በተስፋለም ወልደየስ
በራስ ገዟ የሶማሌላንድ የወደብ ጉዳይ የሚወዛገቡት የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ ለውይይት የሚቀርብበት ልዩ የመሪዎች ጉባኤ በሚቀጥለው ሳምንት በኡጋንዳ ሊካሄድ ነው። በጉባኤው ላይ በእርስ እርስ ጦርነት እያታመሰች ያለችው የኢትዮጵያ ጎረቤት ሱዳን ጉዳይም ለውይይት ይቀርባል ተብሏል።
ልዩ የመሪዎች ጉባኤውን የተጠራው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የወቅቱ ሊቀመንበር በሆኑት የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ ነው። ጉባኤው እንደሚካሄድ ለሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት ትላንት ሐሙስ ጥር 2፤ 2016 ባሰራጨው ደብዳቤ ያሳወቀው፤ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ነው።
የመሪዎች ጉባኤው በኡጋንዳ እንዲካሄድ የተወሰነው፤ የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ምክክር ካደረጉ በኋላ መሆኑ በደብዳቤው ተጠቅሷል። በዚሁ መሰረት ልዩ ጉባኤው በመጪው ሐሙስ ጥር 9፤ 2016 በኡጋንዳ ይካሄዳል። በጉባኤው ላይ ሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት፣ የአፍሪካ ህብረት እና ዓለም አቀፍ አጋሮች እንዲገኙ በጅቡቲ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር በኩል ይፋዊ ጥሪ እንደሚላክላቸው በደብዳቤው ላይ ሰፍሯል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ጨምሮ ስምንት አባል ሀገራት ያሉት ኢጋድ፤ ተመሳሳይ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ያደረገው ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ በጅቡቲ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ የአምስት ሀገራት መሪዎች በተገኙበት በዚሁ ጉባኤ ላይ ዋነኛ አጀንዳ የነበረው የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ነው። የመሪዎች ጉባኤው በሱዳን የሚካሄዱ የሽምልግና ጥረቶች በኢጋድ ማዕቀፍ እንዲከናወን ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ መግለጫ የሰጡት የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፤ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖችን የሚመሩት አብዱል ፋታህ አል-ቡርኻን እና ሞሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ የተኩስ ማቆም ስምምነት ለመፈራረም መስማማታቸውን አስታውቀው ነበር። ጉባኤውን ተከትሎ በነበረው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ግን የተባለው የተኩስ ማቆም ስምምነቱ እንደተባለው ሳይፈረም መቅረት ብቻ ሳይሆን፤ ለኢጋድ ሌላ ራስ ምታት የሆነ ጉዳይ ተከስቷል።
ኢጋድን ልዩ የመሪዎች ስብሰባ እንዲጠራ ያስገደደው ይህ ጉዳይ፤ የባህር ወደብን ለማልማት ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የፈረሙት የመግባቢያ ስምምነት ነው። ይህ የመግባቢያ ስምምነት፤ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ጠረፍ ላይ የራሷን የጦር ሰፈር እንድትገነባ መንገዱን የሚጠርግላት እንደሆነ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል። ስምምነቱን አጥብቆ የተቃወመው የሶማሊያ መንግስት የሀገሪቱን ካቢኔ አስቸኳይ ስብሰባ ከመጥራት ጀምሮ ከዚሁ ጋር የተያያዙ ተከታታይ እንቅስቃሴዎችን ሲያካሄድ ቆይቷል።
በኢትዮጵያ እና “ያለ እኔ እውቅና የግዛቴ አካል ከሆነችው ሶማሌላንድ ጋር ምንም አይነት ስምምነት ሊደረግ አይችልም” በምትለው ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ወዝግብ ለማርገብ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገራት መግለጫዎችን ሲያወጡ ሰንብተዋል። ኢጋድ ተመሳሳይ አካሄድ ለመከተል ቢሞክርም፤ የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ “ለኢትዮጵያ አድልተዋል” በሚል በሶማሊያ ነቀፌታ ቀርቦባቸዋል።
ሶማሊያ በዋና ጸሀፊው ላይ ያላትን አቋም ባትቀየርም፤ ኢጋድ እያጋለ የመጣውን የሁለቱ ሀገራትን ውዝግብ ለመፍታት ያለመ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ጠርቷል። ጉባኤው መጠራቱን ይፋ ያደረገውን ደብዳቤ በኤክስ (የቀድሞ ትዊተር) ገጻቸው ያጋሩት የሶማሊያ የማስታወቂያ፣ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዳውድ አዌይስ፤ “የሶማሊያ ክልል ከሆነችው ሶማሌላንድ ጋር ህጋዊ ያልሆነ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም በአፍሪካ ቀንድ የተፈጠረውን ቀውስ የቀሰቀሰችው ኢትዮጵያ ናት” ሲሉ ወንጅለዋል።
ከዚህ መልዕክት አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ ዘግይቶ የባህር በርን በተመለከተ ሃሳባቸውን በኤክስ ገጻቸው ያሰፈሩት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ ጉዳዩን ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር አነጻጸረውታል። “የህዳሴውን ግድብ ያሳካነው ተጨብጭቦልን ሳይሆን ከቅርብም ከሩቅም እየተላጋን፣ የስጋት ከበሮ እየተደለቀ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ በምድርም በአየርም ልምምድ እያስገመገመብን፣ ሁሉንም ዓይነት ጫና ተቋቁመን ነበር። የባህር በሩም እንዲሁ ይሆናል” ሲሉ ጽፈዋል ሬድዋን።
የኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ጉዳይ ለመፍታት፤ ኢጋድ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ለሚቀጥለው ሳምንት መጥራቱን የቀድሞው የድርጅቱ ቃል አቃባይ ኑር ሙሐመድ ሼክ አድንቀዋል። ድርጅቱ ጉባኤውን መጥራቱ “በቀጠናው ሰላም እና ህብረት ለማበረታት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው” ብለዋል። “ድርጅቱ የቆመላቸው ህዝቦች ያላቸውን ምኞቶች እውን ለማድረግ ያለውን ያላሳለሰ መሰጠት ያስመሰከረ ነው” ሲሉም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)