በሃሚድ አወል
አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አንድ የፓርቲዎች ትብብር፤ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የተቋቋመውን የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ተቀላቀሉ። “የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ” የተሰኘውን ይህን ስብስብ የተቀላቀሉ ፓርቲዎች እና ነባሮቹ የኮከሱ አባላት ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ የካቲት 25፤ 2015 በአዲስ አበባ ከተማ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
አስር የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የተሰኘው የፓርቲዎች ትብብር፤ በኢትዮጵያ ለሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር “አማራጮችን” ለማቅረብ የሚያስችላቸውን “ኮከስ” የመሰረቱት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ነበር። ከኮከሱ ምስረታ ዘጠኝ ወራት በኋላ፤ አራት ክልል አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ትብብር ለሕብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲ ፌደራሊዝም የተሰኘው የፓርቲዎች ጥምረት የስብስቡ አባል ሆነዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስን የተቀላቀሉት ክልል አቀፍ ፓርቲዎች፤ የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ)፣ አገው ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፣ የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ (ገዳ ቢሊሱማ) እና ሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ (ሲፌፓ) ናቸው። ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር በይፋ የተመሰረተው የሲፌፓ ሊቀመንበር አቶ ተሰማ ኤሊያስ፤ ፓርቲያቸው ኮከሱን የተቀላቀለበትን ምክንያት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ሲገልጹ “ሀገራዊ ምክክሩን መርህን የተከተለ እንዲሆን ልናደርግ ነው የተሰባሰብነው” ብለዋል።
በስሩ የያዛቸው አባላት 16 የደረሰው ይህ ስብስብ፤ በተቋቋመበት ወቅት ሀገራዊ ምክከሩን የተመለከቱ አማራጭ ምክረ ሃሳቦችን አቅርቦ ነበር። ኮከሱ ካቀረባቸው ምክረ ሃሳቦች መካከል የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን “በአዲስ መልክ እንዲዋቀር” የሚጠይቀው አንደኛው ነው። የኮከሱ አባል የሆነው የአፋር ህዝብ ፓርቲ (አህፓ) ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደም፤ ከኮሚሽኑ ማቋቋያ አዋጅ ጀምሮ እስከ አስራ አንዱ ኮሚሽነሮች አሰያየም ድረስ “የመንግስት ጣልቃ ገብነት አለበት” ብለው እንደሚያስቡ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በግንቦት 2014 ዓ.ም በኮከሱ ቀርቦ የነበረው ሌላኛው ምክረ ሃሳብ፤ “የኮሚሽኑ አባላትን ግልጽነት፣ ነጻነት እና አካታችነት ለማረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኮሚሽኑ ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል” የሚል ነው። በአጀንዳ ቀረጻ ሂደት ውስጥ “ሁሉም ባለድርሻ አካላት አጀንዳውን ያለ አድሎኦ የሚያቀርብበት ግልጽ አሰራር” እንዲኖር የሚጠይቅ ምክረ ሃሳብም በኮከሱ ቀርቦ ነበር።
በአቶ ሙሳ አደም ሊቀመንበርነት በሚመራው በዚህ ኮከስ፤ አራት ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች፣ ሁለት የፓርቲ ግንባሮች እና ቅንጅቶች በአባልነት ተካተተዋል። አራቱ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) እና ህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ህብር) ናቸው። በኮከሱ አባል ከሆኑ አስር ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲ ሉዓላዊነት (ዓረና)፣ የአፋር ህዝብ ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ይገኙበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[ማረሚያ፦ በዚህ ዘገባ ላይ “የአገው ብሔራዊ ኮንግረስ” ተጠቅሶ የነበረው በስህተት መሆኑን እናስታውቃለን። በመረጃ አሰባሰብ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን]