በሃሚድ አወል
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ከአስር ቀናት በፊት ያቋቋመው “የምስራቅ ቦረና ዞን” ስያሜ እንደሚለወጥ፤ በክልሉ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ቃል እንደተገባላቸው የጉጂ አባ ገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው፤ “ይኼ ገና በውስጥ ያወራነው ጉዳይ ነው። ሲያልቅ ይፋ እናደርጋለን ” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል አዲስ ካደራጀው “የምስራቅ ቦረና ዞን” ጋር በተያያዘ፤ በጉጂ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ላለፈው አንድ ሳምንት ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ ቆይተዋል። “የምስራቅ ቦረና ዞን” የተመሰረተው፤ በክልሉ ከሚገኙ ሶስት ነባር ዞኖች በተውጣጡ አስር ወረዳዎች እና ከተሞች ነው።
ለኦሮሚያ ክልል 21ኛ የሆነውን ይህን አዲስ ዞን የመሰረቱት ወረዳዎች እና ከተሞች የተውጣጡት ከቦረና፣ ጉጂ እና ባሌ ዞኖች መሆናቸው ከአስር ቀናት በፊት በተላለፈ ውሳኔ ይፋ ተደርጎ ነበር። ለተቃውሞ መቀስቀስ ምክንያት በሆነው በዚህ የአደረጃጀት ለውጥ ላይ ለመወያየት፤ የጉጂ አባ ገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ከኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ዛሬ ሐሙስ የካቲት 30፤ 2015 በአዲስ አበባ ከተማ ተገናኝተዋል።

በዛሬው ውይይት፤ የጉጂ አባገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ውይይቱን የመሩት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ቅሬታውን ቁጭ ብለን አዳምጠናል። ተነጋግረናል” ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ “ባላለቀ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ” መስጠት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
ከውይይቱ በኋላ ዛሬ ከሰዓት መግለጫ የሰጡት የጉጂ አባ ገዳዎች በበኩላቸው፤ በአደረጃጀት ለውጡ ያላቸውን ቅሬታ ካቀረቡ በኋላ ስያሜው እንደሚለወጥ በክልሉ መንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች ቃል እንደተገባላቸው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። የጉጂ አባ ገዳዎች የኦሮሚያ ክልል ውሳኔን የተቃወሙት “የጉጂ ዞን ዋና ከተማ የነበረችው ነጌሌ ቦረና፤ የአዲሱ ምስራቅ ቦረና ዞን ዋና ከተማ እንድትሆን በመደረጉ” መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲሱ ዞን ስያሜ “ምስራቅ ቦረና” መባሉ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ጨምረው የገለጹት አባ ገዳዎቹ፤ የክልሉን ውሳኔ “ኢ- ፍትሃዊ እና ህዝብን ያላማከለ” ሲሉ ተችተዋል። በኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት፤ ነባሩ የጉጂ ዞን ዋና ከተማውን ከነጌሌ ቦረና ወደ አዶላ ሬዴ መቀየር ይጠበቅበታል። አዲሱን የመዋቅር ለውጥ በተመለከተ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ፤ “አደረጃጀት መቀየር፤ ማጠፍ፤ ማካፈል ህገ መንግስታዊ እና የመንግስት ጉዳይ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የኦሮሚያ ክልል አዲስ ዞን ማደራጀት ያስፈለገው፤ “በድንበር አካባቢ ያለውን ህገ ወጥነትን ለመቅረፍ፣ በድንበር አካባቢ ከአጎራባች ክልሎች ጋር የሚከሰተውን የሰላም ሁኔታን ለመፍታት እንዲሁም ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ለማቅረብ ውጤታማ የሆነ አደረጃጃትና አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ” መሆኑን ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።
የክልሉ ምክር ቤት ከአስር ቀን በፊት ባሳለፈው ውሳኔ፤ የምስራቅ ቦረና ዞንን ከማደራጀት በተጨማሪ “የመልማት መልካም ዕድል ያላቸው” ከተሞች ተጠሪነት በቀጥታ ለክልሉ መንግስት እንዲሆን ወስኗል። ተጠሪነታቸው ለክልሉ መንግስት ከተደረጉት ዘጠኝ ከተሞች መካከል መቱ፣ አጋሮ፣ ቡሌ ሆራ፣ ሞያሌ እና ሻኪሶ ይገኙበታል። የከተሞቹ ተጠሪነት በቀጥታ ለክልሉ መንግስት የሆነው “በአካባቢያቸው ያሉትን ከተሞችና ወረዳዎችን ልማት እንዲያፋጥኑ እና የአመራሩን ትኩረት በቅርበት እንዲያገኙ” መሆኑን ክልሉ በወቅቱ ገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ውሳኔ ያሳለፈበት ሌላኛው ጉዳይ፤ “ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ከተሞችን አንድ ላይ ቀላቅሎ” እንደ አዲስ ማደራጀት ነው። በዚህም መሰረት አስራ ስድስት የተለያዩ ከተሞች በአንድ ላይ ተሰባስበው፤ በስድስት የተለያዩ ከተሞች ስር እንዲደራጁ ተደርገዋል። ውሳኔውን ተከትሎ፤ የዱከም ከተማ ከሌሎች ማዘጋጃ ቤታዊ ከተሞች ጋር በመሆኑ በቢሾፍቱ ከተማ ስር እንድትሆን ተደርጓል።

ሀረማያ፣ አወዳይ እና አዴሌ ከተሞችን አንድ ላይ በማድረግ “ማያ” የተሰኘ አዲስ ከተማ መመስረቱ በክልሉ ምክር ቤት ውሳኔ ተገልጿል። አዳማ ከተማ በበኩሉ ወንጂ ከተማን በመያዝ በስድስት ክፍለ ከተሞች እና በ19 ወረዳዎች ተደራጅቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)