በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የተደረገው ህዝበ ውሳኔ እና የመራጮች ምዝገባ ውድቅ ተደርጎ በድጋሚ እንዲካሄድ ወሰነ፡፡ ቦርዱ በዞኑ የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ ውድቅ ያደረገው፤ “መጠነ ሰፊ” ጥሰቶች በመፈጸማቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ይህን ያስታወቀው፤ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ህዝበ ውሳኔን አስመልክቶ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 22፤ 2015 በሰጠው መግለጫ ነው፡፡ በዚሁ መግለጫ ላይ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፤ አጠቃላይ የህዝበ ውሳኔውን ሂደት እና በወላይታ ዞን የነበረውን ጥሰት በተመለከተ የተሰጠውን ውሳኔ በንባብ አሰምተዋል።
ቦርዱ በዛሬ መግለጫው በወላይታ ዞን የተፈጸመው ጥሰት “የምርጫ ሂደቱን ተዓማኒነት እና እውነተኝነት ያሳጣ እና አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱንም የሚያዛባ” መሆኑን ገልጿል። አቶ ውብሸት “የወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ ውድቅ እንዲደረግ እና የመራጮች ምዝገባ እና ድምጽ አሰጣጡም በድጋሚ እንዲደረግ ቦርዱ ወስኗል” ሲሉ የወላይታ ዞን የህዝበ ውሳኔ ሂደትን በተመለከተ የቦርዱን ውሳኔ ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ “ጥሰቶቹን ያስፈጸሙ፣ የፈጸሙ እና የተባበሩ” ያላቸውን አካላት በመለየት ምርመራ እንዲያከናውን እና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት እንዲያደርግ ለፌደራል ፖሊስ ደብዳቤ እንዲጻፍ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል። ምርጫ ቦርድ በቅድሚያ ግድፈቶች እንደተፈጸሙ የለየው በ77 የምርጫ ጣቢያዎች “የውጤት ማስታረቂያ እና መግለጫ ቅጾች” ላይ መሆኑን በዛሬው መግለጫ ጠቅሷል።
ቦርዱ በሰባ ሰባቱ ምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች መዝገብ ላይ ባደረገው ማጣራት፤ በ74 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ “ባልተጠበቀ መልኩ መጠነ ሰፊ ጥሰቶች” አግኝቼያለሁ ብሏል። ይህን ተከትሎ በወላይታ ዞን የህዝበ ውሳኔ ሂደት ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ባለፈው ሳምንት ሰኞ የካቲት 13፤ 2015 ውሳኔ አሳልፎ ነበር። ከዚህ የቦርዱ ውሳኔ በኋላ በወላይታ ዞን በስምንት ማዕከላት ከተደራጁት 1,112 ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ፤ ከእያንዳንዱ ማዕከላት 25 በመቶ ጣቢያዎችን በናሙናነት በመውሰድ ምርመራ ተደርጓል።
ምርጫ ቦርዱ ለናሙና ምርመራ ካደረገባቸው 350 የመራጮች መዝገቦች መካከል ሊታለፉ የሚችሉ ጥሰቶች የተፈጸመባቸው 13 መዝገቦች ብቻ መሆናቸውን ዛሬ አስታውቋል። ቀሪዎቹ 337 መዝገቦች “ከፍተኛ የሆነ ጥሰቶች እና ግድፈቶች” እንዳለባቸው ማረጋገጡን ቦርዱ ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ የምርጫ ቦርድ የክትትል ቡድን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እያንዳንዳቸው በ10 ምርጫ ጣቢያዎች፤ የተለያዩ ጥሰቶች ስለመፈጸማቸው ማረጋገጣቸውን የዛሬው የቦርዱ መግለጫ አመልክቷል።
በዛሬው መግለጫ ላይ የተገኙት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፤ “በወላይታ ዞን የተደረገው የመራጮች ምዝገባ ሂደት ከፍተኛ ችግር ጥሰት የገጠመው እውነተኝነቱ የተጣሰ ምዝገባ ሂደት መሆኑን” ተናግረዋል። ብርቱካን በዞኑ ተመዘገቡ ተብሎ ለተቋማቸው ሪፖርት የተደረገውን አሃዝ፤ “የተጭበረበር ወይም ትክክለኝነቱን ቦርዱ ማረጋገጥ ያልቻለው” ሲሉ ገልጸውታል።
ምርጫ ቦርድ ባለፈው ጥር ወር ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በአጠቃላይ ለህዝበ ውሳኔው ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡ 3 ሚሊዮን ገደማ መራጮች ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉት የተመዘገቡት በወላይታ ዞን መሆኑን አስታውቆ ነበር። ሆኖም ይህ አሃዝ በቦርዱ ሰብሳቢ “እውነተኝነት የጎደለው” መሆኑ ዛሬ ተገልጿል።
