በአማኑኤል ይልቃል
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሁን ባለው አሰራር የሚቀጥል ከሆነ፤ ሁሉም የገጠር ከተሞች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ለማድረግ 20 ዓመት እንደሚፈጅበት ገለጸ። መንግስታዊው ተቋም በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ለመተግበር የያዘውን ስትራቴጂክ እቅድ ለማስፈጸም ከሚያስፈልገው 2.76 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ፤ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን በ“ጉድለት” (deficit) የተመዘገበ መሆኑን አስታውቋል።
ባለፈው ዓመት በተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር የሚገኘው ይህ የልማት ድርጅት፤ የኤሌክትሪክ ኃይል በጅምላ ገዝቶ ለደንበኞች የመሸጥ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ነው። ተቋሙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ መስመሮችንም ያስተዳድራል። ይህ መንግስታዊ ድርጅት ከዘንድሮ ዓመት ጀምሮ እየተገበረው በሚገኘው ስትራቴጂክ እቅድ፤ የኤሌክትሪክ ስርጭት መሰረተ ልማት ሽፋንን ለመጨመር፣ ያረጁ መሰረተ ልማቶችን ለመጠገን እና የፋይናንስ አቅሙን ለማሳደግ ወጥኗል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በስትራቴጂክ እቅዱ የመጨረሻ ዓመት በሆነው በ2017፤ የደንበኞቹን ቁጥር አሁን ካለበት 4.5 ሚሊዮን ወደ 7.9 ሚሊዮን ለማድረስ ማቀዱንም አስታውቋል። ተቋሙ ይህን ያስታወቀው፤ የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅዱን አስመልክቶ ዛሬ ሰኞ የካቲት 27፤ 2015 ከ“ቁልፍ ደንበኞች” ጋር ባካሄደው ውይይት ላይ ነው። ይህን እቅድ ለማስፈጸም ተቋሙ የሚያስፈልገው “የካፒታል እና ኦፕሬሽናል” በጀት 2.76 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነም በውይይቱ ላይ ተገልጿል።
በአዲስ አበባው ሂልተን ሆቴል በተካሄደው በዚሁ ውይይት ላይ ማብራሪያ የሰጡት የተቋሙ የለውጥ እና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ጤናው፤ እቅዱን ለማስፈጸም ከሚያስፈልገው በጀት ውስጥ 1.17 ቢሊዮን ዶላሩ “አለ ተብሎ የሚታሰብ” (available) ገንዘብ መሆኑን አስረድተዋል። ቀሪው 1.59 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ በ“ጉድለት” የተያዘ መሆኑን ተናግረዋል። “Available የተባለው በጀት በተለያዩ መንገዶች ሊኖር ይችላል። ግን እጅ ላይ የተያዘ በጀት አይደለም። ወደፊት እንደሚመጣ ታሳቢ ተደርጎ፤ ይሄን ያህል [ገንዘብ] በእነዚህ አማራጮች ይኖረናል ያልነው ነው” ሲሉ አቶ እሱባለው ለ“ኢትዮጰያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዲስትሪውቢሽን ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ብዙወርቅ ደምሴ በበኩላቸው “ይገኛል” ከተባለው በጀት ውጪ ያለው ጉድለትም፤ በተመሳሳይ ተቋሙ አማራጮችን ከግምት ውስጥ አስገብቶ ሊሞላው የሚገባ እንደሆነ አስገንዘበዋል። “ጉድለት ስንል እኛ እጅ ላይ የሌለ ነገር ግን ከመንግስትም ከሌሎችም ባለድርሻ አካሎች የምንጠብቀው ነው። ይህ ካልተገኘ ያስቀመጥነው የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አይሳካም” ሲሉ የተቋሙ ምክትል ስራ አስፈጻሚ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

