የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ የመውጣት ሂደት “ዘገምተኛ ሆኗል” ሲሉ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክትል ኮሚሽነር ተቹ 

የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማብቃት በፕሪቶሪያ በተፈረመው በቋሚነት ግጭት የማቆም ስምምነት መሰረት የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ መውጣት ቢጀምሩም፤ ሂደቱ “ዘገምተኛ ሆኗል” ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ምክትል ኮሚሽነር ናዳል አል-ናሺፍ ተቹ። የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ የመውጣት ሂደት ባለመጠናቀቁ፤ ክትትል እየተደረገ ሪፖርት ሊቀርብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዮርዳኖሳዊቷ ዲፕሎማት ጉዳዩን ያነሱት በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ነው። ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው በኤርትራ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ላይ የመከረ ሲሆን፤ ምክትል ኮሚሽነሯን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል።

“በኤርትራ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ አሳሳቢ ነው። ምንም መሻሻል አላሳየም” ያሉት ናዳል አል-ናሺፍ፤ ለዚህም ማሳያ ያሏቸውን ጉዳዮች ዘርዝረው አቅርበዋል። ቢሯቸው በኤርትራ ስቅየት፣ የጅምላ እስር እና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ እንደሚፈጸሙ ተዓማኒ ሪፖርቶች እየደረሱት እንደሚገኙ ምክትል ኮሚሽነሯ ጠቅሰዋል። ምክትል ኮሚሽነሯ “የትግራይ ግጭትን ተከትሎ ተባብሷል” ባሉት የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት፤ ኤርትራውያን ላልተወሰነ ጊዜ የማገልገል ግዴታ እንደተጣለባቸው ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል።

“ኤርትራ ላለፉም ሆነ አሁንም እየተፈጸሙ ለሚገኙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ይህ ነው የሚባል እርምጃ አልወሰደችም” ሲሉ የወቀሱት ናዳል አል-ናሺፍ፤ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለክሳቸው ማጠናከሪያነት አንስተዋል። የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት በኢትዮጵያ ለፈጸማቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች እና ሰብዓዊ ሕግ ጥሰቶች፤ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስርዓቶችን በመዘርጋት ረገድ ሀገሪቱ “አንዳች እርምጃ አልወሰደችም” ሲሉ ወቅሰዋል።

የሀገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት የሰብዓዊ ጥሰቶች መፈጸማቸውን፤ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ባከናወኑት ምርመራ እንደደረሱበት ያስታወሱት ናዳል አል-ናሺፍ፤ ሆኖም ኤርትራ ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በጥምረት ያከወኑትን ምርመራ እንደማትቀበል ገልጸዋል። ኤርትራ “በመከላከያ ሠራዊቷ ውስጥ የሚገኙ አጥፊዎች ያለ ተጠያቂነት እርምጃ እንዲወስዱ ፈቅዳለች” ሲሉም ተደምጠዋል።

የኤርትራ የፍትሕ ስርዓት አጥፊዎችን ተጠያቂ ያደርጋል የሚል ተስፋ እንደሌላቸው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ምክትል ኮሚሽነር በዛሬው የምክር ቤት ውሎ ተናግረዋል። በዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ፤ ተመድ በኤርትራ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ያለበትን ሁኔታ እንዲከታተሉ የሾማቸው ሱዳናዊው ሞሐመድ አብድሰላም ባብከር እና የሰብዓዊ መብቶች አራማጇ ቫኔሳ ስዩም ተጨማሪ ማብራሪያዎችን አቅርበዋል። 

አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ፈረንሳይን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን ሀገራትን የወከሉ የምክር ቤቱ አባላት፤ ከኮሚሽነሯ እና ተመድ በኤርትራ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታን ለመመርመር ከሾማቸው ዲፕሎማት የተስማማ አስተያየት ሰጥተዋል። እነዚህ የምክር ቤት አባል ሀገራት፤ ኤርትራ ወታደሮቿን ጠቅልላ ከኢትዮጵያ ግዛት እንድታስወጣ ጥሪ አቅርበዋል። የኤርትራ መንግስት፤ ወታደሮቹ “በሰሜን ኢትዮጵያ ፈጽመዋቸዋል” የሚባሉ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች እና የሰብዓዊ ሕግ ጥሰቶች እንዲመረምርም አሳስበዋል።

በኤርትራ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ባተኮረው ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ ተደጋግሞ መነሳቱ ግን ተቃውሞ ገጥሞታል። በምክር ቤቱ ኢትዮጵያን የወከሉት ዲፕሎማት፤ በመድረኩ ማብራሪያ ያቀረቡ ባለሙያዎች እና አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ያነሷቸው ርዕሰ ጉዳዮች “ከኤርትራ የራቁ” መሆናቸው “በጣም ያሳዝናል” ሲሉ ተደምጠዋል። የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፤ ተመድ በኤርትራ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ላይ ባስተላለፈው የውሳኔ ሐሳብ ውስጥ የሚካተት እንዳልሆነ የጠቀሱት እኚሁ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት፤ “ሁሉም ተናጋሪዎች የምክር ቤቱን አሰራር እንዲያከብሩ፤ በጥብቅ እንዲከተሉ ይጠበቃል” ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ጄኔቫ በሚገኘው የተመድ ጽህፈት ቤት የኤርትራ ቋሚ ተልዕኮ አንደኛ ጸሀፊ አደም ኦስማን ኢድሪስ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ተያይዞ ከምክር ቤቱ ለተነሱት ጉዳዮች በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ማተኮርን መርጠዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የውሳኔ ሃሳብ የሚቋቋሙ ልዩ ልዑኮች ዓላማቸው “በኤርትራ የሚታዩ የሰብዓዊ መብት ጉድለቶችን የሚታረሙበት ዘዴ መጠቆም ሆኖ አያውቅም” ሲሉ የከሰሱት ዲፕሎማቱ፤ ዓላማቸው “ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን የሚያራምዱ መድረኮችን መፍጠር ነው” ሲሉ ነቅፈዋል።

ሞሐመድ አብድሰላም ባብከር ባለፈው ዓመት ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፤ ኤርትራ 5,000 ሶማሊያውያንን በትግራይ ጦርነት አሳትፋለች የሚል “የሐሰት ክስ” ማቅረባቸውን ኤርትራዊው ዲፕሎማት ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል። ኤርትራ ሪፖርቱ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ፤ ልዩ ልዑኩም ባሳዩት “ተቀባይነት የሌለው የፖለቲካ አድሎ እና ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣታቸው” እንዲባረሩ ጠይቃ እንደነበር አስታውሰዋል።

የዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ፤ ተሳታፊዎችን ለሁለት ከፍሎ ያወዛገበ ሆኖ ተጠናቅቋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶችን ለመከታተል የሚሰጣቸው ኃላፊነቶች “በሉዓላዊ አገራት ጣልቃ መግባት ነው” የሚሉ ትችቶች ቀርበዋል። ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ እና ቬንዝዌላን የመሳሰሉ ሀገራት በአንጻሩ፤ ኤርትራ “የሰብዓዊ መብቶችን በማስተዋወቅ እና በመጠበቅ ረገድ አሳይታለች” ያሉትን መሻሻል እንደሚያደንቁ በዚሁ ስብሰባ ላይ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)