በደቡብ ወሎ ዋሻ የተናደባቸውን የማዕድን አውጪዎች ለማዳን፤ የመከላከያ ሰራዊት መሐንዲሶች ጥረት እያደረጉ መሆኑ ተነገረ 

በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ ደላንታ ወረዳ ዋሻ የተናደባቸውን የኦፓል ማዕድን አውጪዎች ህይወት ለማዳን፤ በመከላከያ ሰራዊት መሐንዲሶች የታገዘ አዲስ የነፍስ አድን ስራ ከትላንትና ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን የአካባቢው ባለስልጣናት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። በትላንትናው ዕለት ከተደረመሰው ዋሻ ተቆርጦ የቀረን ክፍል ደማሚት በመጠቀም ለማጽዳት የተደረገው ጥረት አለመሳካቱንም ተናግረዋል።

ከደላንታ ወረዳ ዋና ከተማ ወገል ጤና አቅራቢያ በሚገኝ ልዩ ስሙ “ቆቅ ውሃ” በሚል ቦታ የኦፓል ማዕድን በማውጣት ላይ የነበሩ ዘጠኝ ወጣቶች፤ ቁፋሮ ሲያከናውኑ የነበረበት ዋሻ የተናደባቸው ጥር 30፤ 2016 ለሊት ነበር። የአካባቢው ነዋሪዎች የወጣቶቹን ህይወት ለማትረፍ በእጅ በሚደረግ ቁፋሮ ከአንድ ሳምንት በላይ ጥረት ቢያደርጉም፤ እስካሁን ድረስ ማዕድን አውጪዎቹን ከዋሻው ማውጣት አልተቻለም።

የነፍስ አድን ቁፋሮው እስካለፉት ሶስት ቀናት ሲከናወን የቆየው “በባህላዊ መልኩ” እንደነበር የደላንታ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አያሌው በሪሁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህ አሰራር ቁፋሮውን በሚያከናውኑት የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ “ተጨማሪ አደጋ ይፈጥራል” የሚል ስጋት በመፈጠሩ፤ ይህንን ለመቀየር የሚያስችል ውይይት እና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ባለፉት ሶስት ቀናት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

በውይይቱ ላይ የነፍስ አድን ስራውን ለማገዝ ወደ አካባቢው የተጓዙ የመከላከያ ሰራዊት መሐንዲሶች፣ የወጣቶቹ ቤተሰቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት መሳተፋቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ አብራርተዋል። በዚሁ ውይይት ላይ የማዕድን አውጪዎቹ አባል የሆኑበት “ወርቅ ዋሻ ኦፓል ማህበር” አባላትም እንዲገኙ መደረጉንም ጠቁመዋል። 

የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑ የወጣቶቹ ቤተሰቦች እና የአካባቢው ነዋሪዎች “ከተቻለ ወጣቶቹን በህይወት መገኘት የሚችሉበት ዕድል ይሞከር። ካልሆነ ደግሞ አሉ የሚባሉ አማራጮችን ተጠቅሞ፤ አስክሬናቸውን ማግኘት የምንችልበትን ሁኔታ ይሞክርልን” የሚል ሃሳብ ማቅረባቸውን የደቡብ ወሎ ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ እያሱ ዮሐንስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ወደ ቀጣይ ስራ የተገባው፤ በውይይቱ ላይ “የጋራ መግባባት ላይ” ከተደረሰ በኋላ መሆኑንም አመልክተዋል።

ይህን ተከትሎም የመከላከያ ሰራዊት መሐንዲሶች፤ ዋሻው በሚደረመስበት ወቅት ተንጠልጥሎ የቀረውን ክፍል በትላንትናው ዕለት በደማሚት ፈንጂ ለማፍረስ ሙከራ ማድረጋቸውን ሁለቱ የአካባቢው ባለስልጣናት አረጋግጠዋል። ሆኖም “ትላንት የነበረው ስራ በሚፈለገው ልክ ውጤት አለማምጣቱ” ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም ከውሳኔ ላይ መደረሱን አክለዋል። 

ፎቶ ፋይል፦ በደላንታ ወረዳ የኦፓል ማዕድን ከሚገኝባቸው ስፍራዎች አንዱ (ከያባኮን ጂም ስቶን የተወሰደ )