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ በህዝበ ውሳኔው የተስተዋሉ ጥሰቶችን ተከትሎ “የህግ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ አልወሰዱም” ሲሉ ወቅሰዋል። “የተፈጸሙት ጥሰቶች የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ መሆናቸውን ገልጸን፤ በፌደራል ፖሊስ በአፋጣኝ ምርመራ ተደርጎ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀን ነበር። በጊዜው እርምጃ ባለመወሰዱ ጭምር ነው መጨረሻ ላይ ያየነውን መጠነ ሰፊ ችግር ያስከተለው” ሲሉ ብርቱካን በዛሬው መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
በወላይታ ዞን የተፈጸሙት ጥሰቶች “አብዛኛዎቹ” በህግ የሚያስጠይቁ መሆናቸውን ያነሱት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ፤ “የህግ ተጠያቂነት ሳይታይ እንደገና [ህዝበ ውሳኔውን] ብንደግመው፤ ምናልባት ተመሳሳይ ጥሰት ያጋጥማል” ሲሉ አጥፊዎች በህግ ተጠያቂ አለመደረጋቸው የሚኖረውን ውጤት አስረድተዋል።
የወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ በድጋሚ የሚካሄደበትን ቀን በተመለከተ በመግለጫው ላይ ከተገኙት ጋዜጠኞች ለተነሳ ጥያቄ ብርቱካን በሰጡት ምላሽ፤ “አሁን ተነስተን ድጋሚ ህዝበ ውሳኔው በዚህ ቀን ይደረጋል ማለት አንችልም” ብለዋል። ህዝበ ውሳኔውን በድጋሚ ለማካሄድ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት እና አስፈጻሚዎች ምልመላ እንደገና ማድረግ እንደሚያስፈልግም አክለዋል።
በዛሬው የምርጫ ቦርድ መግለጫ፤ ከወላይታ ዞን በተጨማሪ በድምሩ 81 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ጥሰቶች በመፈጸማቸው የህዝበ ውሳኔው ውጤት ላይ ሳይካተቱ መቅረታቸው ተገልጿል። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ እነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች “ትክክለኛ ባለመሆናቸው ቢቀነሱም፤ ቢደመሩም የሚያመጡት ልዩነት ስለሌለ” የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ለመመስረት ህዝበ ውሳኔ የተካሄደባቸው አምስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች የተረጋገጠ ውጤት ይፋ መደረጉን አብራርተዋል።
በተረጋገጠው የቦርዱ የህዝበ ውሳኔ ውጤት መሰረት፤ በአስሩ መዋቅሮች “ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልልን ለመመስረት የቀረበው አማራጭ አብላጫ ድምጽ አግኝቷል። የ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል”ን ለመመስረት ህዝበ ውሳኔ የተካሄደባቸው ስድስት ዞኖች ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ እና ጌዲኦ ናቸው። እንደ ስድስት ዞኖች ሁሉ በነባሩ የደቡብ ክልል ስር ያሉት፤ ደራሼ፣ ቡርጂ፣ አሌ፣ አማሮ እና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎችም ባለፈው ጥር 29፤ 2015 ህዝበ ውሳኔ ተካሄዶባቸዋል።
ከወላይታ ዞን ውጭ ባሉት አስር መዋቅሮች፤ “ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል መመሰረቱን የሚቃወመው አማራጭ የተሻለ ድምጽ ያገኘው በጌዲኦ ዞን ነው። በዞኑ ድምጽ ከሰጡ 300 ሺህ ገደማ መራጮች ውስጥ 46 ሺህ የሚሆኑት፤ በጎጆ ቤት የተወከለውን እና “ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል መመስረቱን የሚቃወመውን አማራጭ መርጠዋል።
በዛሬው የምርጫ ቦርድ መግለጫ ላይ የተገኙ ጋዜጠኞች፤ ለቦርዱ ኃላፊዎች ካቀረቧቸው ጥያቄዎች ውስጥ የወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔው በድጋሚ የሚካሄድበትን ቀን የተመለከተው ይገኝበታል። ብርቱካን ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “አሁን ተነስተን ድጋሚ ህዝበ ውሳኔው በዚህ ቀን ይደረጋል ማለት አንችልም” ብለዋል። ህዝበ ውሳኔውን በድጋሚ ለማካሄድ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት እና አስፈጻሚዎች ምልመላ እንደገና ማድረግ እንደሚያስፈልግም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ዝርዝር መረጃ ከቆይታ በኋላ ታክሎበታል]