የኢትዮጵያ አየር መንገድ “በውጪ ምንዛሪ እጥረት” ምክንያት ከናይጄሪያ ማውጣት የተቸገረውን ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንዲፈቀድለት ጥያቄ አቀረበ። ጥያቄውን ለናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሙሐመድ ቡሃሪ ያቀረቡት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ሊቀመንበር አቶ ግርማ ዋቄ ናቸው።
አቶ ግርማ ከቡሃሪ ጋር የተገናኙት፤ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአዲስ አበባ በተካሄደው 36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ህብረት ጉባኤ ለመሳተፍ በመጡበት ወቅት ነው። ከትላንት በስቲያ እሁድ በተካሄደው በዚህ ውይይት ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንዲሁም የአየር መንገዱ የስትራቴጂክ ዕቅድ እና አሊያንስ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ዳንኤል አበበ መገኘታቸውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከናይጄሪያ መንግስት ጋር በመሰረተው ሽርክና፤ ከ20 ዓመታት ገደማ በፊት የተዘጋውን የሀገሪቱን አየር መንገድ ወደ ስራ ለመመለስ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ቡሃሪ ከሰባት ዓመታት ገደማ በፊት ወደ ስልጣን ሲመጡ ለመፈጸም ቃል ከገቡባቸው ጉዳዮች ውስጥ፤ “ናይጄሪያ ኤይርዌይስ” የተሰኘውን የሀገሪቱን አየር መንገድ መልሶ ማቋቋም ይገኝበታል።
በዚህም መሰረት የናይጄሪያ መንግስት ያወጣውን ዓለም አቀፍ ጨረታ ያሸነፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ 49 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ተገልጾ ነበር። ዳግም ስራ በሚጀምረው አየር መንገድ፤ የናይጄሪያ ፌደራል መንግስት የሚኖረው ድርሻ 5 በመቶ ብቻ ይሆናል። የናይጄሪያ “ሶቨሪን” ኢንቨስትመንት ባለስልጣን በአየር መንገዱ ላይ 46 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ቀደም ሲል ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፤ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ይህንን የሚያስተባበሉ ዘገባዎች ባለፈው መስከረም ወር አሰራጭተዋል።
የዛሬ ሶስት ወራት ገደማ ደግሞ በናይጄሪያ የሚገኙ የግል አየር መንገዶች፤ “ናይጄሪያ ኤይር” በሚል አዲስ ስያሜ ወደ ስራ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት በመቃወም በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በናይጄሪያ መንግስት ላይ ክስ መስርተዋል። ቡሃሪ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት ላይ፤ የናይጄሪያ አየር መንገድን ስራውን እንዳይጀምር ያገደው “የህግ መሰናክል” እንዲፈታ ጥያቄ መቅረቡን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ገልጿል።
ብሔራዊ አየር መንገዱን መልሶ ስራ ለማስጀመር መንግስታቸው ያሳለፈው ውሳኔ “ከፍተኛ ግምት” ያለው እንደሆነ ለአቶ ግርማ የገለጹት ፕሬዝዳንት ቡሃሪ፤ “ነገሮች መልካም ይሆናሉ” የሚል እምነታቸውን እንደገለጹላቸው ጽህፈት ቤታቸው ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል። ናይጄሪያን ለስምንት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ሲመሩ የቆዩት ቡሃሪ፤ በመጪው ቅዳሜ የካቲት 18፤ 2015 በሚካሄደው የናይጄሪያ ጠቅላላ ምርጫ ውጤት መሰረት ስልጣናቸውን ያስረክባሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት አቡጃ እና ሌጎስን ጨምሮ በናይጄሪያ ወደሚገኙ ስድስት ከተሞች በረራዎችን ያደርጋል። በናይጄሪያ የአየር ትራንስፖርት ማጓጓዣ ገበያ ከፍተኛ ቦታ ካላቸው አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የመጀመሪያውን በረራ ወደ ሀገሪቱ ያደረገው ከ60 ዓመታት በፊት ነበር። በእሁዱ ስብሰባ ላይ፤ አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ ወደ ሌጎስ እና አቡጃ በየዕለቱ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ቁጥር የማሳደግ ፍላጎት እንዳለው ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ዳንኤል አበበ መናገራቸው ተጠቅሷል።
አየር መንገዶች ገቢያቸውን ለማውጣት ከተቸገሩባቸው አምስት አገሮች ቀዳሚዋ ናይጄሪያ እንደሆነች ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር (IATA) ባለፈው ህዳር ወር አስታውቆ ነበር። በማህበሩ መግለጫ መሠረት የአየር መንገዶች ገቢ የሆነ 551 ሚሊዮን ዶላር ከናይጄሪያ እንዳይወጣ ታግዷል።
አየር መንገዶች ገቢያቸውን ከናይጄሪያ ማውጣት የተቸገሩት፤ በሀገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ መበረታቱን ተከትሎ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀድሞው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፤ አየር መንገዱ ናይጄሪያ እና ግብጽን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች 220 ሚሊዮን ዶላር ለማውጣት መቸገሩን ከዓመታት በፊት ለሬውተርስ የዜና ወኪል ተናግረው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]