የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት፤ “ሰላም ለማስፈን እና የሽግግር ፍትሕን ለማረጋገጥ በፕሪቶሪያ በተፈረመው በቋሚነት ግጭት የማቆም ስምምነት አተገባበር” ላይ እንደሚወያዩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ። ብሊንከን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በዛሬው ዕለት ባወጡት መግለጫ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፤ ብሊንከን ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ያስታወቁት ትላንት ሐሙስ ቢሆንም የጉብኝታቸው ትክክለኛ ጊዜ አልተገለጸም ነበር። ብሊንከን ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚነጋገሩ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ብሊንከን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከመንግስት ባለስልጣናት በተጨማሪ በሰብዓዊ ዕርዳታ ስርጭት፣ በምግብ ዋስትና እና በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ከሰብዓዊ ድርጅቶች እና ከከሲቪክ ተቋማት ጋር ይነጋገራሉ።
አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሰበብ ከኢትዮጵያ ት ጋር ያላት ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል። የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል በቋሚነት ግጭት የማቆም ስምምነት እንዲፈረም በማደራደር ቁልፍ ሚና ከነበራቸው የአፍሪካ ህብረት፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ብሊንከን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ጋር ይገናኛሉ።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሚቀጥለው ሳምንት የአፍሪካ ጉዟቸው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ኒጀርን ይጎበኛሉ። በሁለቱ የአፍሪካ አገሮች የሚያደርጉት ጉብኝት ከመጋቢት 5 እስከ መጋቢት 8፤ 2015 የሚቆይ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)