በተስፋለም ወልደየስ
የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ ክልል ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ያካሄደው ሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግር አለመሳካቱ፤ የድርድር ሃሳብን “ተስፋ ተቆርጦ ተትቷል ማለት አይደለም” ሲሉ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ተናገሩ። መንግስት “ተደራዳሪዎች ፍላጎት እስካላቸው ድረስ ውይይቱ መቀጠል አለበት” የሚል እምነት እንዳለውም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አቶ ብናልፍ ይህን ያሉት፤ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ያለውን “ግጭት” በተመለከተ፤ ዛሬ ሐሙስ ጥር 2፤ 2016 ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ነው። በዛሬው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የተገኙ በርከት ያሉ የፓርላማ አባላት፤ በኢትዮጵያ ያለውን የጸጥታ ችግር የተመለከቱ ጥያቄዎችን ለሚኒስትሩ ሰንዝረዋል።
በብዙዎቹ የምክር ቤት አባላት በተደጋጋሚ የተነሳው ግን በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ያለው ግጭት ነው። ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የሰላም ሚኒስትሩ፤ “ጦርነት የትኛውንም የሀገሪቱን ችግር ይፈታል” የሚል እምነት በመንግስት በኩል እንደሌለ አስታውቀዋል።
“በየትኛውም መንገድ፣ በየትኛውም አካባቢ፣ በየትኛውም አጀንዳ ምክንያት የሚቀሰቀስ እና የሚካሄድ ጦርነት፣ ግጭት፤ ህዝብን ይጎዳ ካልሆነ በስተቀር፣ ሀገርን ወደ አለመረጋጋት ይወስድ ካልሆነ በስተቀር፣ ዋጋ ያስከፍለን ካልሆነ በስተቀር የሀገሪቱን ችግር ይፈታል የሚል እምነት የለንም” ሲሉ አቶ ብናልፍ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ “ጦር እንድንማዘዝ የሚያስገድድ ሁኔታ የለም” ሲሉ የተደመጡት የሰላም ሚኒስትሩ፤ በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችም ቢሆኑ “ከድርድር እና ከውይይት በላይ አይደሉም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። “ተነጋግረን፣ ቁጭ ብለን፣ ተወያይተን፣ ችግሮቻችንን መፍታት እንችላለን” ያሉት አቶ ብናልፍ፤ በዚህ እምነት መነሻነት የኦሮሚያ ክልል እና የፌደራል መንግስታት ባደረጓቸው “የጋራ ትብብር እና ጥረቶች” ውይይቶች መጀመራቸውን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ ከሚጠራው ቡድን ተወካዮች ጋር የመጀመሪያውን ድርድር ያካሄደው በሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ነበር። በታንዛንያ ዛንዚባር ደሴት ለአንድ ሳምንት ገደማ የተካሄደው ይህ የመጀመሪያ ዙር ድርድር፤ ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ሁለቱም ወገኖች በየፊናቸው ባወጡት መግለጫ በወቅቱ አስታውቀው ነበር።
ይህ ድርድር ከተካሄደ ከመንፈቅ በኋላ በዚያው በታንዛንያ ዳሬሰላም ከተማ የተካሄደው ሁለተኛ ዙር ድርድር፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዥ ድሪባ ኩምሳን ጭምር ማሳተፉ ከፍተኛ ተስፋ እንዲጣልበት ምክንያት ሆኖ ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የኢትዮጵያን መንግስት ወክለው የተሳተፉበት ይህ ድርድር እንደ መጀመሪያው ዙር ሁሉ ያለ ውጤት ተቋጭቷል።
ውይይቱ “የሚታሰበውን ለውጥ አለማምጣት”፤ “ሁላችንም የምንፈልገው አይደለም፣ የምንጠብቀው አልነበረም” ብለዋል የሰላም ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያቸው። “እኛ የምንጠብቀው ስምምነቱ ወደ ሰላም እንዲመጣ በማድረግ፤ ልዩነቶች በውይይት ተቋጭተው፣ ክልሉም ሀገሪቱም ሰላም እንድትሆን ነው” ሲሉም ሚኒስትሩ በመንግስት በኩል በወቅቱ የነበረውን ተስፋ አስረድተዋል።
