በሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በሚንቀሳቀስ የገንዘብ መጠን ላይ በድጋሚ ገደብ ሊጣል ነው 

በአማኑኤል ይልቃል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በቀን ውስጥ ማንቀሳቀስ የሚቻለው የገንዘብ መጠን ላይ ያነሳውን ገደብ በድጋሚ የሚጥል መመሪያ አዘጋጀ። ረቂቅ መመሪያው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞች በአካውንታቸው ውስጥ መያዝ የሚችሉትን የገንዘብ መጠን ከ100 እስከ 233 በመቶ አሳድጓል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጀው ይህ ረቂቅ የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድ አውጪነት ፈቃድ አሰጣጥ ረቂቅ መመሪያ ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ ያለውን መመሪያ እና ማሻሻያዎቹን የሚተካ ነው። አሁን በስራ ላይ ያለው መመሪያ፤ በፋይናንስ ተቋማት ብቻ ተገድቦ የነበረውን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ዘርፍ “ለፋይናንስ ቴክኖሎጂ ተቋማት” (Fintech) የከፈተ ነበር። 

ይህ መመሪያ ከወጣ በኋላ መንግስታዊው የቴሌኮም አቅራቢ ድርጅት ኢትዮ ቴሌኮም፤ በዘርፉ የመጀመሪያ የሆነውን ፈቃድ በማግኘት  የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ስራን ጀምሯል። “ቴሌ ብር” በተሰኘ ስያሜ በግንቦት 2013 ዓ.ም የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ኢትዮ ቴሌኮም፤ እስከ 2015 የመጀመሪያ አጋማሽ ድረስ ብቻ አገልግሎቱን የሚጠቀሙ 27.2 ሚሊዮን ደንበኞችን አፍርቷል።

ከግሉ ዘርፍ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለመስጠት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በማግኘት ቀዳሚ የሆነው “ካቻ ዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስስ” የተሰኘው ድርጅት ነው። “ካቻ” በሚል ስያሜ ለሚጠራው አገልግሎቱ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ፈቃድ ያገኘው ድርጅቱ፤ ወደ ስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል። በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ካገኙት ከእነዚህ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ተቋማት በተጨማሪ የንግድ ባንኮችም የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትን ለደንበኞቻቸው እየሰጡ ይገኛሉ።  

እነዚህ ተቋማት የሚሰጡትን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለመምራት የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ የወጣው የመጀመሪያው መመሪያ፤     ደንበኞችን በሶስት ደረጃዎች ከፋፍሏቸው ነበር። ተጠቃሚዎች በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚቀመጡት፤ አገልግሎቱን ለመጠቀም “አካውንት” ሲከፍቱ ስለራሳቸው የሞሉትን መረጃ መሰረት በማድረግ ነው።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አንድ የብሔራዊ ባንክ ኃላፊ፤ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ በሚቀመጡ ደንበኞች መካከል ያለው ዋነኛው ልዩነት “የመታወቂያ መኖር እና አለመኖር” መሆኑን ይገልጻሉ። መታወቂያ የሌላቸው ደንበኞች “ደረጃ አንድ” ምድብ ላይ በመሆን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ኃላፊው ያስረዳሉ። ይህ አሰራር የተዘረጋው የፋይናንስ ተደራሽነት ለማስፋት በሚል እንደሆነም አክለዋል።  

አሁን በስራ ላይ ባለው መመሪያ መሰረት፤ በ“ደረጃ አንድ” ላይ የሚቀመጡ ደንበኞች የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትን ለማግኘት ስማቸውን፣ የልደት ቀናቸውን፣ የመኖሪያ አድራሻቸው፣ ስልክ ቁጥራቸውን መሙላት የሚኖርባቸው ሲሆን የቅርብ ጊዜ ፎቶግራፍ ማቅረብም ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ደረጃ የሚመደቡ ደንበኞች የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለመጠቀም ምዝገባ የሚያከናውኑት፤ ቀድሟቸው በተመዘገበ ደንበኛ በኩል ነው።

“ደረጃ ሁለት” ላይ የሚቀመጡ ደንበኞች በአንጻሩ ከሚያሟሏቸው ግላዊ መረጃዎች በተጨማሪ መታወቂያቸውን ያቀርባሉ። የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆንም በሌላ ደንበኛ በኩል ማለፍ አይጠበቅባቸውም። “ደረጃ ሶስት” የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ተቋማትን በዋነኛነት የሚመለከት ነው። በዚህ ደረጃ የሚመደቡ ደንበኞች ተቋሙ የሚገኝበትን አድራሻ እንዲያቀርቡ በተጨማሪነት ይጠየቃሉ። 

