የደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ወራሾች “ፍቅር እስከ መቃብር”ን በተመለከተ ለኢቢሲ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አስገቡ 

በአማኑኤል ይልቃል

የ“ፍቅር እስከ መቃብር” ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ወራሾች፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) መጽሐፉን ወደ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ቀይሮ “የማስተላለፍ መብት የለውም” ሲሉ ለተቋሙ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አስገቡ። ይህ ደብዳቤ እንደደረሰው የገለጸው ኮርፖሬሽኑ፤ በጉዳዩ ላይ የተቋሙ አመራሮች ውይይት ካደረጉ በኋላ ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

በ1958 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ለንባብ የበቃው “ፍቅር እስከ መቃብር” በኢትዮጵያ ዘመናዊ የስነ ጹሁፍ ታሪክ በጉልህነት ከሚጠቀሱ ስራዎች አንዱ ነው። የመጽሐፉ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ በዚህ መጽሐፋቸው እስከ ጣሊያን ወረራ የነበረውን የባላባታዊ ስርዓት ገጽታ እና በውስጡ የነበረውን ተቃርኖ በፍቅር ታሪክ አዋዝተው ያሳዩበት ነው። 

ከ10 ጊዜያት ያህል በላይ የታተመው “ፍቅር እስከ መቃብር” ይበልጥ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅ የሆነው፤ በእውቁ ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ ተተርኮ በኢትዮጵያ ሬድዮ ከተላለፈ በኋላ ነበር። በደራሲ ሀዲስ አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ ለንባብ የበቃው ይህ የልቦለድ መጽሐፍ፤ በደርግ ዘመነ መንግስት በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት፣ በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን ደግሞ በሜጋ አሳታሚ ድርጅት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በማንኩሳ አሳታሚ ድርጅት ለገበያ ቀርቧል።

ስልሳኛ ዓመቱን ሊደፍን የተቃረበው ይህ መጽሐፍ፤ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ በተከታታይ ድራማነት ለተመልካቾች እንደሚቀርብ መነገሩ በደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ወራሾች በኩል ተቃውሞ ቀርቦበታል። ተቃውሟቸውን በደብዳቤ ለተቋሙ ያሳወቁት፤  አቶ ስዩም ሀዲስ እና ዶ/ር ፅጌሬዳ አበበ የተባሉት ወራሾች ናቸው። ወራሾቹ “በህጋዊ ወኪሎቻቸው” በኩል ባለፈው አርብ የካቲት 10፤ 2015 ለኢቢሲ በላኩት ደብዳቤ፤ የ“ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሐፍ የመብት ባለቤትነት ወደ ኮርፖሬሽኑ የተላለፈበት አግባብ የወራሾቹ “ህጋዊ እውቅና የሌለው” መሆኑን ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ ደብዳቤ እንደሚስረዳው፤ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ በህይወት በነበሩበት ወቅት “ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሐፍን “በፊልም እና ቲያትር መልክ ተሰርቶ ለገበያ እንዲቀርብ” ስምምነት ፈጽመው የነበረው “ሜጋ ማስታወቂያ ኢንተርፕራይዝ” ከተባለ ድርጅት ጋር ነው። ደራሲው ይህንን “የኮፒራይት ማስተላለፊያ ስምምነት” ውል በግንቦት 1995 ዓ.ም ከተፈራረሙ ከአምስት ወራት በኋላ ህይወታቸው አልፏል። 

ደራሲው ይህን ስምምነት ከ“ሜጋ ማስታወቂያ ኢንተርፕራይዝ” ጋር ተዋውለው የነበረ ቢሆንም፤ ድርጅቱ ከዓመታት በኋላ “ከስሞ በመዘጋቱ” በመጽሐፉ ላይ የባለቤትነት መብት ያላቸው ወራሾቻቸው እንደሆኑ በመጥቀስ ለኢቢሲ ተቃውሞ መቅረቡን የአቶ ስዩም ሀዲስ ህጋዊ ወኪል የሆኑት ወ/ሮ ማህሌት ኒጎስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እርሳቸው ይህን ቢሉም፤ ሜጋ ከስሮ ሲዘጋ “ዋልታ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት” የተሰኘው ድርጅት የመጽሐፉን የባለቤትነት መብት እንደገዛው በድርጅቱ በአመራርነት የሰሩ ግለሰብ ገልጸዋል።  

