በጋዜጠኞች እስር፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሃገራት ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ሲፒጄ ገለጸ

ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ከአፍሪካ ሃገራት ሶስተኛ ደረጃ መያዟን ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (ሲፒጄ) ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል። በአፍሪካ በታሳሪ ጋዜጠኞች ብዛት ቀዳሚውን ቦታውን የያዘችው የኢትዮጵያ ጎረቤት ኤርትራ ስትሆን፤ ግብጽ ሁለተኛ ቦታን ይዛለች። 

ሲፒጄ ዓመታዊ ሪፖርቱን ባጠናቀረበት ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ገደማ፤ በመላው ዓለም የታሰሩ ጋዜጠኞች ብዛት 320 እንደነበር ገልጿል። ይህ ቁጥር ድርጅቱ መሰል ሪፖርቶች ማዘጋጀት ከጀመረበት ከ1985 ዓ.ም. ወዲህ በከፍተኛነቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ መሆኑንም ጠቁሟል። የ360 ጋዜጠኞች እስር የተመዘገበበት የፈረንጆቹ 2022 ዓመት፤ የምንጊዜውንም ከፍተኛ ቁጥር ያስተናገደ ነው።

በአፍሪካ እስካለፈው ህዳር መጨረሻ ድረስ ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ፤ ቢያንስ 67 የሚሆኑ ጋዜጠኞች “ከስራቸው ጋር በተያይዘ ለእስር መዳረጋቸውን” ሲፒጄ በሪፖርቱ አመልክቷል። ከእነዚህ ጋዜጠኞች ውስጥ አስራ ስድስቱን በማሰር እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ኤርትራ ናት። በኤርትራ ከታሰሩት ጋዜጠኞች አብዛኞቹ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በወህኒ ቤት ያሉ መሆናቸውን የጠቀሰው ድርጅቱ፤ በዓለም ላይ ካሉ ጋዜጠኞች “ለረጅም ጊዜ በመታሰር” የሚስተካከላቸው እንደሌለም አብራርቷል። 

ግብጽ 13 ጋዜጠኞችን ወደ ወህኒ በመወርወር ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ፤ ኢትዮጵያ ስምንት ጋዜጠኞችን በማሰር በሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ሲፒጄ በዓመታዊ ሪፖርቱ ገልጿል። ስምንቱ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች የታሰሩት፤ በአማራ ክልል ባሉ አማጽያን እና በፌደራል ኃይሎች መካከል ያለውን ግጭት ከዘገቡ በኋላ መሆኑን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ በሪፖርቱ አመልክቷል። 

በአፍሪካ በፈረንጆቹ 2023 ከታሰሩ ጋዜጠኞች ውስጥ አምስቱ ሴቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ አሁንም በኢትዮጵያ ታስረው እንደሚገኙ ሲፔጄ ይፋ አድርጓል። “በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ቁጥር የሚያሳየው፣ የሀገሪቱ ሁኔታ ለመገናኛ ብዙሃን አመቺ አለመሆኑን ነው” ሲል ድርጅቱ በዓመታዊ ሪፖርቱ ላይ አስፍሯል። በኢትዮጵያ በእስር ላይ ከሚገኙት ጋዜጠኞች መካከል የተወሰኑት ተከስሰው ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት፤ ጋዜጠኞቹ የታሰሩት “ከስራቸው ጋር በተያያዘ እንዳልሆነ” የፌደራል ዐቃቤ ህግ መግለጹ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)