የሰላም ሚኒስቴር የተቋቋመበትን “ርዕይ እና ተልዕኮ ባለመወጣቱ” እና “ስልጣን እና ተግባሩን በአግባቡ ባለመፈጸሙ”፤ የተቋሙ “ ‘አስፈላጊነት አይታየንም’ የሚሉ ኃይሎች ተበራክተዋል” ሲሉ አንድ የፓርላማ አባል ትችት አቀረቡ። ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚውለው ሃብት፤ ለሌሎች ተቋማት መተላለፍ እንዳለፈበትም እኚሁ የፓርላማ አባል አሳስበዋል።
ይህ ትችት እና ማሳሰቢያ የተደመጠው፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ሐሙስ ጥር 2፤ 2016 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው። ምክር ቤቱ በዚሁ ስብሰባው፤ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ እና ማብራሪያ አዳምጧል። በስብሰባው ላይ ጥያቄያቸውን ካቀረቡ የፓርላማ አባላት ውስጥ ሁለቱ፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰላምን የማረጋገጥ ተልዕኮውን በአግባቡ አልተወጣም ሲሉ ተችተዋል።
ሉባባ ሰኢድ የተባሉ የተወካዮች ምክር ቤት አባል “የሰላም ሚኒስቴር ሲባል ከመቼውም [ጊዜ] በላይ ያላሰለሰ የህዝብ ውይይት በማድረግ ችግሩን በመቀነስ፣ ህዝባችን የናፈቀውን እንከን የለሽ ሰላም ያረጋግጣል የሚል ትልቅ እምነት ቢጣልበትም፤ እንዳለመታደል ሆኖ ችግሮች እየተባባሱ መጥተው ወደ ጦርነት እያመሩ ህዝባችንን የበለጠ የጨለመ ተስፋ ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል” ብለዋል።
ተቃዋሚውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው ፓርላማ የገቡት አቶ አበባው ደሳለውም፤ “የሰላም ሚኒስቴር ያለውን አስተዋጽኦ ስናይ በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰንዝረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “ርዕዩን እና ተልዕኮውን አልተወጣም። ስልጣን እና ተግባሩን አንዳቸውንም በአግባቡ አልፈጸመም” ሲሉ የነቀፉት የፓርላማ አባሉ፤ “ለዚህ ተቋም የሚውለው ሃብት ለሌሎች የልማት፣ የዲሞክራሲያዊ ተቋማት መዋል አለበት” ብለዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም፤ የሃገሪቱን የጸጥታ ሁኔታ “ሰላም ሚኒስቴር ከሚባለው ተቋም ጋር ብቻ አነጻጽረን የምናየው ከሆነ ችግሩን እናሳንሰዋለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “አንዳንድ ጊዜ ሲባል [የሚሰማው]፣ እዚህ ምክር ቤትም በግልጽ እንደተነሳው፤ ‘ሰላም ሚኒስቴር ከተቋቋመ በኋላ ነው ግጭቶች የበዙት’ የሚባሉት ነገሮች፤ ታሪካችንን ወደ ኋላ ሄደን ማየት ነው። ሰላም ሚኒስቴር ከተቋቋመ የአምስት ዓመት ዕድሜ ያለው ተቋም ነው። አሁን የምናወራው እኮ የብዙ ዓመታት ግጭት እና የጦርነትን ታሪክ ነው” ሲሉ ችግሩን አሳንሶ መመልከት እንደማይገባ ተናግረዋል።
አቶ ብናልፍ በትላንቱ የፓርላማ ማብራሪያቸው፤ የሚመሩት መስሪያ ቤት የተደራጀው በኢትዮጵያ ያለውን የሰላም እጦት ተቋማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት በማሰብ መሆኑን ገልጸዋል። “የሰላም ችግር በሀገሪቱ አለ። ይህንን የሰላም ችግር ደግሞ ለመፍታት ‘ተቋም መስርተን፣ በተቋም ልንመራው ይገባል’ ተብሎ ስለታመነ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሁሉም ተቋማት በዚያ መንገድ የተደራጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
“[ፓርላማው] ተሳስቶ ከሆነ ራሱን ነው እንጂ ማየት ያለበት፤ ጥያቄው ወደ እኛ አይደለም መምጣት ያለበት”
– አቶ ብናልፍ አንዷለም፤ የሰላም ሚኒስትር
የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ የተደነገገውን ተልዕኮ የሰጠው የተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን ያስታወሱት አቶ ብናልፍ፤ “ምክር ቤቱ ተሳስቶ ከሆነ ራሱን ነው እንጂ ማየት ያለበት፤ ጥያቄው ወደ እኛ አይደለም መምጣት ያለበት” ሲሉ በተቋሙ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ ላነሱት የፓርላማ አባል መልሰዋል። የሰላም ሚኒስቴር የሚመራው የተወካዮች ምክር ቤት በሚያሳልፈው ውሳኔ በመሆኑ፤ “ተቋሙ ‘አሁን ያስፈልጋል ወይም አያስፈልግም?’ የሚለውን ምክር ቤቱ ራሱ ቢያየው ነው ትክክል እና ተገቢ የሚሆነው” ሲሉም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)