በተስፋለም ወልደየስ
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አባል ሀገራት መሪዎች፤ የሶማሊያ ሉዓላዊ ግዛትን የሚመለከት “ማንኛውም ስምምነት የሀገሪቱን መንግስት ይሁንታ ሊያገኝ ይገባል” አሉ። መሪዎቹ ማንኛውም ግንኙነት የሶማሊያን “ሉዓላዊነት፣ አንድነት እና የግዛት አንድነት ያከበረ ሊሆን እንደሚገባም” አሳስበዋል።
የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች ይህን ያስታወቁት ዛሬ ሐሙስ ጥር 9፤ 2016 በኡጋንዳ ካደረጉት ልዩ ጉባኤ በኋላ ባወጡት መግለጫ ነው። መሪዎቹ በቪክቶሪያ ሀይቅ ዳርቻ በምትገኘው ኢንቴቤ ከተማ የተሰበሰቡት፤ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ በሻከረው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት እንዲሁም በሱዳን ባሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ለመወያየት ነበር።
የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር በሆኑት የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በተጠራው በዚሁ ልዩ ጉባኤ ላይ የአስተናጋጇ ሀገር ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒን ጨምሮ የአምስት ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል። ጉባኤው ከሚመለከታቸው ሀገራት መካከል ሶማሊያ በመሪዋ ሀሰን ሼክ መሐመድ ስትወከል፤ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ግን ሳይሳተፉ ቀርተዋል።

በኢንቴቤው ጉባኤ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ ኤል-ኬሄራጂን ተገኝተዋል። የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በስምምነት እንዲፈታ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር እና የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔት ዌበርም በጉባኤው ተሳታፊ ነበሩ።
ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ ይፋ የተደረገው የኢጋድ መግለጫ አብዛኛውን ትኩረቱን ያደረገው በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ነው። በመግለጫው በቀዳሚነት የተቀመጠው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ወቅታዊ ውዝግብ በአራት አንቀጾች ብቻ ቢጠናቀቅም፤ ጠንከር ያለ አቋም ግን የተንጸባረቀበት ነው። መሪዎቹ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት እንዲሻከር ምክንያት የሆኑ ሰሞነኛ ክስተቶች “እጅግ እንዳሳሰባቸው” በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲሻክር ያደረገው፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ታህሳስ 22፤ 2016 በአዲስ አበባ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ነው። ይህ የመግባቢያ ስምምነት፤ ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ የባህር ወደብን ለማልማት የሚያስችላት ነው ተብሏል። የመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ጠረፍ ላይ የራሷን የጦር ሰፈር እንድትገነባ መንገዱን የሚጠርግላት መሆኑም በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ተነግሯል።

ኢትዮጵያ በምላሹ ራስ ገዝ ለሆነችው ሶማሌላንድ እንደ ሀገር ዕውቅና እንድምትሰጥ በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በወቅቱ ገልጸው ነበር። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት ከቀናት በኋላ ባወጣው መግለጫ “ሶማሌላንድ ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሂደት በጥልቀት አጢኖ አቋም የሚወስድበት” መሆኑን መግለጹ ይታወሳል። የኢትዮጵያ መንግስት በዚሁ መግለጫው “በዚህ ስምምነት የሚጎዳ አካልም ሆነ ሀገር የለም። የተጣሰ ህግ እና የተሰበረ እምነት የለም” ማለቱም አይዘነጋም።
ሶማሌላንድ “የግዛቴ አካል ነች” የምትለው ሶማሊያ በበኩሏ፤ የመግባቢያ ስምምነቱ “ሉዓላዊነቷን የጣሰ” መሆኑን በመግለጽ አጥብቃ ስትቃወም ቆይታለች። በኢንቴቤው ጉባኤ የተሳተፉ የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች የሶማሊያ “ሉዓላዊነት፣ አንድነት እና የግዛት አንድነት” ለሚከበርበት “ጥብቅ መርህ” ማረጋገጫ የሰጡ ሲሆን፤ ማንኛውም የሚደረጉ ግንኙነቶች እነዚህን መርሆዎች ሊያከብሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በሶማሊያ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ የሚደረግ “ማንኛውም አይነት ስምምነት እና የሀገሪቱን መንግስት ይሁንታ ሊያገኝ ይገባል” ሲሉም ጠንካራ አቋማቸውን አስታውቀዋል። ይህ አቋም “ያለ እኔ እውቅና የግዛቴ አካል ከሆነችው ሶማሌላንድ ጋር ምንም አይነት ስምምነት ሊደረግ አይችልም” ከምትለው ሶማሊያ ጋር የተስማማ ሆኗል። የሶማሊያ መንግስት፤ የጉባኤው መግለጫ በኢጋድ በኩል ይፋ ከመደረጉ አስቀድሞ በይፋዊ የኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ገጽ ማጋራቱም ይህንኑ የሚያመለክት ይመስላል።
በዛሬው ጉባኤ የተሳተፉ መሪዎች፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት እንዲያደረግቡ ጥሪ አቅርበዋል። ሁለቱ ሀገራት “በገንቢ ውይይት”ላይ እንዲሳተፉም መሪዎቹ በመግለጫቸው ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)