ተቆርጦ የቀረው የዋሻው ክፍል በድማሚት ከተመታ በኋላ ጭምር በቦታው ላይ ጸንቶ መቆየቱ፤ የዋሻው የታችኛው ክፍል በሚቆፈርበት ወቅት “ይደረመሳል” የሚለውን ስጋት ማስወገዱን የደላንታ ወረዳ አስተዳዳሪ አስረድተዋል። በዛሬው ዕለት “የሰው ኃይል እና ሌሎች መርጃ መሳሪያዎችን የማደራጀት ስራ” ሲከናወን መዋሉን የገለጹት አስተዳዳሪው፤ በነገው ዕለት ቁፋሮ ለማካሄድ እና ሌሎች አማራጮችን ለመሞከር “ወደ ቦታው እንደሚገባ” ተናግረዋል።

የማዕድን አውጪዎቹ ዋሻ ከተናደባቸው ዛሬ 12ኛ ቀናቸውን ቢያስቆጥሩም፤ በአካባቢው ባለስልጣናት ዘንድ ግን አሁንም ወጣቶቹን በሕይወት የማግኘት ተስፋ አልተሟጠጠም። በዋሻው ውስጥ “ውሃ እንዳለ” የሚጠቅሱት የደቡብ ወሎ ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ፤ ወጣቶቹ “ውሃውን እየቀመሱ በህይወት ያቆያሉ” የሚል ተስፋ እንዳለ ጠቁመዋል። የማዕድን አውጪዎቹ ዋሻው ውስጥ “በቂ ኦክስጅን ሊያገኙ ይችላሉ” የሚል ተስፋ መኖሩንም ጨምረው ገልጸዋል። 

የአካባቢው ባለስልጣናትም ሆነ ነዋሪዎቹ ይህን ተስፋ እንዲሰንቁ ያደረጋቸው፤ በደላንታ ወረዳ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ተመሳሳይ አደጋ ከተከሰተ ከ11 ቀናት በኋላ የማዕድን አውጪዎችን ህይወት ማትረፍ በመቻሉ ነው። በደላንታ ወረዳ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አብዮት ጌታሁን ይህንኑ ሀሳብ ከሚጋሩት አንዱ ናቸው።  

“ከዚህ ቀደም በ11 ቀናት የተረፈ አካል ስላለ እና የዋሻው ውስጡ ውሃማ ስለሆነ፣ እርሱ ጋር እርጥበት ስላለው፣ ከፈጣሪ ጋር በህይወት እናገኛቸዋለን የሚል ተስፋ ነው ያለን

– አቶ አብዮት ጌታሁን፤ የደላንታ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ

“ከዚህ ቀደም በ11 ቀናት የተረፈ አካል ስላለ እና የዋሻው ውስጡ ውሃማ ስለሆነ፣ እርሱ ጋር እርጥበት ስላለው፣ ከፈጣሪ ጋር በህይወት እናገኛቸዋለን የሚል ተስፋ ነው ያለን። ነገር ግን እንዲሁ በቀላሉ [መፍትሄ የሚያገኝ] ስላልሆነ፤ ከአማራ ክልል ጭምር ያሉ አካላት ስራውን እየተረባረቡበት ነው። መጨረሻውን የሚያውቀው ፈጣሪ ነው” ሲሉ አቶ አብዮት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በደቡብ ወሎ ዞን ኦፓል የሚገኝባቸው ስፍራዎች የመልክዐ ምድር አቀማመጥ አስቸጋሪ መሆን፤ የማዕድን አውጪዎችን ለተመሳሳይ አደጋ ሲያጋልጣቸው ቆይቷል። የአካባቢዎቹ ተራራማ ዳገታማነት የማዕድን አውጪዎች “ማሽነሪዎች” እንዳይጠቀሙ በማድረጉ፤ ቁፋሮው ላለፉት 13 ዓመታት ሲከናወን የቆየው በሰው እጅ ነው። 

ከመንግስት ፍቃድ አግኝተው፤ በዚህ መልክ በደላንታ ወረዳ ስራቸውን የሚያከናወኑ 27 ማህበራት እንዳሉ ከአካባቢው ባለስልጣናት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። እነዚህ ማህበራት እያንዳንዳቸው በስራቸው ከስድስት መቶ በላይ አባላትን ያቀፉ ናቸው። የአሁኑ አደጋ የደረሰባቸው ወጣቶችን ያቀፈው የ“ወርቅ ዋሻ ኦፓል ማህበር” 640 የተመዘገቡ አባላት ቢኖሩትም፤ በአጋዥነት የሚሳተፉትን ጨምሮ በአጠቃላይ አንድ ሺህ ሰዎች በማህበሩ ስር እንዳሉ ይገመታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)