በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለመምከር የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት ለዛሬ ስብሰባ ጠራ 

የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት የኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በዛሬው ዕለት ሊመክር ነው። በስብሰባው ላይ የሁለቱ ሀገራት ተወካዮች ማብራሪያ እንደሚያቀርቡ እና ምክር ቤቱም ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ በጉዳዩ ላይ መግለጫ እንደሚያወጣ ተገልጿል።

የዛሬው ስብሰባ የህብረቱ ምክር ቤት አስቀድሞ በያዘው መደበኛ የስራ መርሃ ግብር ያልተካተተ መሆኑን፤ በአፍሪካ ህብረት እና በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ጥናት እና ምርምር የሚያደርገው “አማኒ አፍሪካ” የተሰኘው ድርጅት አስታውቋል። ስብሰባውን በንግግር የሚከፍቱት የዚህ ወር የምክር ቤቱ ሊቀመንበር የሆኑት፤ በአፍሪካ ህብረት የጋና አምባሳደር አማ ቱም-አሙሃ መሆናቸውን ድርጅቱ ገልጿል። 

እርሳቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ጸጥታ ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴዎዬ፤ ጉዳዩን በተመለከተ ለምክር ቤቱ ገለጻ እንደሚሰጡ “አማኒ አፍሪካ” አስታውቋል። በአፍሪካ ግጭቶችን የመከላከል እና ከተከሰቱም በኋላ የመቆጣጠርና መፍትሄ የማበጀት ዓላማ ያለው የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት 15 አባል ሀገራት አሉት። 

ሀገራት በየሁለት እና ሶስት ዓመት በሚደረግ ምርጫ በሚተካኩበት በዚህ ምክር ቤት ውስጥ፤ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን በመወከል የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ጅቡቲ፣ ታንዛንያ እና ኡጋንዳ ናቸው። በራስ ገዟ የሶማሌላንድ የወደብ ጉዳይ እየተወዛገቡ የሚገኙት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአሁኑ ወቅት የምክር ቤቱ አባል ባይሆኑም፤ ተወካዮቻቸው ግን በዛሬው ስብሰባ ላይ ማብራሪያ ያቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ “አማኒ አፍሪካ” ጠቁሟል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲሻክር ያደረገው፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ታህሳስ 22፤ 2016 በአዲስ አበባ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ነው። ይህ የመግባቢያ ስምምነት፤ ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ የባህር ወደብን ለማልማት የሚያስችላት ነው ተብሏል። የመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ጠረፍ ላይ የራሷን የጦር ሰፈር እንድትገነባ መንገዱን የሚጠርግላት መሆኑም በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ተነግሯል።

ኢትዮጵያ በምላሹ ራስ ገዝ ለሆነችው ሶማሌላንድ እንደ ሀገር ዕውቅና እንድምትሰጥ በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ አስታውቀው ነበር። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት ከቀናት በኋላ ባወጣው መግለጫ “ሶማሌላንድ ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሂደት በጥልቀት አጢኖ አቋም የሚወስድበት” መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።  

ሶማሌላንድ “የግዛቴ አካል ነች” የምትለው ሶማሊያ፤ የመግባቢያ ስምምነቱ “ሉዓላዊነቷን የጣሰ” መሆኑን በመግለጽ   አጥብቃ ስትቃወም ቆይታለች። ሶማሊያ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሯን ወደ ሀገሯ ከመጥራት አንስቶ፤ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ስብሰባ እንዲያደርጉ ጥያቄ እስከማቅረብ ድረስ መጓዟን “አማኒ አፍሪካ” ዛሬ ለንባብ ባበቃው ማብራሪያ ላይ ጠቅሷል። 

ሶማሊያ ስብሰባው እንዲካሄድ የመንግስታቱን ድርጅት መገፋፋቷን ተከትሎ፤ የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካን ለሚወክሉ ሶስት ሀገራት “አቅጣጫ እንዲሰጥ”  እና የስብሰባውን ድምጸት እንዲወስን ጫና እንዳለ ይኸው ማብራሪያ ጠቁሟል። በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት ሞዛምቢክ፣ ጋቦን እና ጋና ናቸው።

የዛሬው የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ ማወቅ ባይቻልም፤ በቀደመው ልምድ መሰረት ግን ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ ምክር ቤቱ መግለጫ ያወጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ “አማኒ አፍሪካ” በማብራሪያው አመልክቷል። ምክር ቤቱ በዚሁ መግለጫው፤ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተባባሰው ውጥረት ወደ ግጭት እንዳያመራ፤ ሀገራቱ “በከፍተኛ ሁኔታ ራሳቸውን እንዲቆጥቡ” ያሳስባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ድርጅቱ ግምቱን አስቀምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]