በጦርነት ሳቢያ ከተቋረጡ 64 መንገዶች፤ 15ቱ ብቻ ግንባታቸው መቀጠሉን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ 

በሚራክል ልደቱ

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ከተቋረጡ 64 የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው የቀጠለው አስራ አምስቱ ብቻ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አብዱራህማን አስታወቁ። ከተቋረጡት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ 39 የሚሆኑት “ከፍተኛ የሆነ ጉዳት” ስለደረሰባቸው፤ በድጋሚ ወደ ጨረታ ሂደት እንዲገቡ መደረጋቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። 

አቶ መሐመድ ይህን ያሉት የተቋረጡ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው። ጥያቄዎቹ በተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተነሱት፤ የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የመንፈቅ የስራ አፈጻጸሙን ለፓርላማ ባቀረበበት ስብሰባ ላይ ነው።

ዛሬ ማክሰኞ ጥር 21፤ 2016 ዓ.ም. በተካሄደው በዚሁ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጥያቄ ካቀረቡ የፓርላማ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሀብተማርያም መኮንን፤ የኦሮሚያ፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎችን የሚያገናኘው የአገር አቋራጭ መንገድ ፕሮጀክት ግንባታው የቆመበትን ምክንያት ጠይቀዋል። ከ1980ዎቹ ጀምሮ “ከህዝብ ጥያቄ ሲቀርብበት ነበር” የተባለው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት፤ ከአለም ከተማ – ሰቆጣ – አቢ አዲ ድረስ የሚገነባ ነው።

“መንግስት ይህንን የረጅም ዓመት የህዝብ ጥያቄ ከግምት ውስጥ በማስገባት መንገዱን በተለያዩ ፕሮጀክቶች ‘በሎት’ በመከፋፈል ግንባታ ተጀምሮ ነበር። ነገር ግን በሀገራችን በሰሜኑ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት የተነሳ በ2013 ዓ.ም. መንገዶቹ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጠዋል” ሲሉ የፓርላማ አባሉ ተናግረዋል። እነዚህን የመንገድ ፕሮጀክቶች በበላይነት የሚያሰራው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፤ ላለፉት ሶስት ዓመታት ግንባታቸውን “ማስቀጠል ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው?” ሲሉ አቶ ሀብተማርያም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በተለያዩ ክፍሎች ተከፋፍሎ ከሚሰራው ከዚህ መንገድ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ግንባታቸው የተቋረጠው አራቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። የመንገዶች አስተዳደር የእነዚህን የመንገድ ግንባታ ኮንትራት ያቋረጠበት ምክንያት፤ ፕሮጀክቶቹ በደረሰባቸው “ከፍተኛ ጉዳት” መሆኑንም ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በጦርነቱ “ከፍተኛ መጠን ያለው ጉዳት የደረሰባቸው” መንገዶች ብዛት 39 መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። እነዚህን ፕሮጀክቶችን መልሶ “ወደ ግንባታ ሂደት ማስገባቱ አዳጋች” መሆኑን የገለጹት አቶ መሐመድ፤ እርሳቸው የሚመሩት መስሪያ ቤት ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንደ አማራጭ የወሰደው ስትራቴጂ ለፕሮጀክቶቹ በድጋሚ ጨረታ ማውጣት መሆኑን ተናግረዋል። 

“በዚህም መሰረት 17 ፕሮጀክቶችን ዘንድሮ በጨረታ አግባብ ስራቸው እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስችል የዲዛይን ዝግጅት አድርገናል። የጨረታ ሰነድ ዝግጅት አጠናቅቀናል። ከዚህም ባሻገር ፕሮጀክቶቹ ጨረታ ላይ እንዲውሉ አድርገናል” ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ለፓርላማ አባላቱ አብራርተዋል። በዚህ የአስተዳደሩ አካሄድ ተጠቃሚ ከሆኑት ፕሮጀክቶች መካከል፤ የአለም ከተማ – ሰቆጣ – አቢ አዲ መንገድ አካል የሆኑ እንደሚገኙበትም አክለዋል። 

የእዚህ አገር አቋራጭ መንገድ ፕሮጀክት አካል ከሆኑት ውስጥ ከጉጉፍቱ – ወረኢሉ- ደጎሎ ያለው ክፍል በአሁኑ ወቅት “የጨረታው ሂደት እየተፋጠነ ነው” ያሉት አቶ መሐመድ፤ ከተንታ መገንጠያ – ኩርባ መገንጠያ –  ተንታ ድረስ ያለው  መንገድም በተመሳሳይ መልኩ “በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ” አስታውቀዋል። “እነዚህ ፕሮጀክቶች ዘንድሮ ወደ እንቅስቃሴ እንዲገቡ እናደርጋለን በሚል ዕቅድ አዘጋጅተን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን” ሲሉም የመንገድ ፕሮጀክቱን በዚህ ዓመት ወደ ግንባታ ለመመለስ እየተደረገ ያለውን ጥረት አመልክተዋል። 

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በአጭር ጊዜ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ጥቆማ ቢሰጡም፤ እስከዚያው ድረስ መንገዶቹ “ለትራንስፖርት ምቹ እንዲሆኑ” ለምን እንዳልተደረገ ጥያቄ ቀርቧል። ግንባታቸው ተጀምሮ የተቋረጡት የመንገድ ፕሮጀክቶች “መቆፋፈራቸውን”፣ “ዝናብ ሲጥልም ለመንቀሳቀስ የማያስችሉ” መሆናቸውን ያነሱት አቶ ሀብተማርያም የተባሉት የፓርላማ አባል፤ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ይህን ችግር ለመፍታት “ምን እንዳሰበ” ጥያቄ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር፤ በአገር አቋራጭ መንገዱ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች “ከተቋረጡበት ጊዜ ጀምሮ” በትራፊክ ፍሰት ላይ “ችግር እንዳይፈጥሩ” የጥገና ስራ ሲከወናወን መቆየቱን በመጥቀስ ለጥያቄው ምላሽ ሰጥተዋል። ጥገናው “ከፍተኛ ሊባል የሚችል” መሆኑን የገለጹት አቶ መሐመድ፤ ይኸው የጥገና ስራ ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን  ተናግረዋል።     

በጥገና እና በጨረታ ሂደት ላይ ካሉ የተቋረጡ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ግንባታ ስለተመለሱ ፕሮጀክቶችም በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያ ላይ ተነስቶ ነበር።  በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በግንባታ ላይ በነበሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የደረሰው ጉዳት “ተመሳሳይ አልነበረም” ያሉት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር፤ “አንዳንዶቹ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ጉዳት ደርሶብናል። አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ላይ ግን የደረሰው መለስተኛ ወይም ዝቅተኛ የሚባል [ነው]” ሲሉ ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል። 

ከእነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል በአስራ አምስቱ ላይ የደረሰው ጉዳት፤ ግንባታውን “መልሶ ማስቀጠል የሚያስችል” መሆኑንም አቶ መሐመድ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር እነዚህን 15 ፕሮጀክቶች መልሰው ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረጉንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)