“ሜጋ ብዙ እዳ የነበረበት ከዋልታ ስለነበር፤ ዋልታ ጠቅልሎታል” ያሉት እኚሁ የቀድሞ አመራር፤ ሜጋ በመጽሐፉ እና በሌሎች ንብረቶች ላይ የነበሩት መብቶች ጭምር ወደ ዋልታ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት በዚሁ ጊዜ እንደተላለፉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል። ይህን ጉዳይ በወሬ ደረጃ “መስማታቸውን” የሚናገሩት ወ/ሮ ማህሌት፤ ሆኖም ይህንን በተመለከተ ለወራሾች የቀረበ ህጋዊ ማስረጃ እንደሌለ አስረድተዋል። 

“እኛ የምናውቀው፤ ዋልታ እንዳልገዛው እና ‘መከነ፣ ተዘጋ እንደተባለ’ ነው” የሚሉት የወራሽ ህጋዊ ወኪል፤ በዚህም ምክንያት ደራሲ ሀዲስ ከሜጋ ድርጅት ጋር የፈጸሙት ስምምነት “ወደ ሌላ አካል አልተላለፈም” ባይ ናቸው። የደራሲው ወራሾች ለኢቢሲ ባስገቡት ደብዳቤ ላይ፤ ስምምነቱ ወደ ኮርፖሬሽኑ መተላለፉ “የደራሲውን ህጋዊ ወራሾች መብት የሚጎዳ ተግባር” እንደሆነ በማንሳት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። የመጽሐፉ የባለቤትነት መብት ለኮርፖሬሽኑ የተላለፈው “የህጋዊ ወራሾች እውቅና በሌለበት እንዲሁም ፈቃድ ሳይኖር” መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዋልታ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት በአመራርነት ያገለገሉት ግለሰብ በበኩላቸው፤ ኢቢሲ የመጽሐፉን የባለቤትነት መብትን ለመግዛት ረዘም ላለ ጊዜ ድርድር ሲያደርግ መቆየቱን እንደሚያውቁ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን “ፍቅር እስከ መቃብርን” ወደ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በመቀየር ለተመልካች ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑን ያስታወቀው ባለፈው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። 

ኮርፖሬሽኑ በዚሁ ጊዜ ባሰራጨው መረጃ፤ መጽሐፉን ወደ ተከታታይ ድራማ ለመቀየር ካወዳደራቸው “ግለሰቦች” ውስጥ የፊልም ባለሙያ እና ዳይሬክተር ሰውመሆን ይስማው መመረጡን አስታውቆ ነበር። ሰውመሆን “አቦል” በተሰኘው የዲኤስቲቪ የቴሌቪዥን ቻናል የሚተላለፈውን “አደይ” ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፤ በራሱ የፊልም ፕሮዳክሽን ድርጅት አማካኝነት ለተመልካች በማቅረብ ላይ ይገኛል። 

በሲኒማቶግራፈርነት እና በዳይሬክተርነት በሰራቸው ፊልሞች በርካታ ሽልማቶችን ያገኘው ሰውመሆን፤ “ፍቅር እስከ መቃብርን” በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማነት ለመስራት ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 14፤ 2015 የስራ ውል ተፈራርሟል። በአራት ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ48 ክፍሎች ለሚቀርበው ለዚህ የቴሌቪዥን ድራማ፤ ኢቢሲ 41.4 ሚሊዮን ብር ለ“ሰውመሆን ፊልም ፕሮዳክሽን” ለመክፈል እንደተስማማ በዛሬው የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዛሬ የተፈጸመውን ስምምነት በተመለከተ በማህበራዊ ድረ ገጹ ባወጣው ዜና፤ ኢቢሲ “ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሐፍን ወደ ፊልም ወይም ድራማ ለመቀየር የሚያስችለው “የመብት ባለቤት” እንደሆነ አስታውቋል። የኢቢሲ የዋና ስራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ ሞላልኝ መለሰ፤ ኮርፖሬሽኑ የመጽሐፉን የባለቤትነት መብት ያገኘው ከዋልታ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት በግዢ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

