የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ በሁለት ወራት ውስጥ እንዲካሄድ ውሳኔ ተላለፈ

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ድርጅታዊ ጉባኤ በሁለት ወራት ውስጥ እንዲካሄድ፤ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የቁጥጥር ኮሚሽን ዛሬ ባካሄዱት የጋራ ስብሰባ ውሳኔ አስተላለፉ። ከአምስት ዓመት በኋላ በሚካሄደው በዚህ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ አጀንዳዎችንም፤ ሁለቱ አካላት በዛሬው ስብሰባ መለየታቸውንም አስታውቀዋል። 

ህወሓት 13ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ያካሄደው በመስከረም 2011 ዓ.ም. ነበር። በመቐለ ከተማ ለስድስት ቀናት ከተካሄደው ከዚህ ድርጅታዊ ጉባኤ መጠናቀቅ በኋላ፤ ህወሓት “ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እና ህገ መንግስቱን ተቀብለው ከሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት” ዝግጁ መሆኑን አስታውቆ ነበር። 

ሆኖም ህወሓት አባል የነበረበት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ውህድ ፓርቲ ለመሆን መወሰኑን ተከትሎ፤ ድርጅቱ ከአንድ ዓመት ከሶስት ወር በኋላ አስቸኳይ ጉባኤ ለመጥራት ተገድዷል። ህወሓት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በጠራው በዚህ አስቸኳይ ጉባኤ፤ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን መዋሃድ እና የብልጽግና ፓርቲን መመስረት መቃወሙ ይታወሳል። 

ይህ የድርጅቱ አስቸኳይ ጉባኤ ከተካሄደ በኋላ ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ ጋር ልዩነቱ እየተካረረ የመጣው ህወሓት፤ ከጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ዓመት ያህል በጦርነት ውስጥ መቆየቱ አይዘነጋም። ህወሓት ከፌደራል መንግስት ጋር የግጭት ማቆም ስምምነት በጥቅምት 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተፈራረመ በኋላ፤ በትግራይ ክልል በተመሰረተው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ትልቁን ድርሻ ይዞ ክልሉን እየመራ ይገኛል። 

ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ ግምገማዎችን በተለያዩ ጊዜያት ሲያካሄድ የቆየው ህወሓት፤ በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ የተካሄደውን እና ሁለት ወራትን የፈጀ ስብሰባ ያጠናቀቀው ባለፈው ጥር ወር ነበር። ህወሓት በዚሁ ስብሰባ ማጠናቀቂያ ላይ፤ ድርጅታዊ ጉባኤ እንዲካሄድ የሚያስችል ዝግጅት እንዲደረግ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። 

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በትላንትናው ዕለት ባካሄደው ስብሰባ ፤ ህወሓት በቀጣይነት ለሚያካሄደው 14ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ የሚሆኑ ሶስት አባላትን መርጧል። በኮሚቴው አባልነት የተመረጡት ፈትለወርቅ ገብረእግዚያብሔር (ሞንጆሪኖ)፣ ወ/ሮ አልማዝ ገብረጻድቅ እና አቶ ኢሳያስ ታደሰ ናቸው።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የፓርቲው የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን በዛሬው ዕለት ባካሄዱት ስብሰባ፤ የአዘጋጅ ኮሚቴው ስራውን “በፍጥነት እንዲጀምር” መወሰናቸውን አስታውቋል። ከጉባኤው ጋር በተያያዘ የዞን እና በወረዳ የሚገኙ የህወሓት ካድሬዎች በሚቀጥለው ሳምንት በክልል ደረጃ ስብሰባ እንደሚያካዱ ፓርቲው ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። 

ከዚህ ስብሰባ መጠናቀቅ በኋላ በትግራይ ክልል በዞን፣ በወረዳ እና በጣቢያ ደረጃ ያሉ አመራሮች፣ የህወሓት አባላት እና የህዝብ ተወካዮች መድረክ እንደሚቀጥልም ፓርቲው ገልጿል። እነዚህን ስብሰባዎች ተከትሎ ከሚካሄደው ክልላዊ ኮንፍረንስ በኋላ፤ የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ እንደሚከናወንም በመግለጫው ተጠቅሷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)