በአማኑኤል ይልቃል
የአማራ ክልል “እየተረበሸ” እና “እረፍት እያጣ” ያለው ከክልሉ ውጪ በሚፈጠር ችግር መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ። ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የአማራ ክልል ተወላጆችን፤ ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመመለስ ስምምነት ላይ መደረሱንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
ዶ/ር ይልቃል ይህንን የተናገሩት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማራ ክልልን ከወከሉ ተመራጮች እና ከክልሉ ምክር ቤት አባላት ጋር ከትላንት በስቲያ እሁድ የካቲት 26፤ 2015 በባህር ዳር ከተማ ባደረጉት ውይይት ነው። በዚሁ ውይይት፤ ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ተወያይተው መመለሳቸው የተነገረላቸው የሁለቱ ምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎችን ለርዕሰ መስተዳድሩ አቅርበዋል።
የምክር ቤት አባላቱ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች ውስጥ የመሰረተ ልማት ዝርጋታን የተመለከቱት በዛ ብለው ተስተውለዋል። ከጸጥታ መደፍረስ፣ ከመፈናቀል እና “ከማንነት ጥቃት” ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ያነሱ የሁለቱ ምክር ቤት አባላት ደግሞ ጠንከር ባሉ ቃላት ጥያቄዎቻቸውን ሰንዝረዋል። በተመራጮቹ ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ የአማራ ክልል አመራሮችን “የትግል አቅጣጫ” እና “የአንድነት ሁኔታ” ያጠየቁም ነበሩበት።
ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ርዕሰ መስተዳድሩ ዶ/ር ይልቃል፤ “የአማራ ክልል የጸጥታ ስጋት አለበት” በሚል የተነሳውን ሀሳብ እንደሚቀበሉት ተናግረዋል። በሀገር ደረጃም “እዚህም እዚያም የሚታዩ ችግሮች እንዳሉ” የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአማራ ክልል ውስጥ ችግር እየተፈጠረ ያለው ግን “ከክልሉ ውጪ” ባሉ ምክንያቶች መሆኑን አስረድተዋል። በሌሎች ክልሎች ውስጥ የሚፈጠረው ችግር ወደ አማራ ክልል ተሻግሮ “የክልሉ ችግር” ሲሆን መታየቱንም ለተመራጮቹ ተናግረዋል።
“ከክልሉ ውጪ በሚፈጠር ችግር ነው አማራ ክልል እየተረበሸ፣ እረፍት እያጣ ያለው። እናም የህዝብ ቅሬታ እየሰፋ የመጣው። ይሄ የአማራ ክልልን ከሌሎች ክልሎች የተለየ ያደርገዋል” ሲሉ ዶ/ር ይልቃል በክልሉ ያለው ችግር የተለየ ቅርጽ እንዳለው አመልክተዋል። “ ‘ይሄ ለምንድነው የሚሆነው?’ የሚለውን በደንብ ማየት ያለብን ይመስለኛል። ይሄ የሚሆነው ደግሞ አማራ ክልል ብቻ ነው። ያንን መረዳት አለብን” ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ በአጽንኦት ተናግረዋል።
በዶ/ር ይልቃል ማብራሪያ የተሰጠበት ሌላኛው ጉዳይ፤ ወደ አዲስ አበባ በሚጓዙ የአማራ ክልል ነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰተው “የመንገድ መዘጋት” ችግር ነው። የዜጎች በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት “ህገ መንግስታዊ መብት” መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህ መብት “በየትኛውም መመዘኛ” መታገድ የሌለበት መሆኑን ገልጸዋል።
