የግል መገናኛ ብዙሃን የፍትህ ሚኒስትሩ ለፓርላማ ያቀረቡትን ሪፖርት እንዳይዘግቡ ተደረገ

በተስፋለም ወልደየስ

የፍትህ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ለፓርላማ ያቀረበውን የግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፤ የግል መገናኛ ብዙሃን እንዳይዘግቡ ተደረገ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዛሬውን መደበኛ ስብሰባ እንዲዘግቡ ፍቃድ የሰጠው ለአምስት መገናኛ ብዙሃን ብቻ ነው። 

የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት፤ የፓርላማ አባላት አሊያም በፌደራል የሕግ አስፈጻሚ የሆነ አካል “በዝግ ስብሰባ እንዲደረግ” ጥያቄ ካላቀረቡ በስተቀር፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎች “በግልጽ እንደሚካሄዱ” ይደነግጋል። “በዝግ ስብሰባ” እንዲደረግ ጥያቄ በሚቀርብበት ወቅትም ቢሆን፤ ከፓርላማ አባላት ውስጥ “ከግማሽ በላይ” ድጋፍ ሊያገኝ እንደሚገባ በሕገ መንግስቱ ላይ ተቀምጧል።

የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛም ሆነ ልዩ ስብሰባዎቹን በዚህ አግባብ ከማከናወን አልፎ፤ በማህበራዊ የትስስር ገጾቹ በቀጥታ ስርጭት ሲያቀርብ ቆይቷል። ከምክር ቤቱ ፍቃድ የተሰጣቸው መገናኛ ብዙሃን እነዚህን ስብሰባዎች ያለ ምንም ገደብ ሽፋን የሚሰጡ ቢሆንም፤ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ግን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢን ጨምሮ በመደበኛ ስብሰባው ለመገኘት ጥያቄ ያቀረቡ የግል መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ፍቃድ ሳያገኙ ቀርተዋል።

በዛሬው ሰብሰባ ተለይተው እንዲገቡ የተደረጉት፤ ሶስት የመንግስት እና ሁለት ለመንግስት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙሃን ብቻ ናቸው። በዝግ ባልተካሄደው በዛሬው ስብሰባ፤ የፍትህ ሚኒስቴርን የመንፈቅ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ናቸው። ሚኒስትሩ በዚሁ ሪፖርታቸው፤ የተሰጠው ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ ቀናት በቀሩት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የታሰሩ ተጠርጣሪዎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ ማንሳታቸው ተገልጿል። 

በባህር ዳር፣ በጎንደር እና በኮምቦልቻ ከተሞች በሚገኙ “የማቆያ ስፍራዎች” ከታሰሩ ተጠርጣሪዎች ውስጥ፤ የ706ቱ “የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ” ተመርምሮ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ ዕዝ መቅረቡን መናገራቸውን ከተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል። በአማራ ክልል በዋነኛነት ተፈጻሚ እንዲሆን የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ እንዲያስፈጽም የተቋቋመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነው።

በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የሚመራው ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተዘረዘሩ እርምጃዎችን በተመለከተ “አስፈላጊውን ውሳኔ የማስተላለፍ እና የማስፈጸም” ስልጣን የተሰጠው ነው። በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር “ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ” መሆኑን ተከትሎ፤ የፌደራል መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገው ሐምሌ 28፤ 2015 ዓ.ም. ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)