በብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብስባ፤ “ነጻነት በዛ”፣ “ክልሎች ልቅ ሆኑ” የሚል ሃሳብ መንጸባረቁን የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። በብልጽግና ፓርቲ “ገና ብዙ መታረቅ” እና “መታረም ያለበት” “አስተሳሰብ እና አሰራር” እንዳለም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
አብይ ይህን ያሉት፤ በትላትናው ዕለት በተጀመረው የገዢው ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ገለጻ ነው። “ስብራትን መጠገን፤ ለትውልድ መታመን” የተሰኘ ርዕስ የተሰጠው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ገለጻ፤ የብልጽግና ፓርቲን አመሰራረት እና ቀድሞ የኢህአዴግ “አጋር” ተብለው ይጠሩ የነበሩ የክልል ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር የተቀላቀሉበትን አካሄድ መለስ ብሎ የቃኘ ነበር።
“ ‘ኢትዮጵያ ስብራት አለባት፤ ከዚያ ትወጣ ዘንድ መደመር አለብን’ የሚል ሃሳብ መጣ። መደመር የሚለው ሃሳብ ብቻውን ቢሆን ዋጋ አልነበረውም። ብልጽግና የሚባል፤ ‘ባለቤት እና ጎረቤት’ ብሎ ያልለየ፣ ‘የመካከል እና የጫፍ’ ብሎ ያልከፋፈለ፣ ሁሉን የሰበሰበ ፓርቲ ያስፈልጋል አልን። ይሄ ተቋም ነው” ሲሉ ብልጽግና ከሃሳብ ተነስቶ እንዴት እውን ሊሆን እንደቻለ አስረድተዋል።
በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን የሶማሌ እና አፋር ክልሎች “ራሳቸውን መርተው አያውቁም” ነበር ያሉት አብይ፤ አመራሩ ይሰጥ የነበረው “በተወከሉ ሰዎች” እንደነበር አስታውሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ችግር” ሲሉ የጠሩት ይህ አሰራር፤ “እስከ ተወሰነ ጊዜ” በደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎችም ይተገበር እንደነበር ገልጸዋል። የብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተ በኋላ ይሄ አሰራር “ትክክል አይደለም” በሚል እንዲቀር ቢደረገም፤ አሁንም ቢሆን በክልሎች “ነጻነት ላይ” ጥያቄ እንደሚነሳ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።
“ትላንት በስራ አስፈጻሚ [ኮሚቴ] በነበረን ግምግማ ላይ፤ ‘ነጻነት በዛ’፣ ‘ክልሎች ልቅ ሆኑ’፣ ‘ትንሽ ሰብሰብ ማድረግ ያስፈልጋል’ የሚል ሃሳብ ይንጸባረቅ ነበር። ምን ማለት ነው? ትላንት ‘አንፈልገውም’፣ ‘ትክክል አይደለም፣ ‘ሰው ራሱን በራሱ ማስተዳደር አለበት። ጣልቃ አንግባበት። በህግ ብቻ እንገናኝ ያልነው’ ጉዳይ፤ እንከን አልባ አይደለም። ችግሮች ስላሉበት፣ ልክ ችግር ስናይ፤ ያን ማረም ሳይሆን፣ ቶሎ ብለን ወደነበርንበት የሚመልስ ቀላል አቋራጭ ይሆናል” ብለዋል አብይ።
ክልሎችን “empower” ማድረግ፤ ሁሉ ነገር “በጠራ ሁኔታ የተሰራ እና የተስተካከለ ማለት አይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ተግባራዊ ሲደረግ “የሚከተሉ ችግሮች” እንዳሉ ጠቁመዋል። ችግሮችን “ለማረም እና ለማረቅ” ተጨማሪ “ትምህርት፣ ዕውቀት እና ስራ” እንደሚያስፈልግም አክለዋል። በገዢው ፓርቲ ውስጥ “የተሰገሰገው ሰው”፤ ለሚቀርብለት “ሃሳብ እና ለፓርቲው የተገዛ መሆኑን ለማረጋገጥ” “ቀጣይነት ያለው ስራ ይጠይቃል” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
“ብልጽግና ተፈጠረ ማለት፣ ትላንትና አጋር የነበሩ ሰዎች እዚህ ገቡ ማለት፣ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆነ ማለት አይደለም። አብሮን የመጣ ባህል፣ አስተሳሰብ፣ አሰራር አለ። ገና ብዙ ስራ የሚፈልግ፤ ገና ብዙ መታረቅ፣ መታረም ያለበት [አለ]” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በገለጻቸው አስገንዝበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)