“እንደውም ህገ መንግስቱ [ዜጎች] በመረጡት ቦታ መኖር ይችላሉ ነው የሚለው። ስለዚህ ይህንን ማስከበር አለብን ብዬ አስባለሁ። ሱዳን በነጻ እየገባን፤ አንዳንድ ሀገሮች ያለ ቪዛ በቀጥታ እየገባን፤ [ዜጎች] በሀገራቸው ‘እዚህ ቁሙ’ ሊባሉ አይገባም። ከዚህ በላይ ነገሩን ያወሳሰበው የአገልግሎት አሰጣጡ ወይም ደግሞ የአፈጻጸም ስርዓቱ፤ ትንሽ እንዳየነው ሰብዓዊ መብትን የሚጥስ ጉዳይ ስለሆነ [ነው]” ሲሉ ችግሩ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ነዋሪዎች ወደ አዲስ አበባ ለመግባት መከልከላቸውን አስመልክቶ፤ ከኦሮሚያ ክልል አመራሮች ጋር ውይይት እንደተደረገም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል። በዚሁ ውይይት ላይ የጸጥታ ስጋት በምክንያትነት መነሳቱን የጠቆሙት ዶ/ር ይልቃል፤ “አማራ ክልልም ቢሆን አድማን አይደግፍም። ወንጀልን አይደግፍም። ሌላውም በሀገር ደረጃ እንደዛው ነው። የአዲስ አበባ ጉዳይ የሁላችን ጉዳይ ነው። ሰላም እና ደህንነት እንዲከበር እዛም እንፈልጋለን” ሲሉ የክልሉን መንግስት አቋም ለተወያዮቹ አስረድተዋል።
የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል አመራሮች ባደረጉት ውይይት ላይ “ወደፊት አሰራሩ በምን አግባብ ይሁን” የሚለውን የተመለከተ “አቅጣጫ” መቀመጡን ዶ/ር ይልቃል ጠቅሰዋል። “ሌላ ችግር መጥቶ” ተመሳሳይ ጉዳይ የሚፈጠር ከሆነ፤ አሰራሩ “ስርዓት እንደሚኖረው” ያላቸውን ተስፋም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከኦሮሚያ ክልል አመራሮች ጋር ስምምነት እንደተደረሰበት የገለጹት ሌላኛው ጉዳይ፤ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮችን የሚመለከት ነው። በተለያዩ አካባቢዎች ችግሮች ሲፈጠሩ ተፈናቃዮች ወደ አማራ ክልል እንደሚሄዱ ያስረዱት ዶ/ር ይልቃል፤ “እንደዚያ ተሁኖ ይቻላል ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል። የአካባቢ አስተዳደሮች “ዜጎችን ያለ ልዩነት” በማስተዳደር ምላሽ መስጠት ነበረባቸው ሲሉም ተደምጠዋል።
ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የሁለቱ ክልል አመራሮች ባደረጉት ውይይት፤ የኦሮሚያ ክልል አመራሮች “ለተፈናቃዮቹ” ኃላፊነት እንደሚወስዱ መናገራቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል። የኦሮሚያ ክልል አመራሮች “[ተፈናቃዮቹ] የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ናቸው። የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ከሆኑ ደግሞ በግንባር ቀደም ኃላፊነት የሚወስደው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ነው። ስለዚህ የእኛው ነዋሪዎች ስለሆኑ የሚመለከተን እኛን ነው” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ዶ/ር ይልቃል ለሁለቱ ምክር ቤት ተወካዮቹ ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል አመራሮች “አሁን የጸጥታ ችግር ስላለ ነው እንጂ፤ አጠቃላይ ተፈናቃይን እንደሚወስዱ” ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል። “የጸጥታ ችግር እስከሚስተካከል ኦሮሚያ ላይ በካምፕ ኑረው፤ በኋላ የሸኔ እና የሌላው ነገር ጉዳዩ ሲያልቅ ወደዚያ እንደሚመልሷቸው ነው የተስማማነው። በዚያ መንፈስ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉም የሁለቱ ክልል አመራሮች የተስማሙበትን የመፍትሔ ሃሳብ ዶ/ር ይልቃል ይፋ አድርገዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)