ተቋሙ ያለበት ይህ የፋይናንስ ውስንነት፤ የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅዱን ለማስፈጸም “ተግዳሮት ይሆናሉ” ተብለው በዛሬው ውይይት ላይ ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ በዋነኛነት የተቀመጠ ነው። ለፋይናንስ ጉድለቱ አንደኛው ምክንያት ተደርጎ በዛሬው ውይይት የተነሳው ጉዳይ፤ ተቋሙ የኤሌክትሪክ ኃይል ከሚያቀርብላቸው ደንበኞቹ የሚሰበስበው ገንዘብ “ዝቅተኛ” መሆን ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2014 ዓ.ም ከኃይል ሽያጭ ያገኘው ገቢ 20.94 ቢሊዮን ብር ሲሆን በተያዘው ዓመት ይህንን ገቢ 33.5 ቢሊዮን ብር ለማድረስ አቅዷል። የሶስት ዓመት እቀዱ በሚጠናቀቅበት 2017 ዓ.ም፤ ከኃይል ሽያጭ ሊሰበሰብ የታሰበው ገቢ 40.2 ቢሊዮን ብር ነው።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ “ዝቅተኛ” እንዲሆን የተደረገው “የህብረተሰቡ የመክፈል አቅም ዝቅተኛ ነው” በሚል እሳቤ እንደሆነ ለውይይቱ ተሳታፊዎች የገለጹት የተቋሙ የለውጥ እና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር፤ ይህም ድርጅቱ በተለያዩ አካባቢዎች የገነባውን ሀብት “እየበላ እንዲሄድ አድርጓል” ብለዋል። አሁን የሚከፈለው የአገልግሎት ታሪፍ፤ የተበላሹ እና ያረጁ መሰረተ ልማቶችን ለመተካት እንኳ የማያስችል መሆኑንም በአጽንኦት አንስተዋል።

አሁን በስራ ላይ ያለው ታሪፍ ከአምስት ዓመት በፊት የተሻሻለ መሆኑን ያስታወሱት አቶ እሱባለው፤ ከማሻሻያው በኋላ የተከሰተው የዋጋ ንረት፤ ለጥገና እና ለማስፋፊያ የሚያስፈልጉ ግብአቶች ዋጋ “ከፍተኛ” እንዲሆን ማድረጉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “የዛሬ አራት ዓመት ያስተካከልነው፤ ለአስር ዓመታት የነበረውን ጉድለት ነው። እሱን አስተካክለን normal ሆነ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ የመጣው [የዋጋ ንረት] ግን የአስር ዓመቱን የሚያስንቅ ሆነ። ይሄ ሊገመት የሚችል አይደለም። ተገምቶም ደግሞ ህብረተሰቡ ላይ መጫን አይቻልም” ሲሉ ይህን ታሳቢ ያደረገ የዋጋ ጭማሪ ያልተደረገበትን ምክንያት አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያለበት የፋይናንስ ውስንነት፤ በ2022 ዓ.ም በሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የተያዘውን እቅድ ጥያቄ ውስጥ እንደከተተውም በዛሬው ውይይት ላይ ተነስቷል። ባለፉት 12 ዓመታት በአማካይ 423 ከተሞች በየዓመቱ ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ መደረጉን አቶ እሱባለው ጠቅሰዋል፡፡
አገልግሎቱ የገጠር ከተሞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ያዘጋጀው በ1999 ዓ.ም ሲሆን በጊዜው 16,652 ከተሞች እንዳሉ ታሳቢ ተደርጎ ነበር፡፡ ይህ እቅድ በ15 ዓመታት ቆይታው ኤሌክትሪክ ማቅረብ የቻለው ስምንት ሺህ ለማይሞሉ የገጠር ከተሞች ነው፡፡ እስከአሁን 8,679 የገጠር ከተሞች ኤሌክትሪክ እንዳላገኙ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ተቋሙ ባለፉት ዓመታት የነበረውን አፈጻጸም በመጥቀስ በዚህ አካሄድ በሁሉም የገጠር ከተሞች ኤሌክትሪክ ለማዳረስ 20 ዓመት እንደሚፈጅ አስረድተዋል፡፡

ይህንን “ደካማ አፈጻጸም” በማሻሻል በሰባት ዓመት ውስጥ በሀገሪቱ በሙሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማቅረብ፤ በየዓመቱ 90 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። “ይህ ዘርፍ በዓመት 90 ቢሊዮን ብር inject የሚደረግ ፋይናንስ ከሌለው በ2030 ኤሌክትሪክ ለሁሉም ዜጎች ማዳረስ የሚለው አይሳካም” ሲሉ ሀገሪቱ በሰባት ዓመት ውስጥ ልትደርስበት ያስቀመጠችውን ግብ ዕጣ ፈንታ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበጀት ውስንነት ውስጥ ሆኖ እየተተገበረ ያለውን የሶስት ዓመት እቅድ ለማሳካት የሀገር ውስጥ ባንኮችን ጨምሮ ከሌሎች አካላት ብድር የማፈላለግ እቅድ እንዳለው አቶ እሱባለው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የተቋሙ የዲስትሪውቢሽን ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ብዙወርቅ፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ገቢ ያሳድጋል የተባለውን የታሪፍ ማሻሻያ ለመተግበር ጥናት እየተደረገ መሆኑን አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)