“ሶስት አይደለም አስር [ሀገር] ቢደመር ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይችልም” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት፤ ከሀገሪቱ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባችው ሶማሊያን “እንደ proxy መጠቀም” የሚፈልጉ “ኃይሎች” መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። “የሶማሊያ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የመጋጨት ፍላጎት ያለው አይመስለኝም” ያሉት አብይ፤ እርሳቸው የሚመሩት መንግስት ተመሳሳይ አቋም እንዳለው በድጋሚ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሰሞነኛውን ኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ውዝግብ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት፤ በዛሬው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው የጥያቄ እና መልስ ቆይታ ላይ ነው። የሁለቱን ሀገራት ወቅታዊ ሁኔታ እና የመግባቢያ ስምምነቱ በተመለከተ ጥያቄ ካቀረቡ የፓርላማ አባላት ውስጥ፤ ከአማሮ ኬሌ ምርጫ ክልል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህን (ኢዜማ) ወክለው የህዝብ ተወካዮችን ምክር ቤትን የተቀላቀሉት ዶ/ር አወቀ አምዛዬ አንዱ ናቸው።

ዶ/ር አወቀ “ውስብስብ፣ ውጫዊ፣ አካባቢያዊ ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች” ባየሉበት በዚህ ወቅት፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት “ቁርጠኝነት እና ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ” እንደሆነ ገልጸዋል። የፓርላማ አባሉ ለዚህ በማሳያነት የጠቀሷቸው ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ጎረቤት ሱዳን ያለውን “ብጥብጥ”፣ “የእስራኤል ፍልስጤም ወረራን” እንዲሁም በየመን የሁቲ አማጽያን “በባብ ኤል መንደብ እና በቀይ ባህር በሚተላለፉ የምዕራባውያን መርከቦች” ላይ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች ነው።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት “የመጀመሪያው አይደለም” ያሉት ዶ/ር አወቀ፤ ሀገሪቱ “የበርበራ ወደብን ለማልማት እና ለማስተዳደር” የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ንብረት ከሆነው “ዲፒወርልድ” ጋር ከስምንት ዓመት ገደማ በፊት ውል ገብታ እንደነበር አስታውሰዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ ኢትዮጵያ ሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት “እውቀት፣ ጥበብ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ የሚሰራ” ሊሆን እንደሚገባ ዶ/ር አወቀ ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት፤ የራስ ገዝ አስተዳደሯ “ከሌሎች ሀገሮች ጋር ከፈጠረቻቸው ግንኙነቶች የተለየ አለመሆኑን” የፓርላማ አባሉ ተናግረዋል። በርካታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት ለሶማሌላንድ እውቅና ባይሰጡም “በሐርጌሳ አገናኝ የዲፕሎማቲክ ጽህፈት ቤቶች አላቸው” ያሉት ዶ/ር አወቀ፤ ሶማሌላንድም ከ20 በማያንሱ የተመድ አባል ሀገራት “የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች” እንዳሏት አስረድተዋል።

ሶማሌላንድ የቀደሙ ስምምነቶች ስታደርግም ሆነ ግንኙነት ስትመስርት፤ ከሶማሊያም ሆነ ከሌሎች አካላት “ያልተነሳው ጩኸት” “አሁን ምን አዲስ ነገር ተፈጥሮ በዚህ ሁኔታ በረከተ?” ሲሉ የፓርላማ አባሉ ጥያቄ አቅርበዋል። በኢትዮጵያ መንግስት በኩል “ይኸ ጩኸት ሊከሰት እንደሚችል ተገምቶ ምን ዝግጅት ተደርጎ ነበር?” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ጠይቀዋል።

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

ዶ/ር አወቀ የጠቀሱትን የመግባቢያ ስምምነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ታህሳስ 22፤ 2016  ከተፈራረሙ በኋላ ሶማሊያ ብርቱ ተቃውሞዋን ስታሰማ ቆይታለች። ጉዳዩን እስከ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት የወሰደው የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ መንግስት፤ የመግባቢያ ስምምነቱን “ሕጋዊ ተቀባይነት የሌለው እና የማይሰራ ነው” ሲል አጣጥሎታል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ አስመራ እና ካይሮ ባደረጓቸው ጉዞዎች፤ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የመግባቢያ ስምምነቱን የነቀፈችው ግብጽ፤ ከሶማሊያ ጎን እንደምትቆም ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ተናግረዋል። አልሲሲ ከሶማሊያው አቻቸው ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ግብጽ ማንም ወገን ሶማሊያንም ሆነ ደህንነቷን እንዲያሰጋ አትፈቅድም” የሚል ማስጠንቀቂያ ያዘለ መልዕክት አስተላልፈው ነበር።