“እስካሁን ባለው ድርድር የሚፈለገው ውጤት አልመጣም። በመንግስት በኩል ግን በማንኛውም ጊዜ፣ ተደራዳሪዎች ፍላጎት እስካላቸው ድረስ ይሄ ውይይት መቀጠል አለበት። ይሄ ውይይት አሁንም ወደ መቋጫው እስኪደርስ ድረስ መቀጠል ያለበት ነው የሚል እምነት አለ” ሲሉ የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም በድርድር አቋሙ እንደጸና አቶ ብናልፍ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
“ይሄ የአሁኑ ውይይት አልተሳካም ማለት ከዚህ በኋላ ድርድር አያስፈልግም፣ ድርድር ተስፋ ተቆርጦ ተትቷል ማለት አይደለም። ስለዚህ ድርድሩ መቀጠል ይኖርበታል”
– አቶ ብናልፍ አንዷለም፤ የሰላም ሚኒስትር
“ይሄ የአሁኑ ውይይት አልተሳካም ማለት ከዚህ በኋላ ድርድር አያስፈልግም፣ ድርድር ተስፋ ተቆርጦ ተትቷል ማለት አይደለም። ስለዚህ ድርድሩ መቀጠል ይኖርበታል። የሚፈለገው ውጤት እስኪመጣ ድረስ ያለማቋረጥ በማንኛውም ጊዜ ብንደራደር ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም” ሲሉ የሰላም ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ሶስተኛ ዙር ድርድር እንደሚኖር የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላም ከአንድ ወር በፊት ፍንጭ ሰጥተው ነበር። ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ለመንግስት ቅርበት ካለው ፋና ቴሌቪዥን ጋር በወቅቱ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ በሁለተኛው ዙር ድርድር አደራዳሪዎች ጭምር “የሚያምኑበት” “የመጨረሻ ሰነድ” (final paper) ተዘጋጅቶ እንደነበር ገልጸዋል።
“እስካሁን የተደከመበት ውይይት እና ሰነድ አለ። እርሱን መቀበል ላይ ከተደረሰ ሶስተኛ ውይይት ሊኖር ይችላል። ሶስተኛም ውይይት የመጨረሻ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። ወደ ሰላም ለመምጣት የመጨረሻ ይሆናል ወይም እስከ መጨረሻው ሁለተኛ ላለመነጋገር ይሆናል” ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ በቃለ ምልልሳቸው ተናግረው ነበር።
የሰላም ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ገለጻቸው፤ መንግስት በአማራ ክልል ያለውን “ግጭት” በተመሳሳይ መንገድ የመፍታት አቋም እንዳለው አስረድተዋል። “ጦር መማዘዙ፣ ይዋጣልን መባባሉ፣ ዜጎችን ለጉዳት ከመዳረግ ባለፈ ሌላ ውጤት አያመጣም” ያሉት አቶ ብናልፍ፤ መንግስት በክልሉ ያለውን ችግር “በሰላማዊ ድርድር እና ውይይት መፈታት አለበት” የሚል እምነት እንዳለው አስገንዝበዋል።
“የሰሜኑን ጦርነት በንግግር፣ በውይይት ቁጭ ብለን እንደፈታነው፤ ነገም በአማራ ክልልም ሆነ በኦሮሚያ፣ በሌሎችም ክልሎች ያሉ ግጭቶች በንግግር እና በውይይት መቋጨት አይችሉም?” ሲሉ የጠየቁት የሰላም ሚኒስትሩ፤ “የማይቀር ስለሆነ ወደዚህ ድርድር እና ውይይት መጥተን፣ ቁጭ ብለን ተወያይተን፣ ከዚህ በላይ ዋጋ ሳንከፍል፣ ከዚህ በላይ መስዋዕትነት ሳንከፍል እንደዚህ አይነት ጉዳዮች መቋጨት አለባቸው” ብለዋል።
“ወደ ድርድር ወደ ውይይት መምጣት በጣም አዋጪ ነው። ይሄንን በሁሉም ክልሎች ባሉ የታጠቁ ኃይሎች ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል” ያሉት አቶ ብናልፍ፤ ለዚህ ግን “ሁሉም ወገን ራሱን ማዘጋጀት አለበት” ሲሉ አሳስበዋል። ይህን ያስባላቸው “አንዳንድ ጊዜ ስለ ድርድር ሲነሳ የሚባለውን ነገር” እንደሆነም ጠቅሰዋል። “ከእንደዚህ አይነት ነገር ወጥቶ፤ ‘መነጋገር እና መወያየት፣ መደራደር ነው ችግሩን የሚፈታው’ በሚል” ወደ ድርድር መምጣት እንደሚያስፈልግም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)