የአማራ ክልል መንግስት ከ“አገው ሸንጎ” ታጣቂ ቡድን ጋር የሰላም ንግግር እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

በአማኑኤል ይልቃል

የአማራ ክልል መንግስት፤ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሚንቀሳቀሰው የ“አገው ሸንጎ” ታጣቂ ቡድን ጋር የሰላም ንግግር እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። በቅርቡ መጀመሩ በተነገረው በዚህ ንግግር ከስምምነት ላይ ለመድረስ፤ ታጣቂ ቡድኑ “ቅድመ ሁኔታዎችን” ማስቀመጡ ተገልጿል።

የአማራ ክልል መንግስት ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ንግግር እያደረገ መሆኑን ያስታወቀው፤ ላለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ መጋቢት 1፤ 2015 በተጠናቀቀው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ነው። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ይህንን የገለጹት፤ የክልሉን የሰላም ሁኔታ አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ መሆኑን የአማራ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት የ“አገው ሸንጎ” ሲል የሚጠራው ታጣቂ ቡድን፤ “የአገው ብሔራዊ ሸንጎ” የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በነበሩ ግለሰቦች የተመሰረተ ነው። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀሰው የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ሊቀመንበር አቶ አላምረው ይርዳው፤ የቀድሞው የፓርቲያቸው አባላት የነበሩ ግለሰቦች “የአገው ዴሞክራሲያው ንቅናቄ” እና “የአገው ነጻ አውጪ ግንባር” የሚሉ ስያሜዎችን ይዘው ወደ ትጥቅ ትግል መግባታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

የ“አገው ሸንጎ” በሚል መጠሪያ የሚታወቁት እነዚህ ታጣቂዎች፤ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መነሳቱን ተከትሎ “ከህወሓት ጋር ሆነው ወደ ውጊያ” እንደገቡ የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አስረድተዋል። ታጣቂዎቹ በአሁኑ ወቅት ከአማራ ክልል መንግስት ቁጥጥር ስር ውጭ በሆኑት፤ ጻግብጂ እና አበርገሌ በተባሉ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሁለት ወረዳዎች ውስጥ “በስፋት” እንደሚንቀሳቀሱም አክለዋል። 

የእነዚህ ሁለት ወረዳዎች ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ፤ ዛሬ በተጠናቀቀው የአማራ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር አቶ ግዛቸው አመልክተዋል። ለጥያቄዎቹ ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል፤ ወረዳዎቹ “ነጻ ላለመውጣታቸው” አንዱ ምክንያት “በዚያ አካባቢ ከህወሓት ጋር በመሆን ሲንቀሳቀስ የነበረው የአገው ሸንጎ ቡድን” እንደሆነ መግለጻቸውን የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል። 

በሁለቱ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ወረዳዎች፤ ከ“አገው ሸንጎ” ታጣቂ ቡድን በተጨማሪ “በፊት አመራር የነበሩ የታጣቂ የህወሓት ኃይሎች እንዳሉ” በመረጃዎች መረጋገጡን አቶ ግዛቸው ተናግረዋል። የእነዚህ ሁለት ወረዳዎች ነዋሪዎች “በችግር ውስጥ ናቸው” ያሉት ኃላፊው፤ ስፍራውን የተቆጣጠሩት ታጣቂዎች የአካባቢው ነዋሪዎችን የያዙበት ሁኔታ “ልክ አይደለም” የሚል እምነት በክልሉ መንግስት በኩል እንዳለ ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል መንግስት በጻግብጂ እና አበርገሌ ወረዳዎች ያለውን ችግር ለመፍታት፤ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች ጋር ሁለት ጊዜ ንግግር ማድረጉን የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። በእነዚሁ ውይይቶች ወቅት፤ በታጣቂ ቡድኑ በኩል “ጉዳዩን በሰላም የመፍታት ፍላጎት” መታየቱን ኃላፊው አመልክተዋል።

“በዚህ ደረጃ ሲታይ በእነሱ በኩልም ይሁንታ አለ። እየመከሩ የሚመጡበት ሁኔታም እንዳለ ተስፋ እናደርጋለን። ያለው ሁኔታ ምልክቱ በጣም ጥሩ ነው። እንግዲህ በቀጣይ ምን ይገጥመዋል? የሚለው በሂደት እያየን ደግሞ ውይይቶች ሲደረጉ የምንገልጽ ነው የሚሆነው” ሲሉ አቶ ግዛቸው የውይይቱን የእስካሁን ሂደት አብራርተዋል።

የአማራ ክልል መንግስት ጅምሩን አጠናክሮ “በከፍተኛ ደረጃ ያሉ አመራሮች እና የጸጥታ አካላት ጭምር ተሳትፈውበት” ውይይቱን የማስቀጠል ፍላጎት እንዳለውም ገልጸዋል። የእስካሁኖቹ ንግግሮች የተካሄዱት የአማራ ክልል መንግስት ልዑካን ታጣቂዎቹ ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች እየሄዱ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ግዛቸው፤ ወደፊት ግን ለውይይት በሚያመች መልኩ በዋግም ሆነ በባህርዳር ሊካሄድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

አሁን በጅምር ላይ ባለው ንግግር “ያልተሟሉ ጉዳዮች” መኖራቸውን ያነሱት የአማራ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፤ በታጣቂዎቹ በኩልም “ቅድመ ሁኔታዎች” መቀመጣቸውን ጠቅሰዋል። ታጣቂ ቡድኑ ምን አይነት ቅድመ ሁኔታዎች እንዳስቀመጠ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ግዛቸው፤ “የሰላም ድርድሩ በሂደት ላይ ስለሆነ ያለው ሂደቶችን ወደ ሚዲያ እያወጣን ከሄድን አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚኖራቸው በሂደት እንገልጻቸዋለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የሰላም ውይይቱን በተመለከተ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የአገው ሸንጎ ፓርቲ ሊቀመንበር፤ “ከአገው ዴሞክራሲ ንቅናቄ ጋር የሚደረገው ውይይት ስምምነት የሚያመጣ ከሆነ እንፈልገዋለን” ሲሉ መልሰዋል። በአማራ ክልል መንግስት ላይ “እምነት እንደሌላቸው” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት አቶ አላምረው፤ ፓርቲያቸው የሰላም ውይይቱ መካሄድ ያለበት “የፌደራል መንግስት አውቆት” እና “ሶስተኛ ወገን ባለበት” መሆን አለበት የሚል አቋም እንዳለው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግን የክልሉ መንግስት በአካባቢው ሰላም ለማስፈን “ቁርጠኛ ነው” ባይ ናቸው። “በእኛ በኩል የሰላም ጉዳይ በጣም ቅድሚያ የምንሰጠው ነው” የሚሉት አቶ ግዛቸው፤ በአካባቢው ሰላም ለማስፈን ከመከላከያ ኃይል እና ከፌደራል መንግስት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል። “ከሰላም ንግግሩ ጎን ለጎንም” በሁለቱ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የእርዳታ ድጋፍ እንዲደርሳቸው “ከፍተኛ ጥረቶች እየተደረጉ ነው” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)