ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ፊት ለማራመድ “ለብዙ አስርት ዓመታት ወደ ኋላ የመለሳትን የብሔር ፖለቲካዊ ግጭት አዙሪት ለመስበር የሚረዱ እርምጃዎች መውሰድ” እንደሚገባት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ተናገሩ። እኚሁ የሀገሪቱ ከፍተኛ ዲፕሎማት፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት የሻከረው የኢትዮጵያ እና አሜሪካ መደበኛ ግንኙነት “ወደ ነበረበት ተመልሷል” ማለት እንደሚቸግራቸውም ገልጸዋል።
ሞሊ ፊ ይህን ያሉት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የአፍሪካ ጉብኝትን አስመልክቶ፤ ትላንት አርብ መጋቢት 1፤ 2015 ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው። ብሊንከን በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ፤ ከፌደራል መንግስት በተጨማሪ የትግራይ ባለስልጣናትን እንደሚያገኙ ረዳት ሚኒስትሯ ተናግረዋል። ሞሊ ፊ፤ ብሊንከን ወደ መቐለ የመጓዝ ዕቅድ እንደሌላቸውም ገልጸዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአዲስ አበባ ጉብኝት፤ በፕሪቶሪያ ከተፈረመው ስምምነት በኋላ “ሰላምን ለማጠናከር” አሜሪካ የምታደርገው ጥረት ቀጣይ አካል እንደሆነ ረዳት ሚኒስትሯ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። “ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ግንኙነት ማደስ እንፈልጋለን” ያሉት ሞሊ ፊ፤ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲኖራት የምትሻው አጋርነት ከሀገሪቱ “ግዝፈት እና ተጽዕኖ እንዲሁም ከአሜሪካ ጥቅም እና ለአፍሪካ ካላት ቁርጠኝነት ጋር የሚመጣጠን” መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ተከትሎ፤ አሜሪካ በጉዳዩ ላይ ስታራምድ በቆየችው አቋም እና በወሰደቻቸው እርምጃዎች ምክንያት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ክፉኛ ተቀዛቅዞ ቆይቷል። ጦርነቱ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ላይ ሳሉ ይቀስቀስ እንጂ፤ ተፋፍሞ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ብርቱ ሰብዓዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ያስከተለው ጆ ባይደን በትረ ስልጣኑን ከተረከቡ በኋላ ነው።
የፕሬዝደንት ባይደን አስተዳደር፤ ጦርነቱ እንዲቆም እንዲሁም የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ልዩነቶቻቸውን በድርድር እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ባደረገው ግፊቶች ምክንያት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ጋር ያለው ግንኙነት በብርቱ ሻክሯል። ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ በአጎዋ ስምምነት መሰረት ሸቀጦቿን ያለ ቀረጥ ለአሜሪካ ገበያ የማቅረብ ዕድሏን በፕሬዝደንት ጆ ባይደን ውሳኔ አጥታለች።
ግንኙነቱ በሻከረበት ወቅት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በተካሄዱ ሰልፎች፤ አሜሪካ “በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብታለች” የሚሉ ተደጋጋሚ ውግዘቶች ሲደመጡ ሰንብተዋል። ከአራት ወራት ገደማ በፊት በፕሪቶሪያ ከተፈረመው ግጭት የማቆም ስምምነት በኋላ፤ በጦርነቱ የተቀዛቀዘው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የመሻሻል አዝማሚያ አሳይቷል። የደቡብ አፍሪካው ስምምነት እስኪፈረም በነበረው የማደራደር ሂደት የአፍሪካ ህብረት ግንባር ቀደም የተጫወተ ቢሆንም፤ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ የአሜሪካ ሚና ቁልፍ እንደነበር ታዛቢዎች ይገልጻሉ።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ተጉዘው፤ ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና ከብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ጋር ተገናኝተዋል። የብሊንከን የመጪው ሳምንት የኢትዮጵያ ጉብኝትም፤ የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት ቀድሞ ወደነበረበት ደረጃ እየተመለሰ መምጣቱን ያመላከተ ነው ተብሏል።
የፖለቲካ ታዛቢዎች ይህን ቢሉም በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትሯ ግን የኢትዮጵያ እና አሜሪካ መደበኛ ግንኙነት “ወደ ነበረበት ተመልሷል” የሚለውን አገላለጽ ለመጠቀም እንደሚቸግሩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ዲፕሎማቷ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ፊት ለማራመድ፤ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ጨምሮ “አገሪቱን ለብዙ አስርት አመታት ወደ ኋላ የመለሰውን የብሔር ፖለቲካዊ ግጭት አዙሪት ለመስበር የሚረዳን የኢትዮጵያ እርምጃዎችን ማየት እንፈልጋለን” ሲሉ የአገራቸውን ፍላጎት አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለሶስት ዓመታት ያህል በዲፕሎማትነት ያገለገሉት ሞሊ ፊ፤ የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት የሚያውቁ ናቸው። በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከአምባሳደሩ ቀጥሎ ሁለተኛውን ቁልፍ ቦታ ይዘው የነበሩት ሞሊ ፊ፤ አዲስ አበባን በ2006 ዓ.ም. ከተሰናበቱ በኋላም ቀጣይ ማረፊያቸው እምብዛም ከሀገሪቱ የራቀ አልነበረም። ከአንድ ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ጎረቤት በሆነችው ደቡብ ሱዳን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ዲፕሎማቷ፤ በቦታው ለሁለት ዓመት ቆይተዋል። ሞሊ ፊ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ረዳት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት በመስከረም 2014 ዓ.ም ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)