ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በቀረበበት ክስ ላይ ፍርድ ለመስጠት ቀጠሮ ተሰጠ  

በሃሚድ አወል

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በቀረበበት ክስ ላይ ፍርድ ለመስጠት ለመጪው ሳምንት ረቡዕ የካቲት 29፤ 2015 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። የመከላከያ ሠራዊት “በተደጋጋሚ” ማስረጃ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ባለማቅረቡ፤ ፍርድ ቤቱ ማስረጃውን ሳይመለከት ፍርድ ለመስጠት መወሰኑን አስታውቋል። 

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ከኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ይቅረብ የተባለውን ማስረጃ በተመለከተ ትዕዛዝ ለመስጠት ነበር። ዛሬ ረቡዕ የካቲት 22፤ 2015 በችሎት በኩል በሶስት ዳኞች የተሰየመው ችሎቱ፤ “ከመከላከያ ሠራዊት ተጨማሪ ማስረጃው እንዲቀርብ ተደጋጋሚ ጥረት” ቢያደርግም  አለመቅረቡን ገልጿል።  

ፍርድ ቤቱ ከመከላከያ ሠራዊት እንዲቀርብለት አዝዞ የነበረው ማስረጃ፤ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ሽልማት እና ማዕረግ የተሰጠበት ቃለ ጉባኤ ነበር። ጋዜጠኛ ተመስገን ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ በ“ፍትሕ” መጽሔት ባሳተመው ጽሁፍ፤ ለመከላከያ ሠራዊት አባላት የተሰጠው ሽልማት እና ማዕረግ አሰጣጥ “የብሔር የበላይነት የተጫነው ነው” ሲል መተቸቱ በዐቃቤ ህግ ክስ እንዲቀርብበት አድርጎታል።

ተመስገን በዚህ ጽሁፉ በሽልማት እና ማዕረግ አሰጣጡ “ግንባር ደርሰው የማያውቁ እና በሰላም አስከባሪነት በውጪ ሀገር የነበሩ ኦሮምኛ ተናጋሪ መኮንኖችንም ጨምሯል” ሲል የሽልማት እና ማዕረግ አሰጣጡን መንቀፉ በክሱ ላይ ተገልጿል። ለመከላከያ ሠራዊት አባላት ሽልማት እና ማዕረግ የተሰጠው፤ “በጦር ሜዳ ጀብዱ ለሰሩ ወታደሮች እና ኃይል ለመሩ አመራሮች” መሆኑ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።   

የጋዜጠኛውን ክስ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ተመስገን እንዲከላከል በወሰነበት ክስ ላይ ከቀረቡት ሁለት ፍሬ ነገሮች መካከል አንዱ የዚሁ የሽልማት እና የማዕረግ ጉዳይ ነው። ፍርድ ቤቱ ታህሳስ 12፤ 2015 በዋለው ችሎቱ “ለትክክለኛ ፍርድ እንዲረዳው” ሽልማት እና ማዕረግ የተሰጠበት የመከላከያ ሠራዊት ቃለ ጉባኤ እንዲቀርብለት አዝዞ ነበር። 

ፍርድ ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ማስረጃው እንዲቀርብለት ካዘዘበት ጊዜ ጀምሮ ለአራት ጊዜ ያህል ተለዋጭ ቀጠሮዎችን ሰጥቷል። የመከላከያ ሠራዊትን ወክለው ፍርድ ቤት የቀረቡ ኃላፊዎች የተባለው ማስረጃ “ሚስጢራዊ ሰነድ” መሆኑን ማቅረብ እንደማይችሉ ገልጸዋል። በጥር ወር ላይ በነበረው የፍርድ ቤት ቀጠሮ የመከላከያ ሠራዊት አመራር የሆኑ ግለሰብ፤ ሽልማት እና ማዕረግ የተሰጠበት ቃለ ጉባኤ “ሚስጢራዊ ሰነድ” መሆኑን የሚገልጽ መመሪያ ለችሎቱ አቅርበው ነበር።

መመሪያው የደረሰው ችሎቱ፤ በመመሪያው መሰረት የሰነዱ ሚስጢራዊነት “ፍርድ ቤትን የሚመለከት ነው ወይ?” የሚለውን ጉዳይ  ከመረመረ በኋላ፤ “ማስረጃው ለፍትህ አሰጣጥ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው መቅረብ አለበት” በሚል በድጋሚ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።   ሆኖም ችሎቱ “በተደጋጋሚ” እንዲቀርብ ያዘዘው ማስረጃ ባለፈው ሳምንት አርብ በነበረው ቀጠሮውም ሳይቀርብ ቀርቷል።

ችሎቱ በዛሬው ውሎው “ማስረጃውን በመጠባበቅ ከዚህ በላይ የተከሳሹን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት ሊገደብ አይገባም” በሚል ማስረጃውን ሳይመለከት ፍርድ ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቷል። ይህን ተከትሎም ችሎቱ ማስረጃውን ሳይመለከት ፍርድ ለመስጠት ለየካቲት 29፤ 2015 ቀጠሮ ሰጥቷል። 

ዐቃቤ ህግ በ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ ላይ ያቀረባቸው ሶስት ተደራራቢ ክሶች ነበሩ። የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከአራት ወራት በፊት ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ባሳለፈው ውሳኔ ግን ተከሳሹን ከሁለቱ ክሶች በነጻ አሰናብቷል። ተመስገን ነጻ የተባለባቸው ሁለት ክሶች “ወታደራዊ ምስጢርን መግለጽ” በተመለከተ በወንጀል ህጉ የተደነገገውን አንቀጽ ተላልፏል በሚል እና “የሀሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ አሰራጭቷል” በሚል የቀረቡ ነበሩ። 

ፍርድ ቤቱ በጥቅምት ወር መጀመሪያ በነበረው የችሎት ውሎ፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ላይ የቀረበውን ሶስተኛ ክስ ድንጋጌ በመቀየር በተቀየረው አንቀጽ እንዲከላከል ወስኗል። በጋዜጠኛው ላይ የቀረበው ሶስተኛ ክስ “መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት የወንጀል ተግባር” ፈጽሟል የሚል ነበር። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይህ ክስ እንዲስተካከል ያደረገው “የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር” በወጣው አዋጅ መሰረት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)