ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩት ከፍተኛ አመራሮቹ ውስጥ፤ ኬሪያ ኢብራሂም እና ሙሉ ገብረ እግዚብሔርን ከማዕከላዊ ኮሚቴ እና ከፓርቲ አባልነታቸው ማሰናበቱን አስታወቀ። በእስር ላይ ከነበሩ አመራሮች መካከል ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ እና ዶ/ር አብርሃ ተከስተ በፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲቀጥሉ ውሳኔ አሳልፏል።
ህወሓት በከፍተኛ አመራሮቹ ላይ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ትላንት ሐሙስ የካቲት 15፤ 2016 ካደረገው ስብሰባ በኋላ መሆኑን ገልጿል። ህወሓት በጦርነቱ ወቅት “በጠላት እጅ ወድቀው ነበር” ያላቸውን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በተመለከተ “ለረጅም ጊዜ ሲንጓተት” የቆየውን ያስተላለፈው ውሳኔ፤ የነበሩትን ሁኔታዎች በመገምገም እና የፓርቲውን ህገ ደንብ በመከተል መሆኑን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በዚህም መሰረት “እጃቸውን ለጠላት በመስጠት” እና “ምስጢር አሳልፈው በመስጠት” የተገመገሙት የቀድሞው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም እና የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉ ገብረ እግዚብሔር፤ ከማዕከላዊ ኮሚቴ እና ከፓርቲ አባልነታቸው “መባረራቸውን” ህወሓት አስታውቋል። በትላንቱ ሰብሰባ “ከባድ ጸጸት” እንደተሰማቸው መግለጻቸው የተነገረላቸው ሁለቱ ተሰናባቾች፤ ወደፊት “በተሰማሩበት የስራ መስክ ህዝቡን ለመካስ እንደሚሰሩ” ቃል መግባታቸውን የፓርቲው መግለጫ ጠቅሷል።

ኬሪያ በፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር የዋሉት በትግራይ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከአንድ ወር በኋላ ነበር። የእርሳቸውን መያዝ በተመለከተ በወቅቱ መረጃውን ይፋ ያደረጉ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን፤ ኬሪያ በገዛ ፍቃዳቸው “ለመንግስት እጃቸውን መስጠታቸውን” መዘገባቸው ይታወሳል። በወቅቱ የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት ኬሪያ፤ “በመከላከያ ሰራዊ ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም” እና “በሀገር ክህደት ወንጀል” ተጠርጥረው የእስር መያዣ ትዕዛዝ ከወጣባቸው 96 ሰዎች መካከል አንዷ ነበሩ።
ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች አንዷ የነበሩት የፓርላማ አባሏ ሙሉ ገብረ እግዚያብሔር በቁጥጥር ስር የዋሉት ከኬሪያ መያዝ ከአንድ ወር በኋላ ነበር። ሁለቱ ተጠርጣሪዎች፤ 62 ግለሰቦች እና ድርጅቶች በተካተቱበት መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው በሐምሌ 2013 ዓ.ም. ነው። የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተጠርጣሪዎቹን የከሰሰው፤ “በሕገ መንግስትና በሕገ መንግስት ስርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀልን እንዲሁም የሽብርተኝነት ድርጊቶች” ፈጽመዋል በሚል ወንጀል ነበር።
በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በተከፈተው በዚህ መዝገብ ከተካተቱ 52 ግለሰቦች ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉት 21 ተከሳሾች ብቻ ነበሩ። ከሃያ አንዱ ተከሳሾች መካከል ስድስቱ በታህሳስ 2014 ዓ.ም. ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ተለቅቀዋል። የፍትሕ ሚኒስቴር “የጤና እና የዕድሜ ሁኔታቸውን ከግምት በማስገባት” ክሳቸው እንዲቋረጥ ማድረጉን በወቅቱ ካስታወቀላቸው ተከሳሾች መካከል ሙሉ ገብረ እግዚያብሔር ይገኙበታል።

የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት ኬሪያ ኢብራሂም፣ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ እና ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማን ጨምሮ ቀሪዎቹ የድርጅቱ አባላት፤ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተለቀቁት በመጋቢት 2015 ዓ.ም. ነበር። የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በትላንትናው ዕለት ባካሄደው ስብሰባ፤ ዶ/ር አብርሃም እና ዶ/ር አዲስ አለም በፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲቀጥሉ መወሰኑን አስታውቋል።
እንደ እነርሱ ሁሉ በፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት፤ ዶ/ር ሰሎሞን ኪዳኔ፣ ዶ/ር ረዳኢ በርሄ፣ ወ/ሮ ኪሮስ ሃጎስ እና አቶ አጽብሃ አረጋዊም በተመሳሳይ ሁኔታ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲቀጥሉ ውሳኔ ማስተላለፉን ህወሓት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በትላንቱ ስብሰባው፤ ህወሓት በቀጣይነት ለሚያካሄደው 14ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ የሚሆኑ ሶስት አባላትን መርጧል። በኮሚቴው አባልነት የተመረጡት ፈትለወርቅ ገብረእግዚያብሔር (ሞንጆሪኖ)፣ ወ/ሮ አልማዝ ገብረጻድቅ እና አቶ ኢሳያስ ታደሰ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)