ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከቀረበበት ክስ በፍርድ ቤት በነጻ ተሰናበተ

በሃሚድ አወል

የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ከተከሰሰበት የሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ወንጀል በነጻ ተሰናበተ። ጋዜጠኛው በነጻ የተሰናበተበትን ፍርድ የሰጠው፤  ዛሬ ረቡዕ የካቲት 29፤ 2015 የዋለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት ነው። 

የችሎቱን ፍርድ በንባብ ያሰሙት የግራ ዳኛ “ተከሳሹ የቀረበበትን ወንጀል በመከላከሉ በነጻ ሊሰናበት ይገባል በማለት በሙሉ ድምጽ ፍርድ ሰጥተናል” ብለዋል። ጋዜጠኛ ተመስገን ተከስሶበት የነበረው የወንጀል ተግባር “መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት የወንጀል ተግባር” ፈፅሟል የሚል ነበር። 

ነገር ግን ችሎቱ ባለፈው ጥቅምት ወር ድንጋጌውን በመቀየር “የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር” በወጣው አዋጅ እንዲከላከል መወሰኑ ይታወሳል። ፍርድ ቤቱ በወቅቱ ድንጋጌውን ሲቀይር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቀርበውበት ከነበሩት ሌሎች ሁለት ክሶች በነጻ አሰናብቶታል። 

ተመስገን ከአራት ወራት በፊት ነጻ የተባለባቸው ሁለት ክሶች “ወታደራዊ ምስጢርን መግለጽ በተመለከተ በወንጀል ህጉ የተደነገገውን አንቀጽ ተላልፏል” እንዲሁም “የሀሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ አሰራጭቷል” የሚሉ ናቸው። በጋዜጠኛው ላይ የቀረቡ ሁለቱ ክሶች ውድቅ ከተደረጉ እና የአንደኛው ክስ ድንጋጌ ከተቀየረ በኋላ፤ ተመስገን በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተፈትቶ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ ሲከታተል ቆይቷል።

ተመስገን በፍርድ ቤት እንዲከላከል የተበየነበት ሶስተኛ ክስ፤ በ“ፍትሕ” መጽሔት ከወጡ ሁለት ጽሁፎቹ ጋር የተያያዘ ነው። የመጀመሪያ ጽሁፍ “ወታደራዊ ጉዳዮች” በሚል ርዕስ ስር በ2012 ዓ.ም በመጽሔቱ የታተመ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “መከላከያ ተቋማዊ ወይስ ኔትዎርክ” በሚል ርዕስ ስር በ2014 ዓ.ም በ“ፍትሕ” መጽሔት የወጣ ነው። 

ጋዜጠኛው ባለፈው ዓመት ለንባብ ያበቃው ጹሁፍ፤ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር የተሰጠውን ሽልማት እና ማዕረግ የተመለከተ ነበር። ተመስገን በዚህ ጽሁፉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሽልማት እና ማዕረግ አሰጣጥ፤ “የብሔር የበላይነት የተጫነው ነው” ሲል ተችቷል።

ይህን የጋዜጠኛውን ጹሁፎች በማስረጃነት ያቀረበው የፌደራል ዐቃቤ ህግ፤ “የመከላከያ ሰራዊት እንዲከፋፈል” እና “ህዝቡ ከመከላከያ ሰራዊት እንዲርቅ” ተመስገን “ሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር አሰራጭቷል” ሲል ክስ አቅርቦበታል። የተከሳሹ ጠበቆች ከሶስት ወራት ገደማ በፊት ባቀረቡት የክርክር ማቆሚያ ንግግር፤ ይህ የጋዜጠኛው ጽሁፍ “የጥላቻ ባህሪ የሌለው” መሆኑን በመግለጽ በነጻ እንዲሰናበት ጠይቀው ነበር።

ጠበቆቹ አክለውም የደንበኛቸው ጽሁፍ “የጥላቻ ባህሪ አለው” ከተባለ “ጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር” በወጣው አዋጅ መሰረት “በልዩ ሁኔታ ታይቶ ውድቅ ሊደረግ ይገባል” ሲሉም ጠይቀው ነበር። ጠበቆቹ የጠቀሱት አዋጅ “ልዩ ሁኔታ” በሚለው የአዋጁ ክፍል ስር፤ “አንድ የጥላቻ ንግግር እንደ ጥላቻ ንግግር ወይም እንደ ሐሰት መረጃ ተወስዶ ማስራጨት የማይከለከለው” በምን አግባብ እንደሆነ ደንግጓል። 

ድንጋጌው አንድ ንግግር “የዜና ዘገባ፣ ትንታኔ ወይም የፖለቲካ ትችት አካል እንደሆነ”፤ እንደ ጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ እንደማይወሰድ ያስቀምጣል። የዛሬው ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት ውሳኔውን ያነቡበት ዳኛ “ተከሳሽ ሂሳዊ የፖለቲካ ትንታኔ ያደረገ መሆኑን [ችሎቱ] ተገንዝቧል። ሂሳዊ መሆኑን ከጽሁፉ ይዘት እና ተከሳሽ ካያያዛቸው የመከላከያ ማስረጃዎች መገንዘብ ይቻላል” ብለዋል። 

ዳኛው አክለውም “ችሎቱ ለክሱ መነሻ የሆነው ጽሁፍ በልዩ ሁኔታ የሚታለፍ ሆኖ አግኝቶታል። ህትመቱን የተጠቀመውም የጥላቻ መረጃ ለማሰራጨት ሳይሆን ለዜና ዘገባ መሆኑን ተገንዝበናል” ሲሉ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለችሎቱ ታዳሚዎች አንብበዋል። ይህን ተከትሎም ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከቀረበበት የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃን ማስራጨት ወንጀል “በነጻ ሊሰናበት ይገባል” ሲል ችሎቱ በሙሉ ድምጽ በይኗል። 

ተመስገን ከቀረበበት ክስ በነጻ መሰናበቱን ተከትሎ፤ ለዋስትና ያስያዘው ገንዘብ እንዲመለስለት ፍርድ ቤቱ አዝዟል። የዛሬውን የችሎት ውሎ፤ ጋዜጠኛው ከሁለት ጠበቆቹ ጋር በአካል ተገኝቶ ተከታትሏል። የዛሬውን የችሎት ውሎ የታደሙ የጋዜጠኛው ወዳጆቹ እና ቤተሰቦቹ፤ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ደስታቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)