ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች፤ በመጪው ማክሰኞ ምላሽ ሊሰጡ ነው    

በተስፋለም ወልደየስ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች፤ በመጪው ሳምንት መጀመሪያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ምላሽ እና ማብራሪያ እንደሚሰጡ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የፓርላማ አባላቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን አስገብተው ያጠናቀቁት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ነው።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የፓርላማ አባላት፤ ጥያቄዎችን እንዲያቀርቡ የተሰጣቸው ቀናት ብዛት ሶስት ብቻ እንደነበር ገልጸዋል። በዚህም መሰረት የፓርላማ አባላቱ ከባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ጥር 18 ጀምሮ እስከዚህ ሳምንት ሰኞ ጥር 20 ድረስ ጥያቄዎቻቸውን ማስገባታቸውን አስረድተዋል።

በ2008 ዓ.ም የወጣው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ፤ “ማንኛውም የቃል መልስ የሚፈልግ ጥያቄ የሚያቀርብ አባል፤ ጥያቄውን ቢያንስ ከአስር ቀናት በፊት ለአፈ ጉባኤው በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት” ሲል ይደነግጋል። የፓርላማው አፈ ጉባኤ፤ ከምክር ቤቱ አባላት የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች መርምረው የመቀበል ወይም ውድቅ የማድረግ ስልጣን በደንቡ ተሰጥቷቸዋል። 

ፓርላማው እስካሁን ሲከተለው በቆየው አሰራር መሰረት፤ አፈ ጉባኤው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን የመለየት ስራ የሚያከናውኑት በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ከሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ጋር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት የሚያቀርቡትን ምላሽ እና ማብራሪያን ጨምሮ፤ “የተወካዮች ምክር ቤት የሚወያይበትን ማንኛውም አጀንዳ የመቅረጽ” ኃላፊነት ያለበት ደግሞ “የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ” ነው።

ይህ አማካሪ ኮሚቴ በፓርላማው አፈ ጉባኤ የሚመራ ሲሆን፤ ምክትል አፈ ጉባኤ፣ የፓርቲ ተጠሪዎችን ጨምሮ የምክር ቤቱ የፓርላማ ቡድኖች “ባላቸው መቀመጫ መጠን የሚወከሉበት” መሆኑ በምክር ቤቱ የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ ላይ ሰፍሯል። በአማካሪ ኮሚቴው ከተካተቱ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ውስጥ፤ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ጥር 22፤ 2016 ዓ.ም. በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ይገኙበታል። 

ዶ/ር ደሳለኝ ከመታሰራቸው ቀናት አስቀድሞ፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ሲያዘጋጁ መመልከታቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የቤተሰባቸው አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር። “በአራት ገጾች የተዘጋጁ ናቸው” የተባሉት እነዚህን ጥያቄዎች፤ ዶ/ር ደሳለኝ ለተወካዮች ምክር ቤት ማስገባታቸውን ሲናገሩ መስማታቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ባለፈው ሰኔ ወር በተካሄደ ተመሳሳይ የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንከር ያለ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል። ከባህር ዳር ምርጫ ክልል የተመረጡት የፓርላማ አባሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልጣን እንዲያስረክቡ እና ፓርላማው እንዲበተን ሃሳብ አቅርበው ነበር። 

ይህ የሰኔ ወር የፓርላማ ጥያቄ እና መልስ ስብሰባ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓመት ውስጥ በተወካዮች ምክር ቤት ፊት መቅረብ ከሚጠበቅባቸው ሶስት ዋነኛ መድረኮች አንዱ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰኔ እና በዓመቱ አጋማሽ በፓርላማ የሚቀርቡት፤ የፌደራል መንግስትን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ለመስጠት ነው። 

በዓመቱ የመጀመሪያ ወራት የሚከናወነው ሌላኛው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ስብሰባ፤ ደግሞ የፌደራል መንግስትን ዓመታዊ እቅድ በተመለከተ ማብራሪያ እና ገለጻ የሚያቀርቡበት ነው። ይህ ማብራሪያ፤ የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት በተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ዓመታዊ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ በሚያቀርቡት የፌደራል መንግስት ዕቅድ ላይ በፓርላማ  አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች የሚሰጥ ነው። 

የ2016 በጀት ዓመት የመንግስትን ዕቅድ በተመለከተ ለቀረቡ ጥያቄዎች፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በፓርላማ በመገኘት ምላሽ የሰጡት ከሁለት ወር በፊት ህዳር 4፤ 2016 ነበር። ቀጣዩ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ፤ በመጪው ማክሰኞ ጥር 28፤ 2016 የሚካሄድ መሆኑን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ከዚህ ስብሰባ ሁለት ቀናት በኋላ የፓርላማ አባላቱ ለዕረፍት የሚበተኑ ይሆናል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)