የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን፤ በመቐለ አየር ማረፊያ የመንሸራተት አደጋ ገጠመው

ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ የመንገደኞች አውሮፕላን፤ ዛሬ ሐሙስ በመቐለ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ በሚያርፍበት ወቅት ከመንደርደሪያው መንገድ ተንሸራትቶ በመውጣቱ በአውሮፕላኑ ላይ ጉዳት አጋጠመ። በክስተቱ ጉዳት የደረሰበት መንገደኛ እንደሌለ አየር መንገዱ ዛሬ ከሰዓት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ጉዳት የደረሰበት የአየር መንገዱ አውሮፕላን በበረራ ቁጥር ኢቲ 106 የተመዘገበው፤ ከአዲስ አበባ የተነሳው ከቀኑ ስድስት ሰዓት ተኩል መሆኑን አየር መንገዱ ገልጿል። ክስተቱ የደረሰው ከቀኑ ስምንት ሰዓት ከአስር ደቂቃ ላይ እንደሆነም ጠቁሟል። ከአደጋው መከሰት በኋላ ተሳፋሪዎች እና የበረራ ሰራተኞች ላይ ያለምንም ጉዳት ከአውሮፕላኑ መውረዳቸውንም አየር መንገዱ አመልክቷል።

አየር መንገዱ ይህን ቢልም በስፍራው የነበሩ ሁለት የዓይን እማኞች ግን በአደጋው ቢያንስ አንድ መንገደኛ ቀላል ጉዳት እንደደረሰበት መመልከታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአውሮፕላኑ ተሳፋሪ የነበሩ መንገደኞች ከአየር ማረፊያው ሲወጡ ከፍተኛ የመደናገጥ ስሜት ይታይባቸው እንደነበር የዓይን እማኞቹ ጨምረው ገልጸዋል። 

የአሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ እና የመቐለ ከተማ እሳት አደጋ ተከላከይ ሰራተኞች፤ ከአውሮፕላኑ እሳት እንዳይነሳ የመከላከል ስራ ሲሰሩ መስተዋላቸውን እማኞቹ አክለዋል። በአውሮፕላኑ አደጋ መድረሱ ከተነገረ ከሁለት ሰዓት በኋላም ጭምር ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ መንገደኞች በአየር ማረፊያው መግቢያ አካባቢ ሲጠብቁ እንደነበር በቦታው የነበሩ የመቐለ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረ ገጽ፤ ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ ለዛሬ የተያዙ በረራዎች ብዛት 11 መሆናቸውን ያሳያል። አደጋው ከደረሰ በኋላ አምስት በረራዎች ወደ መቐለ እንደሚደረጉ የሚጠበቁ ቢሆንም፤ እስከ ቀኑ 11 ሰዓት ድረስ ሌላ አውሮፕላን በአሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ አለማረፉን በስፍራው የሚገኙ የዓይን እማኞች ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]