የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር በክልሉ መንግስት ተሰጥቶት የነበረው ፈቃድ ተሰረዘ

በአማኑኤል ይልቃል

የሶማሌ ክልል ፍትህ ቢሮ “ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ፈጽሟል” ያለውን የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር ፈቃድ ሰረዘ። የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር በበኩሉ እርምጃው “የመገናኛ ብዙሃንን ነጻነት ለማፈን የተወሰደ ነው” ሲል ውሳኔውን ነቅፏል። 

በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 24 የጋዜጠኛ ማህበራት ውስጥ አንዱ የሆነው የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር የተመሰረተው ከሶስት ዓመት ገደማ በፊት በህዳር 2012 ዓ.ም ነው። ማህበሩ የተቋቋመው፤ በክልሉ በጋዜጠኝነት ሙያ ረገድ ያለውን “አነስተኛ ልምድ ለማሳደግ” እና በጋዜጠኞች ላይ ለሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች “ድምጽ ለመሆን” በሚል ዓላማ እንደነበር መስራቾቹ ይናገራሉ።

በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 86 ጋዜጠኞችን በአባልነት ያቀፈ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ማህበር፤ ፈቃዱ የተሰረዘው ከሁለት ሳምንት በፊት ነው። የሶማሌ ክልል ፍትህ ቢሮ ለማህበሩ የሰጠውን ፈቃድ መሰረዙን ያስታወቀው፤ ለክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ጥር 23፤ 2015 በጻፈው ደብዳቤ ነው። ማህበሩ ፈቃዱ የተሰረዘበት “ተገቢ ያልሆነ ድርጊት” በመፈጸሙ መሆኑን የክልሉ ፍትህ ቢሮ በደብዳቤው አስፍሯል። 

ይህ ደብዳቤ የደረሰው የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፤ የጋዜጠኞች ማህበሩ በክልልም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ “ፈቃድ የሌለው” መሆኑን በመግለጽ ለክልሉ የጸጥታ ቢሮ እና ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ ጽፏል። የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በዚሁ ደብዳቤው፤  የጋዜጠኞች ማህበሩ “ህዝብን የሚያሳስት እና የአካባቢውን መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል የተሳሳተ መልዕክቶችን ለማሰራጨት” በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቅሶ ነበር።

የጋዜጠኞች ማህበሩን “ማህበራዊ ንቅናቄ” (social mobilization) በማደራጀት የሚወቅሰው የኮሚዩኒኬሽን ቢሮው፤ የክልሉ የጸጥታ አካላት “በህጉ መሰረት ተገቢውን እርምጃ” በማህበሩ ላይ እንዲወስዱ አሳስቧል። ፈቃዱ የተሰረዘበት የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር በክልሉ ፍትህ ቢሮ የተወሰደበትንም እርምጃም ሆነ በኮሚዩኒኬሽን ቢሮው በኩል የቀረበትን ወቀሳ አይቀበልም።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት አብዱራዛቅ ሀሰን፤ የማህበሩን ፈቃድ መሰረዝ “የመገናኛ ብዙሃንን ነጻነት ለማፈን የተወሰደ እርምጃ ነው” ሲሉ ተችተውታል። የክልሉ ፍትህ ቢሮ በማህበሩ ላይ የወሰደው እርምጃ፤ በሶማሌ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 15 መገናኛ ብዙሃን እና ወኪሎች “ከስራ እንዲታገዱ ከተላለፈው ውሳኔ ጋር የተያያዘ ነው” የሚል እምነት እንዳላቸውም የማህበሩ ፕሬዝዳንት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በአስራ አምስቱ መገናኛ ብዙሃን እና ወኪሎቻቸው ላይ የእገዳ እርምጃው የተላለፈው፤ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን “ፈቃድ ሳይኖራቸው” በጋዜጠኝነት ስራ ላይ ተሰማርተዋል በሚል ነበር። በሶማሌ ክልል የሚያከናውኑትን የዘገባ ስራ እንዲያቆሙ በክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በደብዳቤ ከታዘዙት መገናኛ ብዙሃን መካከል፤ የቢቢሲ የሶማሊኛ ቋንቋ አገልግሎት፣ ዩኒቨርሳል ቲቪ፣ ስታር ቲቪ፣ ኤም ኤም ቲቪ እና ሆርን ኬብል ቲቪ ይገኙበታል።