ዶ/ር አወቀ በዛሬው ጥያቄያቸው መንደርደሪያ ላይ የመግባቢያ ስምምነቱ የተፈረመበት ወቅት፤ “ከህዳሴ ግድብ ጋራ በተገናኘ” ግብጽ ኢትዮጵያን ለመጉዳት “አሁንም እያሴረች ባለችበት ሁኔታ” የተፈረመ መሆኑን ገልጸው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከፓርላማ አባሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ በስም የጠቀሱት ሀገርም ይሁን ወገን ባይኖርም፤ “ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች ሶማሊያን እንደ proxy መጠቀም ይፈልጋሉ” ሲሉ ተደምጠዋል። 

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

“የሶማሊያ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የመጋጨት ፍላጎት ያለው አይመስለኝም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ በኢትዮጵያ በኩልም ተመሳሳይ አቋም እንዳለ አስታውቀዋል። አብይ በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያቸው “የሶማሊያ ወንድሞቻችን ላይ ምንም ዓይነት የከፋ ነገር ለመናገርም፤ ለማድረግም ዝግጁ አይደለንም” ብለዋል። ሆኖም ሶማሊያን መጠቀሚያ ማድረግ ይፈልጋሉ ያሏቸው ኃይሎች “ለአንዳንድ የዲያስፖራ ወንድሞቻችን ሚዲያ እንደከፈቱላቸው ሁሉ ለአንዳንድ የሶማሊያ ወንድሞቻችን የተወሰነ ነገር ሊያደርጉላቸው ይችላሉ” ሲሉ ወንጅለዋል።

እንዲያም ቢሆን ግን እነዚህ ኃይሎች ሁለቱን ሀገራት “ሊያዋጉ እንደማይችሉ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል። “ቢያንስ በእኛ በኩል አንዋጋም” የሚል አቋማቸውንም በድጋሚ ተናግረዋል። “አቧራው ጨሰ ማለት የሚፈልጉ ሀገሮች አሉ። ከእኛ ተምረው መሰለኝ” በማለት የፓርላማ አባላቱን ፈገግ ያስባሉት አብይ፤ “የምንፈልገው ልማት ብቻ ነው። ግርግር አንፈልግም” ሲሉ የመግስታቸውን አቋም አስታውቀዋል። 

“ኢትዮጵያ በታሪኳ ማንንም ሀገር ወርራ አታውቅም። ማንም ሀገር ወሯት ግን አሸንፏት አያውቅም” ያሉት አብይ፤ “ሶስት አይደለም አስር ቢደመር ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይችልም” ሲሉ የፓርላማ አባላቱ ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ አሳስበዋል። “እኛ አንዋጋም፤ አንፈልግም። ወደዚህ ከመጣ ደግሞ አይችልም” የሚል ማስተማመኛም ለፓርላማ አባላቱ ሰጥተዋል። 

ፎቶ፦ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አሚሶም)

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ገለጻቸው፤ ኢትዮጵያ እና መንግስታቸው ለሶማሊያ መረጋጋት የተጫወቱትን ሚና አለፍ አለፍ እያደረጉ ጠቃቅሰዋል። “የሶማሊያን ሰላም ለማስከበር በሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሞተዋል” ያሉት አብይ፤ “ሶማሊያ ውስጥ የምንሞተው የሶማሊያ ሰላም የእኛ ሰላም ስለሆነ ነው። የሶማሊያ ልማት የእኛ ልማት ስለሆነ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። መንግስታቸው “ሶማሊያ ጠንክራ፣ አድጋ፣ በልጽጋ፣ ለኢትዮጵያ ትልቅ ገበያ ሆና፤ ከኢትዮጵያ ተጠቅማ፤ ኢትዮጵያን ጠቅማ ማየት” እንደሚፈልግም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም በነበረ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ስለ ቀይ ባህር በተነጋገሩ “ማግስት”፤ መንግስታቸው “በሺህ የሚቆጠሩ የሶማሊያ መንግስት ወታደሮችን” በሁርሶ ወታደራዊ ማስልጠኛ ማዕከል “አሰልጥኖ መላኩን” አብይ አስታውሰዋል። “በውስጣችን ክፋት ካለ እንዴት ወታደር ሁርሶ አሰልጥነን ወደዛ እንልካለን?” ሲሉም ጥያቄ አዘል አስተያየት አስደምጠዋል። “ሶማሌላንድ እና ሶማሊያን ለማገናኘት ብዙ ጥረት አድርገናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “ነገም ሶማሌላንድ እና ሶማሊያ ቢስማሙ የመጀመሪያው ተደሳች ሀገር ኢትዮጵያ ናት” ብለዋል።

ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት፤ ለንግድ እና ወታደራዊ የጦር ሰፈር ለማቋቋም የሚያስችል የባህር ወደብ ለኢትዮጵያ የሚሰጥ ነው። ሶማሌላንድ በምላሹ ከኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቆም የሚያስችላትን እውቅና እንደምታገኝ የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙት የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት በወቅቱ ተናግረው ነበር። የመግባቢያ ስምምነቱ ቀጣይ ድርድር በአንድ ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ከዚህ ቀደም ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፤ የተባለው ቀነ ገደብ ካለፈ ከሳምንት በኋላ ከሁለቱ ወገኖች በጉዳዩ ላይ የወጣ አዲስ መረጃ የለም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)