በሶስት ተከፍሎ የነበረው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ምደባ፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አማካኝነት በየካቲት 2014 ዓ.ም. በተሻሻለው መመሪያ ወደ ሁለት ዝቅ እንዲል ተደርጓል። ይህ የመመሪያ ማሻሻያ ደንበኞች በቀን ውስጥ ማዘዋወር በሚችሉት የገንዘብ መጠን ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ እንዲነሳ አድርጎ ነበር። ከሁለት ሳምንት በፊት ለባለድርሻ አካላት የተሰራጨው አዲሱ ረቂቅ መመሪያ ግን ዕለታዊ የገንዘብ ዝውውር መጠን ላይ በድጋሚ ገደብ የጣለ ሆኗል።  

በኢትዮጵያ በብሔራዊ ባንክ የክፍያ እና የሂሳብ ማወራረጃ ሥርዓት ተጠባባቂ ዳሬክተር አቶ ሰለሞን ዳምጠው ተፈርሞ የተሰራጨው ይኸው ረቂቅ መመሪያ፤ የ“ደረጃ አንድ” ደንበኞች በአንድ ቀን ውስጥ ከ20 ሺህ ብር በላይ ማዘዋወር እንደማይችሉ አስፍሯል። በዚህ ደረጃ የተቀመጡ ደንበኞች፤ በአካውንታቸው ውስጥ መያዝ የሚችሉት የገንዘብ መጠን ከአምስት ሺህ ወደ 10 ሺህ ብር ከፍ እንዲልም ተደርጓል።

አዲሱ ረቂቅ መመሪያ በ“ደረጃ ሁለት” የተመደቡ ደንበኞች በቀን ውስጥ ማዘዋወር የሚችሉት የገንዘብ መጠን እስከ 300 ሺህ ብር ድረስ    መሆኑን አስቀምጧል። መመሪያው በዚህ ምድብ ያሉ ደንበኞች በአካውንታቸው ውስጥ መያዝ የሚችሉት የገንዘብ መጠን በ70 ሺህ ጨምሮ 100 ሺህ ብር አድርሶታል። ባለፈው ዓመት ተነስቶ የነበረው ገደብ በአዲሱ መመሪያ በድጋሚ እንዲጣል የታቀደው በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የብሔራዊ ባንክ ኃላፊ ገልጸዋል።

የመጀመሪያው ምክንያት ከገንዘብ ፖሊሲ ቁጥጥር ጋር የተያያዘ ነው። በሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የሚንቀሳቀሰው ብር በባንክ ውስጥ የሚቀመጥ እና እንደ ብድር ላሉ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎቶች የማይውል መሆኑ ገደቡ እንዲጣል ምክንያት መሆኑንም ያስረዳሉ። “ይህ ገንዘብ ገደብ የማይቀመጥለት ከሆነ፤ እዚህ ቦታ ላይ ተጠራቅሞ ለሌሎች አገልግሎቶች እንዳይውል ያደርገዋል” የሚሉት ኃላፊው፤ ይህ አይነቱ አካሄድ በገንዘብ ፖሊሲው ላይ መዛባትን ሊያስከትል እንደሚችል አብራርተዋል። 

የብሔራዊ ባንክ ኃላፊው በሁለተኛነት የጠቀሱት ምክንያት “በዲጂታል መንገድ” የሚዘዋወረው ገንዘብ ለዘረፋ የመጋለጥ እድል ያለው መሆኑን ነው። አብዛኛው ማህበረሰብ ጋር ያለው የዲጂታል ግንዛቤ “አነስተኛ” መሆኑን የሚያነሱት ኃላፊው፤ “ይህንን አደጋ ለመቀነስ የመጠን ገደብ የማይቀመጥበት ከሆነ በቀላሉ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ለመጭበርበር ወይም ለስርቆት እንዲዳረግ ያደርጋል” ብለዋል። ይህንን አይነቱን ገደብ ማስቀመጥ “በሁሉም አገራት” ውስጥ የሚተገበር እና “ዓለም አቀፍ ልምምድ” ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል። 

በአዲሱ ረቂቅ መመሪያ የገደብ አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግ ቢገለጽም፤ ከብሔራዊ ባንክ በሚሰጥ “የተለየ ፈቃድ” ከገደቡ በላይ የሆነ ገንዘብ ማስተላለፍ የሚቻልበት መንገድ እንዳለ አስቀምጧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ፈቃድ ለሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ሰጪው የሚፈቅደው፤ ወደ አገር ውስጥ ለሚመጣ ውጭ ምንዛሬ፣ እንዲሁም ለደመወዝ እና ታክስ ክፍያዎች መሆኑ በረቂቅ መመሪያው ላይ ሰፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)