ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “ሀገር ለማዳን” እየተከናወኑ ናቸው ያሏቸው ስራዎች፤ “በዛሬ ድጋፍና ተቃውሞ አይለኩም፤ በዛሬ ወሬና አሉባልታ አይገመገምም” አሉ። የጀመሩት ጉዞ “ሀገር የሚታደግና ስብራትን የሚጠግን” መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት “ጥቂቶች የተረዱት ነገ ግን ህዝብ ሁሉ የሚከተለው ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የጥምቀት በዓልን በተመለከተ ዛሬ አርብ ጥር 10፤ 2016 ባስተላለፉት መልዕክት ነው። በሀገር ድረጃ እየሰሯቸው ያሏቸው “ሁለት ዓላማ “ ያላቸው መሆናቸውን በመልዕክታቸው ያሰፈሩት አብይ፤ አንደኛው “ሀገርን ማዳን” ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “ለሌሎች መንገድ ማሳየት” መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግስታቸው “ሀገርን ለማዳን” እያከናወናቸው ያላቸው ስራዎች “ለሁሉም እኩል ላይታዩ ይችላሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዚህን ምክንያት ምን እንደሆነም አስረድተዋል። “ካለፈው የችግር ጊዜ እየወጣን መሆኑ፣ ወደ አዲስ ሀገራዊ ሁኔታ እየተሻገርን መሆኑ፤ ለጊዜው ላይታወቅ ይችላል” ያሉት አብይ፤ እንዲያም ሆኖ ግን “የኢትዮጵያ ትንሳኤ እና ህዳሴ ለሁሉም ግልጽ የሚሆንት ጊዜ ይመጣል” ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
“አንዳንድ ነገሮች ወዲያው ግልጽ ይሆናሉ፤ አንዳንድ ነገሮች ዘግይተው ግልጽ ይሆናሉ፤ አንዳንድ ነገሮችም ከዘመናት በኋላ ግልጽ ይሆናሉ። በዓለም ላይ የመጡ ለውጦች ሁሉ የተጓዙት እንዲሁ ነው። መጀመሪያ ተቃዋሚዎቻቸው ይበዙ ነበር። የሻማውም ብርሃን ጥቂት ነበር። ሲውል ሲያድር ግን ጨለማው እየተገፈፈ፤ ብርሃኑ እየተቀጣጠለ ሄዶ፣ ለሁላችንም ደረሰ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳባቸውን አብራርተዋል።
አብይ ለዚህ ማብራሪያቸው በማሳያነት የጠቀሱት፤ የስልክ ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገባ በወቅቱ የነበረውን አቀባበል ነው። “ዛሬ ሁላችንም እንደዋዛ የምንጠቀመበት ስልክ ከመቶ ዓመታት በፊት ወደ ሀገራችን ሲገባ ብዙ ፈተና ነበረው። ተወግዞ ነበር፤ ሰይጣን ነው ተብሎ ነበር። ብዙ ተወርቶበት ነበር። በአጭር እንዲቀጭ ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበርም” ሲሉ “ሀገር የማዳን” ጉዞም በተመሳሳይ “ፈታኝ” እና ጊዜ የሚወስድ መሆኑን አስረድተዋል።
“ሀገር የማዳን ተግባር በዛሬው ሚዛን አይመዘንም። በዛሬ ድጋፍና ተቃውሞ አይለካም። በዛሬ ወሬና አሉባልታ አይገመገምም። ጊዜ ይፈልጋል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህንኑ ዓላማቸውን የሚያሳኩ ስራዎች በሚያከናወኑበት ወቅት የገጠማቸውን ፈተናም አብይ በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።
ሀገር ለማዳን ስንሰራ በሀገር ላይ ተጨማሪ ቁስል ለማምጣት የሚሠሩ አሉ፡፡ ተሸንፈው መቅረታቸው ግን አይቀሬ ነው”
– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
“ሀገር ለማዳን ስንሰራ በሀገር ላይ ተጨማሪ ቁስል ለማምጣት የሚሰሩ አሉ” በማለት የከሰሱት አብይ፤ ሆኖም እነዚህ አካላት “ተሸንፈው መቅረታቸው አይቀሬ ነው” ሲሉ ከጀመሩት ስራ ወደ ኋላ እንደማይሉ አስታውቀዋል። “የጀመርነው ጉዞ ጥቂት የሚመስል ግን የሚበዛ፤ እዚህ የተወጠነ ግን ረዥም፤ ጥቂቶች የተረዱት፣ ነገ ግን ሕዝብ ሁሉ የሚከተለው” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ስብራት እየጠገንን፣ ሀገር እየታደግን፣መንገድም እየከፈትን መጓዛችንን እንቀጥላለን” ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ያሉትን በድጋሚ አስታጋብተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)