ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ የሚመክረው የተመድ ጉባኤ ተጀመረ

የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ይዞታን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክረው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በጄኔቫ ተጀመረ። በምክር ቤቱ ጉባኤ የመጀመሪያዎቹ አራት ቀናት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ ከ100 በላይ የአገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች እና የክብር እንግዶች ይሳተፉበታል።

ከዛሬ ሰኞ የካቲት 20 ጀምሮ ለአምስት ሳምንታት የሚካሄደው ይኸው ስብሰባ፤ በተሳታፊዎቹ ቁጥር ብቻ ሳይሆን ለመወያያነት በተያዙ አጀንዳዎች ትልቅ ግምት የተሰጠው ሆኗል። በ52ኛው መደበኛ ጉባኤ የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት ዋነኛ መነጋገሪያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በዚሁ ጉባኤ ላይ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፤ በዩክሬን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታን ለመመርመር ያቋቋመው እና ሶስት አባላት ያሉት ኮሚሽን ሪፖርት ያቀርባል። 

በአውሮፓ የበረታው ጦርነት ከፍተኛ ትኩረት ያግኝ እንጂ፤ ምክር ቤቱ ለውይይት የመረጣቸው አጀንዳዎች በርካታ ናቸው። በጉባኤው ኢትዮጵያን ጨምሮ የአራት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ በተመለከተ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ጉዳይ ለውይይት የሚቀርበው፤ በጉባኤው አራተኛ ሳምንት መጋቢት 12፤ 2015 እንደሚሆን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው መርሀ ግብር ያሳያል።

በኢትዮጵያ “የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ” ላይ የሚደረገው ውይይት፤ “የምክር ቤቱን ትኩረት የሚሹ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታዎች” ከተባሉት ጎራ የተመደበ ነው። በዚሁ ውይይት፤  የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር ያቋቋመው ኮሚሽን አባላት የቃል ማብራሪያ ይሰጣሉ።

መቀመጫውን በኡጋንዳ ኢንቴቤ ያደረገው መርማሪ ኮሚሽኑ ባለፈው መስከረም ለ51ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተሳተፉ ወገኖች “የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች፣ የሰብዓዊ ሕግ ጥሰቶች እንደፈጸሙ ለማመን ምክንያታዊ የሆኑ ማስረጃዎች” ማግኘቱን አስታውቆ ነበር። የኮሚሽኑ አባላት ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፤ የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ባዳረሳቸው አካባቢዎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እስከ ጦር ወንጀል ሊደርሱ እንደሚችሉ መግለጻቸው ይታወሳል። 

የስራ ዘመኑ ለተጨማሪ አንድ ዓመት የተራዘመለት ይኸው መርማሪ ኮሚሽን፤ የሚያቀርባቸው ሪፖርቶች ከኢትዮጵያ መንግስት ብርቱ ተቃውሞ እና ትችት ሲቀርብባቸው ቆይቷል። መርማሪ ኮሚሽኑን በተመለከተ ጎላ ያለ ተቃውሞ በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ የሚደመጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ናቸው። 

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የመርማሪ ኮሚሽኑን ጉዳይ አንስተው ነበር። ኮሚሽኑ የተቋቋመው በኢትዮጵያ ላይ “ያልተፈለገ የፖለቲካ ጫና” በሚያሳድሩ አንዳንድ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ምክር ቤት አባል አገራት ፍላጎት እንደሆነ የገለጹት ደመቀ፤ የስራ ዘመኑ መራዘም መንግስታቸውን እንዳላስደሰተ አስታውቀዋል። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መርማሪ ኮሚሽኑ ያቀረበውን ሪፖርት፤ “ጎዶሎ እና በፖለቲካ ፍላጎት የተዘጋጀ” ሲሉ በአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ነቅፈውታል። አቶ ደመቀ በዚሁ ንግግራቸው፤ የመርማሪ ኮሚሽኑ አካሄድ በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት፣ በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም እንደዚሁም የኢትዮጵያ ተቋማት እያደረጉ ያለውን ጥረት ሊያዳክም እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በመጪው መጋቢት 12 የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ይዞታን በተመለከተ በጄኔቫ የቃል ማብራሪያ የሚያቀርቡት የመርማሪ ኮሚሽኑን በሊቀመንበርነት የሚመሩት መሐመድ ቻንዴ ኦትማን ናቸው። ኦትማን ከዚህ ቀደም ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሱዳንን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ የሚከታተሉ ገለልተኛ ባለሙያ ሆነው ሰርተዋል። የ71 ዓመቱ የቀድሞ የታንዛኒያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ፤ በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምረውን ኮሚሽን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተሾሙት ኬንያዊቷን ካሪ ቤቲ ሙሩንጊን በመተካት ነበር።

 ከሙሩንጊ በፊት መርማሪ ኮሚሽኑን በሊቀመንበርነት የመሩት ጋምቢያዊቷ ፋቱዋ ቤንሱዳም በኃላፊነታቸው ረዥም ጊዜ ሳይቆዩ መሰናበታቸው አይዘነጋም። መርማሪ ኮሚሽኑን ከዚህ ቀደም በሊቀመንበርነት የመሩት ሁለቱ የህግ ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ ከአባልነታቸው ጭምር ቢለቅቁም፤ ከምስረታው ጀምሮ የነበሩት አሜሪካዊው የህግ ባለሙያ ስቴቨን ራትነር እና ስሪላንካዊቷ ራዲካ ኮማራስዋሚ በ አባልነታቸው ቀጥለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)