የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማራዘም የተወካዮች ምክር ቤት ለነገ “ልዩ ስብሰባ” ጠራ 

በተስፋለም ወልደየስ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ አርብ ጥር 24፤ 2016 በሚያካሄደው ልዩ ሰብሰባው፤ ለስድስት ወራት ታውጆ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያራዝም ነው። ምክር ቤቱ በነገው ስብሰባው ሌሎች አራት አጀንዳዎችንም ይመለከታል።

የተወካዮች ምክር ቤት በዋነኛነት በአማራ ክልል ተፈጻሚ እንዲሆን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያጸደቀው ነሐሴ 8፤ 2015 ነበር። ለስድስት ወራት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀነ ገደብ በዛሬው ዕለት መጠናቀቁን ተከትሎ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለነገ “ልዩ ስብሰባ” መጥራቱን አራት የፓርላማ አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የፓርላማ አባላቱ ለነገው ስብሰባ አጀንዳ የተላከላቸው፤ ዛሬ ምሽት አንድ ሰዓት ገደማ እንደነበር አንድ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ለልዩ ሰብሰባው ከተያዙ አምስት ጉዳዮች መካከል፤ በአጀንዳው ዝርዝር ላይ በቀዳሚነት የተቀመጠው “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማራዘም” የሚለው እንደሆነ እኚሁ አባል ጠቁመዋል። 

ይህንኑ የተመለከተ የውሳኔ ሃሳብ ለተወካዮች ምክር ቤት ከቀረበ በኋላ፤ የፓርላማ አባላቱ ጉዳዩን መርምረው እንዲያጸድቁ በአጀንዳ መያዙን ሶስት የፓርላማ አባላት አረጋግጠዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም በአጀንዳው ቢገለጽም፤ “ለምን ያህል ጊዜ ይራዘማል?” የሚለውም ሆነ የውሳኔ ሃሳቡ ዝርዝር ለፓርላማ አባላቱ እንዳልተገለጸላቸው አስረድተዋል። 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28፤ 2015 ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ውሳኔ ያሳለፈው፤ በክልሉ እየተካሄደ ነው ያለውን “በትጥቅ የተደገፈ ህገወጥ እንቅስቃሴ”፤ “በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ መሸጋገሩን” በመጥቀስ ነው። በዚህም ምክንያት “የህዝብን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ” እንዲሁም “ህግ እና ስርዓት ለማስከበር” የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ መታወጁን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በወቅቱ አስታውቆ ነበር።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸሙን የሚከታተል ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አቋቁሟል። በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ የሚመራው ይህ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ፤ በአማራ ክልል መንግስት ስር የሚገኙ የህግ አስከባሪ አካላትን “በአንድ ዕዝ ስር አድርጎ፣ በበላይነት የማስተባበር እና የመምራት” ስልጣን የተሰጠው ነው።


ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ የአማራ ክልልን በአራት “ኮማንድ ፖስት” በመክፈል፤ “ህግ እና ስርዓት የማስከበር ስራዎችን” ሲያከናወን መቆየቱን በየጊዜው ሲያስታውቅ ነበር። እነዚህ ኮማንድ ፖስቶች “ምዕራብ አማራ”፣ “ሰሜን ምዕራብ አማራ”፣ “ምስራቅ አማራ” እና “ማዕከላዊ ሸዋ” የሚሉ መጠሪያዎችን የያዙ ናቸው።

በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገጉ ምክንያት የሆነው፤ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የጸጥታ መድፍረሶች መከሰታቸውን ተከትሎ ነው። በክልሉ የጸጥታ ችግር የተከሰተው፤ የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ኃይሎችን “መልሶ ለማደራጀት” ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ነበር። በዚህ ወቅት የክልሉን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ የወረዳ እና የዞን ባለስልጣናት በታጣቂዎች ተገድለዋል።  

ይህንን ተከትሎ በወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ፤ በአማራ ክልል ያጋጠመው “የጸጥታ መደፍረስ” “በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች” መሆኑን በመግለጽ ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ደብዳቤ ጽፈዋል። ዶ/ር ይልቃል በዚሁ ደብዳቤያቸው፤ የፌደራል መንግስት በህገ መንግስቱ መሰረት “ተገቢውን እርምጃ” እንዲወስድ ጥያቄ አቅርበው ነበር። ርዕሰ መስተዳድሩ ጥያቄውን ካቀረቡ ከአንድ ቀን በኋላ ስብሰባውን ያደረገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]