የአዲስ አበባ ስታዲየም “በአጭር ጊዜ” ውስጥ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ  

በተስፋለም ወልደየስ 

ለዓመታት በእድሳት ላይ የቆየው የአዲስ አበባ ስታዲየም “በአጭር ጊዜ” ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንደሚጀምር የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ። በስታዲየሙ የሚገጠሙ የቪአይፒ መቀመጫዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በነበረ ችግር የማጠናቀቂያ ስራ መዘግየቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ይህን ያስታወቀው፤ የ2016 በጀት ዓመት የአምስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ከትላንት በስቲያ ለፓርላማ ባቀረበበት ወቅት ነው። ሪፖርቱን ጉዳዩ ለሚመለከተው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ፤ “የአዲስ አበባ በስታዲየሙ መቶ ፐርሰንት አልቋል ማለት ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ በስታዲየም “በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) እና በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የተቀመጡ መስፈርቶችን አላሟላም” በሚል የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ከማስተናገድ ለመጀመሪያ ጊዜ የታገደው በ2011 ዓ.ም. ነበር። ካፍ እግዱን ከማስተላለፉ በፊት፤ በስታዲየሙ የመጫወቻ ሜዳን ጨምሮ የተጨዋቾች መልበሻ እና መታጠቢያ ክፍሎች፣ የመጸዳጃ ቤቶችና ሌሎች ተጨማሪ ማስፋፊያ ስራዎች እንዲደረጉለት በተደጋጋሚ ምክረ ሃሳቦችን ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል። 

ፎቶ፦ በኤልያስ ባዩ

ከተገነባ 75 ዓመታት ያለፈው የአዲስ አበባ ስታዲየም፤ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ ዕድሳት እንዲደረግለት የውል ስምምነት የተፈረመው በሰኔ 2013 ዓ.ም. ነበር። ለስታዲየሙ የወጣውን ጨረታ በ39.6 ሚሊዮን ብር ያሸነፈው ፍሬንድስ ኢንጅነሪንግ የተባለ የግል ኩባንያ፤ ዕድሳቱን “በአጭር ጊዜ አጠናቅቆ እንደሚያስረከብ” በወቅቱ ቢገለጽም ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ እስካሁንም ለአገልግሎት ክፍት አልሆነም። 

የአዲስ አበባ ስታዲየም ግንባታ መዘግየት ጉዳይ፤ በተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት እና ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴም ጥያቄ አስነስቷል። የቋሚ ኮሚቴውን ከፊል ጥያቄዎች በንባብ ያሰሙት አልማዝ ተመስገን የተባሉ የፓርላማ አባል፤ “ነባሩ የአዲስ አበባ ስታዲየም ጥገናን በተመለከተ በተደጋጋሚ የገባችሁትን ቃል አልፈጸማችሁም። አሁንስ በእርግጠኝነት የሚጠናቀቀው መቼ ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ኃላፊ፤ የስታዲየሙን እድሳት መጠናቀቅ ያዘገየው የቪአይፒ ተመልካቾች መቀመጫዎችን ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ጉዳይ እልባት በማግኘቱ “በአጭር ጊዜ ውስጥ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል” ብለዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በስታዲየሙ “መጫወት ይችላል” ያሉት እኚሁ ኃላፊ፤ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ቡድኖችም ቢሆኑ በአዳማ የጀመሩትን መርሃ ግብር ከሁለት ሳምንት በኋላ ሲጨርሱ “በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ” ብለዋል። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አ.ማ.

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ 16 የእግር ኳስ ክለቦች፤ በአሁኑ ወቅት ውድድራቸውን እያደረጉ ያሉት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ላይ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በበኩሉ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ሲያካሄድ የቆየው፤ በኪራይ በሚያገኛቸው የአፍሪካ ሀገራት ስታዲየሞች ነበር።

የአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታዎችን ወደ ማስተናገድ ይመለሳል ተብሎ የታቀደው፤ ባለፈው ወር መጨረሻ አካባቢ እንደነበር የባህልና ስፖርት ሚኒስቴሩ አቶ ቀጄላ ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስረድተዋል። “የቪአይፒ እና የቪቪአይፒ ተመልካቾች መቀመጫዎች ደረጃቸውን የጠበቁ መሆን አለባቸው” የሚል ሃሳብ “በካፍ እና በፊፋ በኩል ስለቀረበ”፤ መቀመጫዎቹን በቻይና ሀገር አስመርቶ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በተደረገ ጥረት መዘግየት መፈጠሩን ገልጸዋል። 

“[ቻይና] ተመርቶ ሲመጣ፤ ‘ፈርኒቸር ወደ ሀገር ውስጥ መግባት አይችሉም’ ከሚባሉት ቁሳቁሶች ውስጥ አንዱ በመሆኑ ጅቡቲ ላይ ተያዘ። ሊገባ አልቻለም፤ ቆየ ማለት ነው። ኮንትራክተሮቹ በየቀኑ በዶላር እየከፈሉ ችግር አጋጥሟቸው ነበር” ሲሉ ሚኒስትሩ ችግሩ በምን ምክንያት እንደተከሰተ አብራርተዋል። መስሪያ ቤታቸው ችግሩን ለመፍታት አንድ ወር ያህል እንደፈጀበትም ጠቁመዋል። 

“ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረን ‘ይሄ የቅንጦት ዕቃ አይደለም። የግንባታ ዕቃ ነው። ፕሮጀክቱ የህዝብ ፕሮጀክት ነው እና ይግባልን’ ብለን፤ በማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ነው የተወሰነው። በኋላ [ጉዳዩ] ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ሄዶ፤ አሁን ተፈቅዶ እየገባልን ነው። እርሱን ብቻ ነው የምንጠብቀው እንጂ፤ ሌላው ተሰርቶ አልቋል” ሲሉ የስታዲየሙ የውስጥ እድሳት መጠናቀቁን ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። 

ለደጋፊዎች መቀመጫ የሚሆን 17 ሺህ ወንበር “ከተተከለ መቆየቱን” በማብራሪያቸው ያነሱት አቶ ቀጄላ፤ በስታዲየሙ ያለውን አሮጌ የመሮጫ መም ከመቀየር አንስቶ በካፍ ያልተጠየቁ ሌሎች ማሻሻያዎች በስታዲየሙ የውስጠኛው ክፍል መደረጉን አመልክተዋል። በስታዲየሙ ዙሪያ ያሉትን አካባቢዎች በዙሪያ ካሉት መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር፤ ወደ አረንጓዴ ስፍራ እና ሌሎች አገልግሎት መስጪያዎች ለመለወጥ የዲዛይን ስራ መጠናቀቁንም አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)