አቶ ደመቀ መኮንን ከመንግስት እና ከገዢው ፓርቲ ከነበራቸው ኃላፊነት ተሰናበቱ

ላለፉት 11 ዓመታት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ደመቀ መኮንን፤ ከመንግስት እና በገዢው ፓርቲ ከነበራቸው ኃላፊነት መሰናበታቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። አቶ ደመቀ በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትነት በነበራቸው የኃላፊነት ቦታ ላይ፤ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ መተካታቸውን ምንጮቹ አስታውቀዋል።

ላለፉት አራት ዓመታት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ስራን ደርበው ሲሰሩ የቆዩት አቶ ደመቀ፤ ከትላንት በስቲያ ጀምሮ ሲካሄድ በነበረው የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ “በክብር መሸኘታቸውን” ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል። አቶ ደመቀ ከኃላፊነታቸው ተሰናብተው ወደ ተሰብሳቢዎች መቀመጫ ሲያመሩ፤ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከመቀመጫቸው በመነሳት በጭብጨባ ሲቀበሏቸው በፎቶግራፎች ታይቷል።


አቶ ደመቀ ኢህአዴግ ከስሞ ወደ ብልጽግና ፓርቲ ሽግግር ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ፓርቲውን በምክትል ፕሬዝዳትነት ሲመሩ የቆዩ ናቸው። ብልጽግና ፓርቲ በመጋቢት 2014 ዓ.ም ሁለት ምክትል ፕሬዝዳንቶች እንዲኖሩት ውሳኔ ባሳለፈበት የመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤ፤ በድጋሚ ተመርጠው እስከ ስንብታቸው ድረስ በዚሁ የኃላፊነት ቦታ ቆይተዋል። 

ከአቶ አደም ፋራህ ጋር የምክትል ፕሬዝዳትነቱን ኃላፊነት በተጋሩበት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፤ አቶ ደመቀ “አሰናብቱኝ” የሚል ጥያቄ ለፓርቲያቸው ሊያቀርቡ በዝግጅት ላይ እንደነበሩ አስታውቀው ነበር። በፖለቲካ አመራርነት ለ30 ዓመታት መስራታቸውን ያስታወሱት አቶ ደመቀ፤ “እኔ በውስጤ ይበቃኛል የሚለው ፍላጎት በጣም ገዢ ነው” ሲሉ በወቅቱ ስልጣን ለመልቀቅ የነበራቸውን ፍላጎት እንደነበራቸው ገልጸዋል። 

የአቶ ደመቀን በምክትል ፕሬዝዳትነት በዕጩነት መቅረብ ደግፈው በወቅቱ አስተያየት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “አቶ ደመቀ ካሉት እጅግ አስደማሚ ባህሪዎች አንዱ ነገሮችን በእርጋታ፤ በጥሞና የማየት ብቃቱ ነው። አብሬ በሰራሁባቸው አራት አመታት የደመቀ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ነው” የሚል ሙገሳ አቅርበው ነበር። በብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ከተመረጡ በኋላ አቶ ደመቀ ባደረጉት ንግግር፤ “ይህን አገር ወደ በለጠ እና ወደ ተሟላ ለማሻገር ኃላፊነቴን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ” ማለታቸው አይዘነጋም።

የገዢው ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት “በክብር የተሸኙት”፤ የብልጽግና ፓርቲን “የአመራር የመተካካት መርህን እና የአሰራር ስርዓት በመከተል” መሆኑን ፓርቲው ዛሬ ባወጣው መረጃ ገልጿል። ለብልጽግና ፓርቲ ቅርብ በሆኑ ሰዎች ዘንድ፤ የአቶ ደመቀ  ስንብት ለሳምንታት ይታወቅ እንደበር ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]