እግዱን አስመልክቶ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አስተያየት መስጠታቸውን ያስታወሱት አብዱራዛቅ፤ “የማህበሩ ፈቃድ የተሰረዘው የመገናኛ ብዙሃኑን መታገድ በመቃወሜ ነው” ሲሉ ይከስሳሉ። ለዚህም በማሳያነት የሚጠቅሱት የማህበሩ ፈቃድ በክልሉ ፍትህ ቢሮ የተሰረዘው፤ በመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከአንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ጋር ቃለመጠይቅ ባደረጉት ዕለት መሆኑን ነው።

“የክልሉ መንግስት በሚያደርገው ክትትል እና እስር” ምክንያት ጋዜጠኞች “መንግስትን መተቸት” አለመቻላቸውን የሚናገሩት አብዱራዛቅ፤ “የማህበሩ ፈቃድ የተሰረዘው ከሚዲያ ጋር በተያያዘ በክልሉ ውስጥ የሚፈጠሩ ነገሮች ላይ አስተያየት እንዳንሰጥ፣ ዝም የሚያስብሉበት ብቸኛው መንገድ ስለሆነ ነው” ይላሉ። የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር፤ በክልሉ ውስጥ ከጋዜጠኞች እስር እና የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ጋር በተያያዘ የነበሩ ክስተቶችን በተመለከተ ባለፉት ሶስት ዓመታት መግለጫዎችን ሲያወጣ ቆይቷል። 

በማህበሩ እነዚህ ዓመታት ውስጥ ከጋዜጠኞች ሙያዊ ስነምግባር ጋር የተያያዙ ስልጠናዎችንም አዘጋጅቷል። በስነ ምግባር የታነጹ፣ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግሉ መገናኛ ብዙሃንን የማጎልበት ዓላማ ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤትም አባል ነው። የጋዜጠኞች ማህበሩ ፍቃድ መሰረዝን በተመለከተ የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤቱ ለማጣራት ባደረገው ሙከራ፤ ማህበሩ “ምዝገባ ተደረገለት እንጂ ፈቃድ አልወሰደም” የሚል ምላሽ ማግኘቱን የተቋሙ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታምራት ኃይሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ይህን ምላሽ ለምክር ቤቱ የሰጠው የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ፤ የጋዜጠኞች ማህበሩ በማህበርነት ለመንቀሳቀስ የሚያበቃውን ፈቃድ የሚያገኘው ከፌደራል ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ባለስልጣን መሆኑን እንደገለጸላቸውም አስረድተዋል። ይህንኑ “ህጋዊ መንገድ” በመከተል፤ በአዲስ አበባ ከሚገኘው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፍቃድ ማግኘት የሚቻልበት አካሄድ ካለ እርሱን   እንዲፈጽሙ ከሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር አመራሮች ጋር መነጋገራቸውንም አክለዋል። 

የፈቃድ አሰጣጥን አስመልክቶ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ፤ በፌደራል እና በክልል የሚሰጡ የተለያዩ የፈቃድ አይነቶች እንዳሉ ገልጸዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቱ በአንድ ክልል ውስጥ ብቻ የሚንቀሳቀስ ከሆነ፤ ፈቃድ የሚያገኘው ከክልል መንግስታት መሆኑን አስረድተዋል።

በ2011 ዓ.ም በወጣው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መሰረት በፌደራል ደረጃ ፈቃድ የሚያገኙት፤ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች እንዲሁም ከአንድ በላይ በሆኑ ክልሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ናቸው። የውጭ የሲቪል ማህበራት እና በሀይማኖት ተቋማት የሚመሰረቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም እንዲሁ ከፌደራሉ ባለሰልጣን ፈቃድ የሚያገኙ መሆኑ በአዋጁ ተደንግጓል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በፌደራሉ ተቋም በሚመዘገቡበት ጊዜ፤ ፈቃዳቸውም በዚያው ወቅት ሳይነጣጠል የሚፈጸም መሆኑን አቶ ፋሲካው ገልጸዋል። የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር በፌደራል ደረጃ ፈቃድ እንዲያገኝ የማመልከት እቅድ ስለመኖሩ ጥያቄ የቀረበላቸው የማህበሩ ፕሬዝዳንት አብዱራዛቅ፤ በአሁኑ ወቅት ይህ ሀሳብ ባይኖርም ለወደፊት ግን በእቅድ መያዙን ተናግረዋል። 

የጋዜጠኞች ማህበሩን  የፈቃድ መሰረዝ በተመለከተ ከሶማሌ ክልል ፍትህ ቢሮ እንዲሁም ከክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ተጨማሪ ማብራሪያ እና መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራዎች ብናደርግም፤ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)