የሶማሌ ክልል መንግስት፤ የክልሉ ልዩ ኃይሎች “በሶማሌላንድ ግዛት በተቀሰቀሰው ግጭት እየተሳተፉ ነው” መባሉን አስተባበለ  

በአማኑኤል ይልቃል

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይሎች የራስ ገዟን ሶማሌላንድ ድንበር አልፈው፤ በሶሎ ግዛት ላሳኖድ ከተማ “ጦርነት ውስጥ እየተሳተፉ ነው” መባሉን የክልሉ መንግስት አስተባበለ። የሶማሌላንድ አመራሮች ሁለቱን “ወንድማማች ህዝቦች ሊነጥሉ የሚችሉ ቃላት እና ድርጊቶችን” ከመጠቀም እንዲቆጠቡም የሶማሌ ክልል መንግስት አሳስቧል። 

የሶማሌ ክልል መንግስት ይህንን ማስተባበያ እና ማሳሰቢያ የሰጠው፤ በፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የሚመራው የሶማሌላንድ ካቢኔ ትላንት ሐሙስ የካቲት 30፤ 2015 ካደረገው ስብሰባ በኋላ ያቀረበው ክስን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ነው። የራስ ገዟ አስተዳደር ካቢኔ በዚሁ ስብሰባው ግጭት እየተካሄደባት ባለው ላሳኖድ ከተማ፤ “የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኃይሎች፣ የሶማሊያ እና የፑንትላንድ ወታደሮች ይገኛሉ” ሲል ከስሷል።  

ካቢኔው “የሶማሌ ላንድን ዓለም አቀፋዊ ድንበር አልፈው የገቡ” ሲል የገለጻቸው እነዚህ ኃይሎች፤ ከአካባቢው እንዲወጡም አሳስቧል። ይህ ክስ በቀረበ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ መግለጫ ያወጣው የሶማሌ ክልል መንግስት በበኩሉ “በላሳኖድ ከተማ የሚካሄደው ጦርነት አካል የሆነ አንድም የሶማሌ ክልል ኃይል አባል የለም” ሲል ክሱን አጣጥሎታል። በሶማሌ ላንድ ካቢኔ የወጣውን መግለጫ “ኃላፊነት የጎደለው ውንጀላ” ሲልም አውግዞታል።

የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ረሺድ “እኛ የሌላ ሀገር ፖለቲካ [ውስጥ] እጅ የምናስገባበት ምንም አይነት ተልዕኮ የለንም፤ እሳቤውም የለንም። ስለዚህ ያወጡት መግለጫ እኛን የማይመለከተን ነው” ሲሉ የክልሉን መንግስት አቋም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። “በፕሬዝዳንቱ የሚመራው የሶማሌላንድ ካቢኔ ላይ ነው እንደ አጀንዳ ተነስቶ ይህን የተናገሩት። ይህንን ማለታቸው ደግሞ ቸኩለዋል” ሲሉ ወቅሰዋል። 

የክልሉ መንግስት ባወጣው በዚሁ መግለጫው፤ ከሶማሌላንድ አመራሮች “በተደጋጋሚ” ለሚቀርብበት “ክስ እና ውንጀላ” ምላሽ ባለመስጠት ጉዳዩን “በትዕግስት” ሲያልፍ መቆየቱን ጠቅሷል። የራስ ገዟ አስተዳደር በሶሎ ግዛት ውስጥ ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ የሚነሱበትን “ውስጣዊ እና ውጫዊ ጥያቄዎች” ለማስተናገድ ሲል “የሌለ ጠላት ላይ እየጠቆመ ነው” ሲል ክልሉ ለወቀሳው ምላሽ ሰጥቷል።

የሶማሌ ክልል መንግስት በትላንቱ መግለጫው “የሶማሌላንድ አስተዳደር፤ የሶማሌ ክልል እና የሶማሌ ላንድ ህዝቦችን ሊያራርቁ ከሚችሉ ቃላት እና ድርጊቶች እንዲቆጠብ በድጋሚ እንጠይቃለን” ሲል አሳስቧል። ይህንን ሀሳብ የሚያጠናክሩት የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ አብዱልቃድር በበኩላቸው፤ “ያላቸው ችግር በቀጣናው እንዳይባባስ ስጋት አለን። ጎረቤት በመሆናችን የእነሱ ችግር የእኛ ችግር ነው” የሚሉት የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው፤ የሶማሌ ክልል መንግስት በጉዳዩ ላይ ያለው አቋም “ውስጣዊ ችግራቸውን በራሳቸው ይፍቱ” የሚል እንደሆነም አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)