርተዋል። 

“ድንጋይ መወርወር ተጀመረ። እኛ፤ ጸጥታ ኃይሉንም፣ ልዩ ኃይሉንም ብንለምንም፤ ከማናቸውም መሆን አልቻልንም። ከዚያ በኋላ እነሱም ‘ድንጋይ እየተወረወረብን ነው’ በሚል ተኩስ ጀመሩ። ከቆይታ በኋላ ሁለት ሰው ሞተ ሰባት ሰው ደግሞ ቆሰለ” ሲሉ ዋና ሳጅን ዛሬ ጠዋት የተከሰተውን ሁኔታ አስረድተዋል። በድንጋይ ውረወራው ከጸጥታ ኃይሎች ጉዳት የደረሰበት ሰው አለመኖሩንም ጨምረው ገልጸዋል። 

ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው የወልቂጤ ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር፤ ትላንት ማክሰኞ የካቲት 7፤ 2015 በተካሄደው የከተማይቱ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ተነስቶ ነበር። በዚሁ ስብሰባ ላይ የወልቂጤ ከተማ የውሃ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል ጃፋር፤ የመጠጥ ውሃ የከተማይቱ “ዋነኛ ችግር” መሆኑን መናገራቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የከተማዋ የምክር ቤት አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ይህንኑ ችግር ለመፍታት በ46 ሚሊዮን ብር ሁለት የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ባለፈው ዓመት አስጀምሮ ነበር። ባለፈው ጥቅምት ወር የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም 95 በመቶ መድረሱን የከተማይቱ የውሃ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ቢያስታውቅም፤ እስካሁን ድረስ ግን ፕሮጀክቶቹ አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸውን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።  

በጉራጌ ዞን ከተነሳው የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ፤ የወልቂጤ ከተማን ጨምሮ ዞኑ ላለፉት ሶስት ወራት እየተመራ የሚገኘው በኮማንድ ፖስት አደረጃጀት ነው። ዞኑ በኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆን የተደረገው፤ በአካባቢው የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር “በመደበኛ አሰራር ለማስተዳደር” ባለመቻሉ መሆኑን የደቡብ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ መገራቸው ይታወሳል። የጸጥታ ኃይሎች በዛሬው ዕለት በወልቂጤ ከተማ የወሰዱትን እርምጃ በተመለከተ እኩለ ቀን ገደማ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አለማየሁ፤ “ጉዳዩን እስካሁን አላጣራንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)