በሃሚድ አወል
ኢትዮጵያ “ወጪ ለመቆጠብ” በሚል ምክንያት ዘግታቸው ከነበሩ ኤምባሲዎች መካከል፤ አምስቱን ዳግም ልትከፍት መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያሉ ሁለት የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ተናገሩ። ኤምባሲዎቹን ለመክፈት ለገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጥያቄ መቅረቡንም ምንጮቹ ገልጸዋል።
በድጋሚ ይከፈታሉ የተባሉት አምስት ኤምባሲዎች፤ በብራዚል፣ ኢንዶኔዢያ፣ ኩባ፣ ኮትዲቯር እና ዚምባቡዌ የሚገኙ ናቸው። በእነዚህ ሀገራት ይገኙ የነበሩት ኤምባሲዎች ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር እንዲዘጉ የተደረገው፤ “ወጪ ለመቆጠብ” እንደዚሁም “ኢትዮጵያውያን ዜጎች ያሉባቸውን አካባቢዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት” እንደነበር ምንጮች አስረድተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአምስቱ ሀገራት ያሉትን ኤምባሲዎች የመዝጋት እርምጃ የወሰደው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ በውጭ ሀገር ያሏትን ኤምባሲዎች እና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ቁጥር መቀነስ እንደሚገባት ካሳሰቡ በኋላ ነው። አብይ ከአንድ አመት ከስምንት ወራት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፤ “እኛ ዶላር በየቦታው ከምንበትን፤ ለጊዜውም ቢሆን ለስድስት ወርም ለዓመትም ቢሆን፤ አሁን ካሉን ኤምባሲዎች ቢያንስ ሰላሳው መዘጋት አለበት” ሲሉ ወጪ ለመቆጠብ የሚዘጉ ኤምባሲዎች እንዳሉ ተናግረው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ከተናገሩ ጥቂት ወራት በኋላ በውጭ ሀገራት ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ተዘግተው ሰራተኞቻቸውም ወደ ሀገር ውስጥ ተመልሰዋል። ኢትዮጵያ ዳግም ኤምባሲ ለመክፈት በዝግጅት ላይ ካለችባቸው አምስት ሀገራት ያላትን ግንኙነት፤ ላለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ስታከናውን የቆየችው በሀገር ውስጥ ባሉ ዲፕሎማቶቿ አማካኝነት ነበር።
ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ሆነው ለአምስቱ ሀገራት በአምባሳደርነት የሚያገለግሉ (non-resident ambassadors) ዲፕሎማቶች በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሹመት አማካኝነት የተሾሙት ደግሞ ከአንድ ዓመት በፊት ነበር። በዚህም መሰረት ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ የኢንዶኔዢያ፣ ዶ/ር ገነት ተሾመ የኩባ፣ አቶ ጣፋ ቱሉ የብራዚል፣ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ የኮትዲቯር እንዲሁም አቶ ረሻድ መሐመድ የዚምባቡዌ አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል።
ይህንን ሹመት ተከትሎ በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ የነበሩት ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ፤ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሚሆኑ አምባሳደሮች ወደ ተወከሉበት ሀገር አስፈላጊ ሲሆን እየተመላለሱ እንደሚሰሩ አስታውቀው ነበር። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያሉ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ፤ “ሀገሪቷ ኤምባሲዎች home based ሆነው እንዲሰሩ ሌላ መዋቅር ፈጥራ ነበር። እርሱ አሰራር አሁን ውጤታማ ሊያደርግ ስላልቻለ home based ተብለው የነበሩት ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው” ሲሉ አዲሱን የመንግስት ውሳኔ አስረድተዋል።
አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራር፤ ውሳኔው ከአንድ ወር በፊት የተወሰነ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዚህ ውሳኔ መሰረት በአምስት ሀገራት የነበሩ ኤምባሲዎች ዳግም የሚከፈቱት፤ “ስራው ውክልና ስለሚፈልግ፤ ኢትዮጵያም በኤምባሲ መወከል ስላለባት መሆኑን” አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)