በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘም “በጥልቅ ያሳስበኛል” አለ  

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ፤ በዋነኛነት በአማራ ክልል ተፈጻሚ ሲደረግ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘም “በጥልቅ ያሳስበኛል” አለ። ኤምባሲው ስጋቱን የገለጸው፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት አርብ ለስድስት ወራት ተግባራዊ ሲሆን የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ በሁለት ተቃውሞ እንዲራዘም መወሰኑን ተከትሎ ነው። 

ይህ የፓርላማው ውሳኔ፤ በሐምሌ 2015 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕድሜ በድምሩ ወደ አስር ወራት ያራዘመ ሆኗል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ ዛሬ ቅዳሜ ጥር 25፤ 2016 ባስተላለፉት መልዕክት “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም እንደ ረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ወዳጅ በጣም ያሳስበናል” ብለዋል። 

በኤምባሲው የፌስቡክ እና የኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ይፋዊ ገጾች በተሰራጨው በዚሁ መልዕክት፤ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎችን የተከሰቱትን ጨምሮ “ውስብስብ የፖለቲካ እና የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ብቸኛው መንገድ ውይይት” እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህንን የአምባሳደሩን አቋም፤ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀን ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመርም ከዚህ በፊት ሲያስተጋቡት ቆይተዋል።  ልዩ ልዑኩ ባለፉት ወራት ወደ ኢትዮጵያ ያደረጓቸው ጉዞዎች፤ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተፈጠሩ ግጭቶች “በውይይት እንዲፈቱ ግፊት የማድረግ” ዓላማን አንግበው እንደሆነ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ማስታወቁ አይዘነጋም።

ሞሊ ፊ የሚመሩት ቢሮ ይህን አቋሙን የገለጸው፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በአዋጁ ተግባራዊ የሚደረጉ “የአስቸኳይ ጊዜ ስልጣኖች” መራዘም “እጅግ አሳሳቢ” እንደሆነ መግለጻቸውን ተከትሎ ነው። አዋጁ “በግጭት ተጎጂዎች”፣ “በሰብዓዊ ቀውስ” እንዲሁም “ከክስ በፊት የተጠርጣሪዎች ለረዥም ጊዜ መታሰርን” ጨምሮ “በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚኖረው አንድምታ” ኢሰመኮን የሚሳሰበው እንደሆነ ዶ/ር ዳንኤል ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ ይህን መልዕክታቸውን በይፋዊ የኤክስ ገጻቸው ያሰፈሩት፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘመን በተመለከተ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ ከማጽደቁ አንድ ቀን አስቀድሞ ነው።ብሔራዊውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የሚመሩት ዶ/ር ዳንኤል በዚሁ መልዕክታቸው፤ “የተወካዮች ምክር ቤት እና መንግስት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት፣ ሕጋዊነት እና ተመጣጣኝነት በቅጡ እንዲያጤኑ” ጥሪ አቅርበው ነበር። ኮሚሽነሩ መልዕክታቸውን የደመደሙት “ውይይት ቁልፍ ነው” በሚል ማሳረጊያ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)