በስራ ላይ ላሉ መምህራን “ልዩ የአቅም ማጎልበቻ” ስልጠና በመጪው ክረምት ሊሰጥ ነው

በሚራክል ልደቱ

ትምህርት ሚኒስቴር በስራ ላይ ላሉ መምህራን፤ “ልዩ የአቅም ማጎልበቻ” ስልጠና በመጪዎቹ የክረምት ወራት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። ስልጠናው መምህራን ባሉበት የትምህርት ደረጃ እና በሚያስተምሩት የትምህርት አይነት ስነ ዘዴ ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል። 

ሚኒስቴሩ ይህን ያስታወቀው፤ መምህራንን እና የትምህርት ቤት አመራሮችን በተመለከተ ስላዘጋጃቸው መመሪያዎች፤ ትላንት አርብ የካቲት 1፤ 2016 በዋና መስሪያ ቤቱ ስብሰባ አዳራሽ ባደረገው የህዝብ ውይይት ላይ ነው። መመሪያዎቹ የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን የደረጃ እድገት አፈጻጸም፣ የትምህርት ቤት አመራሮች ምልመላ እና ምደባ እንዲሁም የእጩ መምህራን ምልመላ እና መረጣን የሚመለከቱ ናቸው።

ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን ባለፉት ሶስት ዓመታት እንደተዘጋጁ የተነገረላቸው እነዚህ መመሪያዎች፤ በኢትዮጵያ ያለውን “የትምህርት ጥራት ውድቀት ችግርን ሊያስተካክል የሚችል ሃሳቦችን የያዙ” መሆኑ በስብሰባው ላይ ተነስቷል። አዲሶቹ መመሪያዎች ከዚህ ቀደም ከመምህራን እና ከትምህርት ቤት አመራሮች ምደባ ጋር ተያይዞ የነበረውን “የፖለቲካ ተጽዕኖ” ከማስቀረት በተጨማሪ “የተጠያቂነት ስርዓትን” ለማስፈን ጉልህ አስተዋጽኦ የሚኖራቸው መሆኑ ተገልጿል። 

መመሪያዎቹ ብቃት ያላቸውን መምህራን እና የትምህርት አመራሮችን “አቅም”፤ “እውቅና በመስጠት” ረገድ ማሻሻያ የተደረገባቸው ናቸውም ተብሏል። ትምህርት ሚኒስቴር መመሪያዎችን ከማሻሻል በተጨማሪ የመምህራን እና የትምህርት ቤት አመራሮችን አቅም ለማሳደግ በዚህ ዓመት ልዩ የክረምት ስልጠናዎችን እንደሚጀምርም በስብሰባው ላይ ተጠቁሟል።

ለመምህራን የሚሰጠው ይህ ስልጠና፤ “በሚያስተምሩት የትምህርት ይዘት እና ስነ ዘዴ ላይ” ያተኮረ መሆኑን በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን እና የትምህርት ልማት ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ አሰገደች ምሬሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በመጪው ክረምት ከ15 እስከ 20 ለሚሆኑ ቀናት “በተመረጡ ዩኒቨርስቲዎች” እንደሚሰጥ የሚጠበቀው ይህ ስልጠና፤ ይበልጡኑ ትኩረት የሚያደርገው “የሁለተኛ ደረጃ የሳይንስ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርቶች ላይ” መሆኑን ኃላፊዋ አስረድተዋል። 

“[ዕቅዳችን] ስልጠናውን ለሁሉም መምህራን ለማድረስ ነው። ነገር ግን በመጀመሪያ [ስልጠናውን] የምንሰጠው የተለዩ ቦታዎች ላይ ነው። ዘንድሮ ልንጀምር የምንችለው፤ በሁለተኛ ደረጃ መምህራን፣ በቅድመ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አመራሮች ነው” ሲሉ ወ/ሮ አሰገደች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ዕቅድ አብራርተዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር እነዚህን ስልጠናዎች ለማከናወን የሚያስችሉ “ሞጁሎችን” ከማዘጋጀት ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን ኃላፊዋ ገልጸዋል። የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናው፤ የመምህራንን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን መስሪያ ቤታቸው የዳሰሳ ጥናት እያደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በዚሁ መሰረት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን የተዘጋጀ የበይነ መረብ መጠየቅ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትላንትናው ዕለት በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ይፋ አድርጓል። መጠይቁን ሞልተው እንዲልኩ ጥሪ የቀረበላቸው፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሒሳብ፣ እንግሊዘኛ እና የተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዓይነቶችን የሚያስተምሩ መምህራን ናቸው። 

ከመምህራኑ የሚሰበሰቡት መረጃዎች፤ በዚህ ዓመት ለሚካሄደው ስልጠና “ጥራት” “አስተዋጽኦ” ያላቸው መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል። በዚህ የክረምት የስልጠና መርሃ ግብር፤ መምህራን 120 ሰዓት፣ ርዕሰ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች 60 ሰዓት እንዲሰለጥኑ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አበበ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  

ይህ ስልጠና “መምህራን አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያደርግ” መሆኑን የሚገልጹት አቶ ሽመልስ፤ “በጎለበተው አቅማቸው ልክ በትምህርት ስራው ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ” ብለዋል። በስልጠናው የሚያልፉ መምህራን “የትምህርት ጥራት ላይ ለውጥ ያመጣሉ” የሚል ተስፋ በማህበራቸው ዘንድ እንዳለ ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)