“መጽሐፉን ወደ ፊልም የመቀየር መብት ክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ለሜጋ ሸጠዋል። የሜጋ መብት ደግሞ በህግ ለዋልታ ተላልፏል። ዋልታ የመብት ባለቤት (right holder) ስለመሆኑ ማረጋገጫ አምጥቶ፤ ከዋልታ መብቱን በህጋዊ መንገድ ገዝተን ነው ወደ ስራው እየገባን ያለነው” ሲሉ ኮርፕሬሽኑ ያለፈበትን ሂደት አብራርተዋል። 

የደራሲ ሀዲስ ወራሽ ህጋዊ ወኪል የሆኑት ወ/ሮ ማህሌት፤ ከ20 ዓመታት ገደማ በፊት ከሜጋ ጋር በተፈጸመው ውል ላይ ድርሰቱን ወደ ፊልም የመቀየር ስራው በደራሲው እውቅና የሚፈጸም እንደሚሆን መጠቀሱን በማንሳት ኢቢሲ ይህንን አለማድረጉን ይገልጻሉ። “ውሉን ቢገዙትም እንኳን በውሉ ላይ የደራሲው መብት አለ። ‘በማንኛውም መልኩ ፊልሙን ከደራሲው ውጪ ሲሰራ እንዲያማክር እና እንዲያሳውቅ’ የሚል አለ። ስራውን ሊጀምሩ ሲሉ ‘ደራሲው ማወቅ አለበት’ የሚል አለው” ሲሉ በውሉ ላይ ያለው ይህ ሃሳብ ለወራሾችም የሚሰራ መሆኑን በማንሳት ይሞግታሉ። 

ከዚህም በተጨማሪ ውሉ ከተፈጸመ በኋላ ላለፉት 20 ዓመታት ገደማ ወደ ፊልምነት ባለመቀየሩ፤ ወራሾች በጊዜው በውል የተሰጠውን መብት የማንሳት ህጋዊ ድጋፍ እንዳላቸው ያስረዳሉ። ወ/ሮ ማህሌት ለዚህ መከራከሪያቸው በአስረጂነት የሚጠቅሱት፤ በ1996 ዓ.ም በወጣው የቅጅና ተዛመጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ላይ “ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ስላለመጠቀም” የተደነገገበትን አንቀጽ ነው።

የአዋጁ ይህ አንቀጽ “አንድ የኢኮኖሚያዊ መብት የተላለፈለት ወይም የብቸኝነት ፈቃድ ያገኘ ሰው”፤ የተሰጠውን መብት “ሙሉ ለሙሉ ወይም በበቂ ሁኔታ ካልተጠቀመበት” ፈቃዱን ሊሻር እንደሚችል ደንግጓል። መብቱን የሰጠው አካል “ህጋዊ ጥቅም የተጎዳ” በሚሆንበት ጊዜ “የስራ አመንጪው” “የመብቱን መተላለፍ ወይም ፈቃዱን ሊሽር” እንደሚችልም በዚህ አዋጅ ላይ ሰፍሯል።

ሁለቱ የደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ወራሾች ለኢቢሲ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ግን “የመብት መሻር ጉዳይ” አልተጠቀሰም። ይልቁንም “ተገቢውን ስምምነት በማድረግ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ” እንዲፈታ ቀነ ገደብ ያስቀመጠ ነው። ኮርፖሬሽኑ ለደብዳቤያቸው በሰባት ቀናት ምላሽ እንዲሰጣቸው ያሳሰቡት ወራሾቹ፤ ሆኖም ተቋም ይህን ሳያደርግ ወደ ስራ የሚገባ ከሆነ ጉዳዩን “ወደ ፍትህ አካላት” ለመውሰድ እንደሚገደዱ አስታውቀዋል። ተቋሙ ለሚደርስባቸው “ጉዳት እና ወጪ” ኪሳራን ጨምሮ ተጠያቂ እንደሚሆንም አስጠንቅቀዋል።  

ወራሾቹ ለኢቢሲ የላኩት ደብዳቤ ለኮርፖሬሽኑ የደረሰው ትላንት ሰኞ የካቲት 13፤ 2015 መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ በጉዳዩ ላይ በኮርፖሬሽኑ አስተዳደር ደረጃ ግን ውይይት እንዳልተካሄደበት ተናግረዋል። ከወራሾቹ ለተሰጠው “ህጋዊ ማስጠንቀቂያ” ምላሽ መስጠት የሚቻለው በአመራሮች ደረጃ ውይይት ከተደረገበት በኋላ እንደሚሆን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)