“በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ላጎደልኩት ነገር ሁሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ” – አቶ ደመቀ መኮንን   

በዛሬው ዕለት ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ የምክትል ፕሬዝዳንት ኃላፊነታቸው የተሰናበቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ በአመራር ዘመናቸው “አጉድየዋለሁ” ላሉት ነገር በይፋ ይቅርታ ጠየቁ። በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን “የሀገረ መንግስት ግንባታ ፈተና” ለመሻገር፤ ሕገ መንግስትን ከማሻሻል ጀምሮ ሌሎች ስብራቶችን ማረም እንደሚያስፈልግም አቶ ደመቀ ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ ይህን ያሉት በብልጽግና ፓርቲ ዛሬ አርብ ጥር 17፤ 2016 በተደረገላቸው የሽኝት መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ይፋዊ የፌስ ቡክ ገጽ የተጋራው የአቶ ደመቀ ንግግር፤ የኢትዮጵያ “ፖለቲካ እና የስልጣን ቅብብሎሽ” ከዚህ ቀደም “በመጠፋፋት” ላይ የተመሰረተ እንደነበር ይጠቅሳል። 

እርሳቸው በነበሩበት የአመራር ዘመን “ከሁሉም በላይ ትልቅ ቦታ” የሚሰጡት፤ ይህ አይነቱ አካሄድ “በትውልድ ቅብብሎሽ እና ስልጡን አግባብ መቀጠል ሲችል” እንደሆነ ምኞታቸውን ገልጸዋል። በዚህ ረገድ በዚህ ዘመን “በጎ ጅምር” እንዳለም በንግግራቸው ጠቁመዋል። የብልጽግና ፓርቲ አቶ ደመቀ ከምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው “በክብር የተሸኙት”፤ የፓርቲውን “የአመራር የመተካካት መርህን እና የአሰራር ስርዓት በመከተል” እንደሆነ አስታውቆ ነበር። 

ፎቶ፦ ብልጽግና ፓርቲ

አቶ ደመቀ ለብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባደረጉት ንግግር፤ ለ31 ዓመት ተኩል በአመራርነት መቆየታቸውን አስታውሰዋል። ከኃላፊነት ለመሰናበት ያቀረቡት ጥያቄ “ክብር እና ዕውቅና” ተሰጥቶት፤ በፓርቲው ተቀባይነት በማግኘቱ ምስጋናቸውን ገልጸዋል። ጥያቄያቸው ምላሽ በማግኘቱም “በጣም ደስተኛ ነኝ። በጣም ዕድለኛ ነኝ” ሲሉም ተደምጠዋል።

ላለፉት አራት ዓመታት አቶ ደመቀ በምክትል ፕሬዝዳንትነት የመሩት ብልጽግና ስምንት የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማዋሀድ የተመሰረተ ነው። ሶስት የቀድሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አባል እና አምስት አጋር ፓርቲዎች ብልጽግናን የሚያቋቁም ስምምነት በህዳር 2012 ሲፈራረሙ፤ የቀድሞው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (አዴፓ) የወከሉት አቶ ደመቀ ነበሩ። አቶ ደመቀ የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ለሰባት ዓመታት ሰርተዋል።

ተሰናባቹ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ከዚህ ቀደም ጥያቄ አቅርበው እንደነበር፤ በመጋቢት 2014 ዓ.ም. በተካሄደው የፓርቲው የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ መገለጹ አይዘነጋም። አቶ ደመቀ በወቅቱ “እኔ በውስጤ ይበቃኛል የሚለው ፍላጎት በጣም ገዢ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር።

ሶስት አስርት ዓመታት የተሻገረው የአመራር ጉዟቸው “ስኬቶችን እና ፈተናዎችን” ያዩበት እንደነበር አቶ ደመቀ ዛሬ ለፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ባደረጉት ንግግር መለስ ብለው አስታውሰዋል። በስልጣን ላይ የቆዩባቸው ዓመታት “ከጊዜ ወደ ጊዜ የአመራርን ዋጋ እና የኃላፊነት ሚዛን እየተገነዘብኩ እንድሄድ ያደረገኝ ነው” ሲሉም አክለዋል።

“እኔ በተሰማራሁባቸው፣ የኃላፊነት ደረጃዎች፣ አመራር በሰጠሁባቸው ጊዜያት እና ውሎዎች የተማርኩት ነገር ቢኖር ምን ያህል ጽኑ ህዝብ እና ብርቱ አገር ያለን መሆኑን ነው” ሲሉ በዛሬው የሽኝት መርሃ ግብር ላይ የተናገሩት አቶ ደመቀ፤ “ይህን አገርና ህዝብ የሚመጥን አመራር በየደረጃው መገንባት እጅግ ተገቢ ነው” ሲሉ በአጽንኦት አስገንዘበዋል። በዚሁ  ንግግራቸው ላይም “በዚህ ረጅም የአመራር ዘመን፤ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ላጎደልኩት ሁሉ ነገር ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለዋል።  

ኢትዮጵያ “በለውጥ ተስፋ ላይ” መሆኗን በንግግራቸው ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሆኖም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉት የሰላም እጦቶች እንዲሁም “ሞት፣ መፈናቀል፣ የማህበራዊ መስተጋብር ምስቅልቅል” አይነት ፈርጀ ብዙ ጉዳቶች “በእጅጉ ልብ የሚሰብሩ” መሆኑን ገልጸዋል። ከእነዚህ ችግሮች ለመውጣት “መደማመጥ፣ የሃሳብ ተግባቦት መፍጠር፣ መተማመን እና ከችግሮች በላይ የሆነ ሁነኛ መፍትሄ መሻት እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉም አሳስበዋል።

“እኔ በተሰማራሁባቸው፣ የኃላፊነት ደረጃዎች፣ አመራር በሰጠሁባቸው ጊዜያት እና ውሎዎች የተማርኩት ነገር ቢኖር፤ ምን ያህል ጽኑ ህዝብ እና ብርቱ አገር ያለን መሆኑን ነው”

– አቶ ደመቀ መኮንን

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በተጨማሪ፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አጋጥሟታል ያሉትን “የሀገረ መንግስት ግንባታ ፈተና ለመሻገር” መደረግ አለባቸው ያሏቸውን እርምጃዎች በንግግራቸው ጠቁመዋል። አቶ ደመቀ በመፍትሔነት ካነሷቸው ሃሳቦች መካከል “ሕገ-መንግሥትን ማሻሻል” እና “ሌሎች ስብራቶችን ማረም” የሚለው ይገኝበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)