በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ ትምህርት ቤቶች የኦሮምኛ ቋንቋ በተጨማሪነት መሰጠት ተጀመረ 

በአማኑኤል ይልቃል

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚተዳደሩ ትምህርት ቤቶች፤ የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መሰጠት ተጀመረ። የከተማይቱ ትምህርት ቢሮ የተጨማሪ ቋንቋ ትምህርቱን የሚሰጡ 2,600 ገደማ መምህራንን ለመቅጠር በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

የብዝኃ ቋንቋ ስርዓተ ትምህርት በአዲስ አበባ በሚገኙ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መተግበር የተጀመረው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባለፈው ጥር ወር ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው። በዚህ ውሳኔ መሰረት በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ኦሮምኛ በሁለተኛ ቋንቋነት እንዲሰጥ ይደረጋል። 

የአፍ መፍቻቸው ኦሮምኛ ለሆነ እና በዚሁ ቋንቋ ለሚማሩ ተማሪዎች ደግሞ፤ አማርኛን እንደ ተጨማሪ ቋንቋ እንዲወስዱ ካቢኔው ወስኖ ነበር። የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ ያካሄደውን ጥናት መሰረት በማድረግ እንደተላለፈ የተገለጸው ይህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ፤ የአረብኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋ ትምህርት ለዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍል ተማሪዎች በምርጫቸው መሰረት እንዲሰጥ መወሰኑም በወቅቱ ተገልጿል። 

ይህንን መሰረት በማድረግ የሀገር ውስጥ ተጨማሪ ቋንቋዎች ከሶስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች፤ አሁን ከተጀመረው የሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ጀምሮ እንዲሰጥ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ ደቻሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት 786 የግል እና የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ፤ 625 ያህሉ የኦሮምኛ ቋንቋን በተጨማሪነት ማስተማር መጀመራቸውንም አቶ አድማሱ ገልጸዋል። 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በኦሮምኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚያስተምሩ 402 ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፤ እነዚህ ትምህርት ቤቶች ከአዲሱ ውሳኔም አስቀድሞ አማርኛን በሁለተኛ ቋንቋን ሲያስተምሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል። የከተማ አስተዳደሩ ከኦሮምኛ በተጨማሪ በጋሞኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት እንደሚሰጥ እና በሶማሊኛ ቋንቋም በተመሳሳይ መልኩ ለማስተማር በዝግጅት ላይ እንዳለ ጠቁመዋል። 

በጋሞኛ የሚማሩም ሆነ ወደ ፊት በሚጀመሩ ሌሎች የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች፤ ከአማርኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋዎች ውስጥ የሚፈልጉትን መርጠው በተጨማሪነት እንደሚወስዱ አቶ አድማሱ አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት የኦሮምኛ እና አማርኛ ቋንቋዎችን በተጨማሪነት ለማስተማር የሚያስችሉ መጽሐፍት ዝግጅት ተጠናቅቆ፤ ለሁሉም የግል እና የመንግስት ትምህርት ቤቶች “በሶፍት ኮፒ” መሰራጨቱን አስረድተዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ የኦሮምኛ እና አማርኛ ቋንቋ መጽሐፍትን ለማሳተም በጨረታ ሂደት ላይ መሆኑን ምክትል የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል። የትምህርት ቢሮው ሁለቱን ቋንቋዎች የሚያስተምሩ 2,600 ገደማ ተጨማሪ መምህራን ቅጥር እያካሄደ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ቢሮው ባለፈው ሰኞ የካቲት 14፤ 2015 ባወጣው መረጃ፤ ኦሮምኛ እና አማርኛ ቋንቋዎችን ለማስተማር ማመልከቻ ካስገቡ መምህራን ውስጥ 657 ያህሉን መምረጡን አስታውቋል። 

የሁለቱ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ትምህርት በስራ ላይ ባሉ መምህራን ቢጀመርም፤ በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ የተላለፈበት የውጭ ቋንቋዎች ትምህርት ግን በዚህኛው መንፈቅ ዓመት ሳይጀመር ቀርቷል። በከተማይቱ ትምህርት ቢሮ ስር ያሉ ትምህርት ቤቶች የውጭ ቋንቋዎቹን ትምህርት መስጠት ያልጀመሩት፤ የአረብኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን ለመስጠት የሚያስችለውን “መርሃ-ትምህርት” (ካሪኩለም) ከትምህርት ሚኒስቴር ስላልደረሰው እንደሆነ አቶ አድማሱ ተናግረዋል።  

ለሁለቱ የውጭ ቋንቋዎች “መርሃ ትምህርት” የሚያዘጋጀው ትምህርት ሚኒስቴር ቢሆንም፤ የማስተማሪያ መጽሐፍት እና የመምህራን መምሪያ የማዘጋጀት ኃላፊነት የተጣለበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ነው። በ“መርሃ ትምህርቱ” መሰረት የመጽሐፍት ዝግጅት እንደተጠናቀቀ፤ የውጭ ቋንቋዎች ትምህርት እንደሚጀመር ምክትል የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል። ቢሮው የኦሮምኛ እና አማርኛ እና ቋንቋዎች ትምህርትን በሁለተኛ መንፈቅ ዓመት መጀመር የቻለው፤ የመጽሐፍት ዝግጅት በቶሎ በመጠናቀቁ እንደሆነ በማሳያነት አንስተዋል። 

