ከዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ውስጥ 600 ሺህ ገደማ የሚሆኑት፤ ወደ ቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት እንደሚገቡ ተገለጸ

በአማኑኤል ይልቃል

የዘንድሮውን የ12ተኛ ክፍል ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ 600 ሺህ ገደማ የሚሆኑት ወደ ቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት እንደሚገቡ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ። ከእነዚህ ተማሪዎች ውስጥም 69.9 በመቶ የሚሆኑት ያመጡት ነጥብ፤ የ“ደረጃ ሶስት እና አራት” የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ለመሰልጠን የሚያስችላቸው መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ይህንን ያስታወቀው፤ የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት መቁረጫ ነጥብን አስመልክቶ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 22፤ 2015 በዋና መስሪያ ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን በትክክል ከወሰዱ 900 ሺህ ገደማ ተማሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ በማምጣት ወደ ዩኒቨርስቲ መግባት የሚያስችል ነጥብ ያመጡት 30 ሺህ ገደማ ብቻ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ከአንድ ወር በፊት አስታውቆ ነበር። 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በወቅቱ በሰጠው መግለጫ፤ ከቀሪዎቹ ተማሪዎች ውስጥ የተሻለ ያመጡት ተመርጠው ወደ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ እንደሚደረግ ገልጿል። የዩኒቨርሲቲዎችን የመቀበል አቅም መሰረት በማድረግ የሚመረጡት እነዚህ ተማሪዎች፤ በቀጥታ የዩኒቨርስቲ  ትምህርት የሚከታተሉ ሳይሆን በዚህ ዓመት የማሻሻያ ትምህርት ሲወስዱ ቆይተው ለፈተና የሚቀርቡ መሆናቸውንም አስታውቆ ነበር። 

ይህንን መሰረት በማድረግ የትምህርት ሚኒስቴር ከሁለት ሳምንት በፊት ባደረገው ድልድል፤ 100 ሺህ ገደማ የሚሆኑት በማሻሻያ የትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ ይታወሳል። ከእነዚህ ውጭ ያሉት ተማሪዎች ዕጣ ፈንታን በተመለከተ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በዛሬው መግለጫቸው በሰጡት ማብራሪያ፤ “ቀሪዎቹስ የሚለው እና የዩኒቨርስቲ መግቢያ ነጥብ ያገኙትን ጨምሮ ፍላጎት ያላቸው ካሉ የሚስተናገዱበትን ስርዓት መዘርጋት ደግሞ የእኛ ኃላፊነት ነው” ብለዋል።

ዛሬ ይፋ በተደረገው የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት የመቁረጫ ነጥብ መሰረት 760,832 ሺህ ያህሉ ተፈታኞች ስልጠናውን ለመከታተል የሚያበቃ ነጥብ ያመጡ ቢሆንም፤ ከእነዚህ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት በሌሎች ተቋማት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ተብሎ መገመቱን ወ/ሮ ሙፈሪያት ገልጸዋል። በዚህም መሰረት በቀጥታ በቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት ውስጥ ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቁት 608,666 ተፈታኞች መሆናቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ተማሪዎች እንደየነጥባቸው “ከአንድ እስከ አምስት ባሉ የስልጠና ደረጃዎች” ውስጥ እንደሚካተቱ አስታውቀዋል።

ከተፈታኝ ተማሪዎች ውስጥ አብዛኞቹ “በደረጃ ሶስት እና አራት” ለመሰልጠን የሚያበቃ ነጥብ ያመጡ መሆኑ በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። በእነዚህ ደረጃዎች የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች ብዛት 426,066 ናቸው። የመቁረጫ ነጥቡ ሲዘጋጅ “በደረጃ ሶስት እና አራት” የሚሰለጥኑ ተማሪዎች ቁጥር ከፍ እንዲል የተደረገው፤ ኢንዱስትሪው በእነዚህ ደረጃዎች የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በብዛት ስለሚፈልግ መሆኑን ወ/ሮ ሙፈሪያት ተናግረዋል።

የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል “በደረጃ አንድ እና ሁለት” የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ለመሰልጠን የሚያስችል ነጥብ ያመጡት 152,166 መሆናቸው ተገልጿል። የ“አድቫንስድ ዲፕሎማ” አቻ በሆነው ደረጃ አምስት ለመሰልጠን የሚያስችል ነጥብ ያመጡት ደግሞ 30,500 ተማሪዎች ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)