የሁለቱ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በተያዘው ሁለተኛ መንፈቅ ዓመት መጀመሩ ግን በስነ ትምህርት ባለሙያዎች ዘንድ ጥያቄ አስነስቷል። በጎንደር ዩኒቨርስቲ የስነ ትምህርት ኮሌጅ ዲን የሆኑት ዶ/ር ክንዴ አበጀ፤ የቋንቋ ትምህርት ከሁለተኛው መንፈቀ ዓመት መጀመሩን እንደማይስማሙበት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “አንድ የትምህርት መጽሐፍን መሸፈን የሚቻለው በሁለት ሴሚስተሮች ነው” የሚሉት ዶ/ር ክንዴ፤ ተማሪዎች ከሁለተኛው መንፈቅ ዓመት በሚጀምሩት ትምህርት መማር የሚችሉት የመጽሐፉን ግማሽ በመሆኑ ትምህርቱ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ቢጀመር ይሻል እንደነበር ይከራከራሉ። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትኛዎቹ ቋንቋዎች በሁለተኛ ትምህርትነት እንደሚሰጡ ውሳኔ ባሳለፈ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ትምህርቱ መጀመሩም የስነ-ትምህርት ዲኑ ጥያቄ ያነሱበት ሌላኛው ነጥብ ነው። የአፍ መፍቻቸው አንድ ቋንቋ ለሆኑ እና ሌላ ቋንቋ በተጨማሪነት ለሚማሩ ተማሪዎች የሚዘጋጀው የትምህርት መጽሐፍ የተለያየ መሆኑን የሚያስረዱት ዶ/ር ክንዴ፤ እንደዚህ አይነቱን መጽሐፍ ለማዘጋጀት “ብዙ ጊዜ” እንደሚፈጅ ተናግረዋል። 

“የቋንቋ መማሪያ መጽሀፍት ሲዘጋጁ የሚጠቀሱት ምሳሌዎች፣ ስዕሎች የመሳሰሉት፤ በማህበረሰቡ ቅቡልነት ያላቸው እና ከተማሪዎች ስነ ልቦና ዝግጅት ጋር የተጣጣሙ መሆን አለባቸው” ሲሉም የመጽሐፍ ዝግጅቱ ረጅም ጊዜ ከሚወስድባቸው ምክንያቶች አንዱን ጠቅሰዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የትምህርት ጥናት ኢንስቲትዩት የካሪኩለም ዝግጅት መምህር የሆኑ ሌላ ባለሙያም ይህንን ሀሳብ ይስማሙበታል።

መጽሐፍት ከተዘጋጁ በኋላ በሙከራ ደረጃ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ላይ ሙከራ ሊደረግባቸው እና ግብረ መልስ ሊሰበሰብ እንደሚገባ የሚናገሩት የካሪኩለም ዝግጅት መምህሩ፤ በዚህም ምክንያት ሂደቱ ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚወስድ ያስረዳሉ። ለዚህም በምሳሌነት የሚጠቅሱት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ለተጀመረውን አዲስ ስርዓተ ትምህርት መጽሐፍት የተደረገውን ዝግጅት ነው። 

ከአንደኛ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ለሚተገበረው አዲሱ ስርዓተ ትምህርት የተዘጋጁ መጽሐፍት፤ ባለፈው ዓመት በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ መደረጋቸውን ባለሙያው ይጠቅሳሉ። “በሳይንሱ ሙከራ ተደርጎ፣ ግብዓት ተሰብስቦ፣ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ ነው የሚተገበረው። በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጀው እንዲሁ ወደ ትግበራ አይገባበትም” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት የካሪኩለም ዝግጅት መምህሩ፤ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በነበረው አጭር ጊዜ ይህን ዝግጅት ስለማድረጉ ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ግን የቋንቋዎቹ ትምህርት ከሁለተኛ መንፈቅ  ጀመሩ መጀመሩ ችግር አይፈጥርም ባይ ናቸው። ለዚህም በማስረጃነት የሚያቀርቡት፤ የትምህርት ቢሮው የዘንድሮውን የትምህርት ዘመን ያስጀመረው ተጨማሪ ቋንቋን ታሳቢ ያደረገ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ድልድል እንዲዘጋጅ በማድረግ መሆኑን ነው። 

“የክፍለ ጊዜ ድልድሎ ቀደም ብሎ የሄደ ነው። ድልድሉ ውስጥ ቀድሞ አለ። ይሄኛው አልቆ እስከሚመጣ ድረስ ክፍለ ጊዜው ለሌሎች የትምህርት አይነቶች ይሰጣል። መጽሐፍቱ አልቀው ስለመጡ፤ ክፍለ ጊዜውን ወደዚህ ማዞር ነው” ሲሉ አቶ አድማሱ መስሪያ ቤታቸው የተከተለውን ሂደት አስረድተዋል። ከውጤት አያያዝ ጋር በተያያዘም ችግር እንደማይፈጥርም ገልጸው፤ ይህ አይነቱ አሰራር “የተለመደ” መሆኑን አክለዋል።

“ዋናው የሚወስነው ለመማር ማስተማሩ የሚያስፈልጉ መምህራን እና መጽሐፍት መኖራቸው ነው። ከዚህ አንጻር ክፍተቶች የሉም ማለት አይደለም። ከአዲስነቱ አንጻር ግን [አካሄዱ] የተለሳለሰ ነው” ሲሉ ምክትል የቢሮ ኃላፊው አብራርተዋል። አቶ አድማሱ ክፍተቶች ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የመምህራን ዝግጅት ነው። እስካሁን ተጨማሪ ቋንቋ ማስተማር ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች፤ የመምህራንን ቅጥር የዘገየባቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)